በሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሀመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ላይ የቀረበው ክስ ውድቅ ሆነ

ፕሬዝዳንት መሀመድ አብዱላሂ ፋርማጆ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሀመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ላይ በሃገሪቱ ፓርላማ አባላት ላይ ከስልጣናቸው እሰከመባረር የሚያደርሰው በቂ የፓርላማው አባላትን ድጋፍ ባለማግኘቱ ውድቅ ተደረገ።

እሁድ ዕለት በሃገሪቱ ሕግ አውጪ ምክር ቤት አባላት በፕሬዝዳንቱ ላይ የቀረበው እንዲከሰሱ የሚጠይቀው የውሳኔ ሃሳብ አስፈላጊ ቁጥር ባላቸው የምክር ቤቱ አባላት ድጋፍ ማግኘት አልቻለም።

ከሶማሊያ ፓርላማ ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ እንዳመለከተው መጀመሪያ ላይ በፕሬዝዳንቱ ላይ እምነት እንደሌላቸው በመጥቀስ ክሱን ካቀረቡት 92 የምክር ቤት አባላት መካከል 14ቱ ከጥያቄው እራሳቸውን በማግለላቸው ነው የውሳኔ ሃሳቡ ውድቅ የተደረገው።

በዚህም ሳቢያ በፕሬዝዳንት ፋርማጆ ላይ የቀረበውን ክስ ለምክር ቤቱ ለማቅረብ የሚያስችል ፊርማ ከፓርላማ አባላቱ ስላልተገኘ ጥያቄው ውድቅ ሆኗል ተብሏል።

በፕሬዝዳንቱ ላይ ከቀረበው የክስ ማመልከቻ ዝርዝር ውስጥ እራሳቸውን ያገለሉት 14 የፓርላማ አባላት እንዳሉት ስማቸው በስህተት መካተቱንና በፕሬዝዳንቱ ላይ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ እንደማይደግፉት ተናግረዋል።

በፕሬዝዳንቱ ላይ ይህንን የውሳኔ ሃሳብ ያቀረቡት የምክር ቤት አባላት ዋነኛ ክስ ፕሬዝዳንት ፋርማጆ የሃገሪቱን ሕገ መንግሥት በመጣስ ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ጋር ምስጢራዊ ስምምነት ተፈራርመዋል የሚል ሲሆን በተጨማሪም በተናጠል ዳኞችን እንዲሁም የጦር ሠራዊት አዛዦችን ሾመዋል የሚል ነው።