ያለጠበቃ ችሎት የቀረቡት ታዬ ደንደአ ‘ጠበቆቼ ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ነው’ ሲሉ አቤቱታ አቀረቡ

የፎቶው ባለመብት, Prosperity Party
የወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ አቶ ታዬ ደንደአ “ጠበቆቼ ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ነው” ሲሉ ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቀረቡ።
አቶ ታዬ ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 18/2016 ዓ.ም. ችሎት ሲቀርቡ ከአምስቱ ጠበቆቻቸው አንዳቸውም ሳይገኙ ቀርተዋል።
የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ እና የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባል ፀረ ሰላም ኃይሎችን በመደገፍ እና ጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት በሚሉ ወንጀሎች ተከሰው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገ መንግሥት እና የሽብር ወንጀል ችሎት ጉዳያቸው እየታየ እንደሚገኝ ይታወቃል።
ችሎቱ ሐሙስ ግንቦት 29/2016 ዓ.ም. ዐቃቤ ሕግ በአቶ ታዬ ላይ ያቀረባቸውን የሁለት ምስክሮች ቃል ተቀብሎ ውሳኔ ለምስጠት ለዛሬ ሰኔ 18/2016 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።
ይሁን እንጂ በችሎቱ ላይ የተገኙ ዳኞች በመዝገብ መብዛት ምክንያት የአቶ ታዬ ደንደአ ጉዳይ ሳይታይ መቅረቱን በመግለጽ ለሐምሌ 17/2016 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ አቶ ታዬ በጠበቆቻቸው ላይ ከባድ ያሉት ማስፈራሪያ እየደረሰ መሆኑን በመናገር ማስፈራሪያውን ፍርድ ቤቱ እንዲያስቆም ጠይቀዋል።
“ዐቃቤ ሕግ እና የእሱ ሰዎች ጠበቆቼን እያስፈራሩ ነው” ያሉት አቶ ታዬ፤ ቁጥሩ በማይታይ ስልክ እየተደወለላቸው ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው መሆኑንም ለችሎቱ ተናግረዋል።
በአቶ ታዬ ደንዳአ መዝገብ ላይ አምስት ጠበቆች ተመዝግበው ቢገኙም በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ ግን ሁሉም ጠበቆች ሳይገኙ ቀርተዋል።
በዚህም ምክንያት አቶ ታዬ ብቻቸው ከችሎቱ ፊት ቀርበው አቤቱታቸውን በራሳቸው አንደበት አቅርበዋል።
ከአምስቱ ጠበቆቻቸው በሁለቱ ላይ “ከደኅንነት መሥሪያ ቤት ነው የምንደውለው” በሚሉ ግለሰቦች ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ነው ያሉት አቶ ታዬ፤ በተቀሩት ሦስት ጠበቆቻቸው ላይ ማስፈራሪያ እየተሰነዘረ ስለመሆኑ መረጃው እንደሌላቸው ተናግረዋል።
ዳኞችም በአገሪቱ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 20 መሠረት ተከሳሾች በመረጡት የሕግ ጠበቃ የመወከል መብት እንዳላቸው በማስታወሰ፤ በጠበቆች ላይ ተጨባጭ የሆነ ማስፈራሪያ እየደረሰ ከሆነ የፍትህ ሂደቱን እንደሚያጓድል ተናግረዋል።
ዳኞቹ በጉዳዩ ላይ ውይይት እንደሚያደርጉ ጭምር ተናግረዋል።
በዛሬው ችሎት አቶ ታዬ ደንደአ በፌደራል ፖሊስ እጅ ይገኛሉ ስላሏቸው የግል የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች ቅሬታ አቅርበዋል።
አቶ ታዬ ምንም እንኳ ፍርድ ቤቱ በኤግዚቢትነት ያልተያዙ ሁለት ሞባይል ስልኮች እና አንድ ታብሌት እንዲመለስላቸው ቢያዝም የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎቹ እስካሁን እንዳልተመለሱላቸው ተናግረዋል።
ፌደራል ፖሊስ በበኩሉ ዛሬ ለፍርድ ቤቱ በላከው ደብዳቤ ከላይ የተጠቀሱት የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች በኤግዚቢት የተያዙ ስለመሆናቸው ገልጿል።
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎቹ በክስ መዝገቡ ላይ በኤግዚቢትነት ተመዝግበው ስለማይገኙ ዕቃዎቹ ለተከሳሹ እንዲመለሱ በድጋሚ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
አቶ ታዬ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ሆነው በመንግሥት ውስጥ የሚፈጸሙ ተገቢ አይደሉም የሚሏቸውን ድርጊቶች ለመገናኛ ብዙኃን በመናገር እና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በማስፈር ይታወቃሉ።
የቀድሞው ባለሥልጣን በቀጥታ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጻፈ የስንብት ደብዳቤ ከኃላፊነታቸው በተነሱበት ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩን አጥብቆ የሚያወግዝ ጽሁፍ በፌስቡክ ላይ አስፍረው ነበር።
አቶ ታዬ ከሥልጣን መነሳታቸው ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የተቹበትን ጽሁፍ ካሰፈሩ ከሰዓታት በኋላ ነበር በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋሉት።
የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ታዬ ደንዳአ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በምክር ቤቱ ያለመከሰስ መብታቸው መነሳቱ ይታወሳል።












