እርቃን ፎቶዎችን እንደ ማስፈራሪያ በመጠቀም ገንዘብ የማግኛ መመሪያዎችን የሚሸጡት ወንጀለኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ወሲባዊ ይዘት ያላቸውን ፎቶዎች ወይም ቪዲዮዎች እንደ ማስፈራሪያ በመጠቀም ገንዘብ እንዴት ማግኘት ይችላሉ የሚሉ መመሪያዎችን በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሸጡ ወንጀለኞች እንዳሉ ቢቢሲ ደርሶበታል።
መመሪያዎቹ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ ወጣት ሴቶችን መስሎ እንዴት መቅረብ እንደሚቻል፣ ወሲባዊ ይዘት ያላቸውን ፎቶዎች ወይም ቪዲዮዎች እንዲላክላቸው በማታለል በመጨረሻም ያንን እንዴት እንደ ማስፈራሪያነት መጠቀም ይቻላል የሚሉ መረጃዎችን ይዟል።
ባለፈው ግንቦት ወር ኦላሚዴ ሻኑ የተባለ ግለሰብ ከዚህ ጋር በተያያዘ ክስ ተመስርቶበት በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ለንደን ውስጥ ፍርድ ቤት ቀርቧል።
ግለሰቡ ኢንርኔትን በመጠቀም ታዳጊዎችን ጨምሮ ሰዎችን በማስፈራራት 2 ሚሊዮን ፓውንድ አግኝቷል የተባለ የወሮበሎች ቡድን አባል እንደሆነ ይታመናል።
ባለፈው ወር የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የወንጀል ኤጀንሲ በእንግሊዝኛው ‘ሴክስቶርሽን’ በሚባለው ወሲባዊ ይዘቶችን ለማስፈራሪያነት በመጠቀም ገንዘብ ማግኛ ማድረግ አደገኛነቱ እየጨመሩ መሆኑን በመግለጽ በመላው ዩናይትድ ኪንግደም ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
መቀመጫቸውን በምዕራብ አፍሪካ በተለይም በናይጄሪያ ባደረጉ ቡድኖች ሰለባ እየሆኑ ያሉ ታዳጊዎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።
በዩኬ ውስጥ ሁለት ታዳጊዎች ወሲባዊ ይዘቶችን ለማስፈራሪያነት በሚጠቀሙ ግለሰቦች ሰለባ መሆናቸውን ተከትሎ ሕይወታቸውን አጥፍተዋል።
የደኅንንት ባለሙያ እና በሴክስቶርሽን ወንጀል ጥልቅ እውቀት ያላቸው ፖል ራፊል ይህንን ወሲባዊ ይዘቶችን ገንዘብ ለማግኘት እንደ ማስፈራሪያ የመጠቀሙን ጉዳይ በልጆች ላይ የተጋረጠ ‘ትልቅ ስጋት’ ነው ሲሉ ነው የሚገልጹት።
“ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የኢንተርኔት አጭበርባሪዎች ይህንን በመጠቀም በፍጥነት ሃብታም እንደሚሆኑ ደርሰውበታል። በዚህ ደግሞ ሰለባዎቹ ታዳጊዎች ናቸው” ይላሉ።

ከዚህ ቀደም ለዓመታት የዚህ ወንጀል ኢላማ ሆነው የቆዩት አዋቂዎች እንደነበሩ የሚናገሩት የደኅንነት ባለሙያው በአሁኑ ወቅት በአስራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ በተለይም ታዳጊ ወንዶች በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ሆነዋል ይላሉ።
እነዚህ ወንጀለኞች “በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን እና የታዳጊ የስፖርት ቡድኖችን ኢላማ በማድረግ ሰለባዎችን እያገኙ ነው” ይላሉ።
እነዚህን ወሲባዊ ይዘቶች እንደ ማስፈራሪያ በመጠቀም ገንዘብ ማግኘት የሚያስችሉት መመሪያዎች በኢንተርኔት ላይ በተለጠፉ ቪዲዮዎች እንደሚሸጡ ቢቢሲ ባደረገው ማጣራት ደርሶበታል።
መመሪያዎቹ ክትትል የማይደረግባቸውን ስልክ ቁጥሮች እንዴት ማውጣት እንደሚቻል፣ ሐሰተኛ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ማውጣት እና ደኅንነታቸው የተጠበቁ የመክፈያ ዘዴዎችን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል በዝርዝር ማብራሪያ ይዟል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አንዳንዶች እንዴት እነዚህን በመጠቀም ምን ያህል ሰዎች እንዳስፈራሩ የሚናገሩት በኩራት ነው።
አንደኛው ግለሰብ በየሳምንቱ አርብ የሚያስከፍለው ሰው እንደነበር ጽፏል።
ሉሲ የተባለች ግለሰብ የ14 ዓመት ልጇ ይህንን የሚያደርጉ ቡድኖች ሰለባ ውስጥ ከሆኑት አንዱ እንደነበር ገልጻለች።
ታዳጊው የራሱን ምሥል ባይልክም ግለሰቦቹ ፎቶውን ኤዲት በማድረግ በአንድ ጽሁፍ ውስጥ አድርገው በኢንተርኔት ላይ እናጋራዋለን ሲሉ አስፈራርተውታል።
“በ24 ሰዓት ውስጥ ገንዘብ ካልላክልን ይህንን ፎቶ ለሚያውቁህ ሰዎች ሁሉ እንልካለን” የሚል መልዕክት ታዳጊው እንደደረሰው እናቱ ለቢቢሲ ገልጻለች።
“በጣም ደንግጦ ነበር። አካሉም እየተንቀጠቀጠ ነበር” ትላለች ሁኔታውን ስታስታውስ።

ታዳጊው ለሚያስፈራሩት ሰዎች 100 ፓውንድ ከፍሎ የነበረ ቢሆንም በወላጆቹ እርዳታ አካውንቱን እና ስልኩን ከዘጋ በኋላ የሚያስፈራሩት ሰዎችም አቆሙ።
“የዚያን ቀን ጥዋት ቤት ውስጥ አንድ ላይ ባንሆን፤ ስለተፈጠረው ጉዳይ ባይነግረኝ ኖሮ ምን እንደሚሆን አላውቅም ነበር” ትላለች እናት።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት በዌስትሚኒስትር ፍርድ ቤት የቀረበው ኦላሚዴ ተላልፎ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበዋል።
የ33 ዓመቱ ወጣት በአይዳሆ ግዛት በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ በማስፈራራት ገንዘብ በማግኘት እና በሳይበር ወንጀል ክሶች ቀርበውበታል።
ክሶቹ አንድ ታዳጊን ጨምሮ አራት ተጎጂዎች ላይ የተፈጸሙ ድርጊቶችን የሚመለከቱ እንደሆነ ተጠቅሷል።
ሆኖም መርማሪዎች ባለፉት ሦስት ዓመታት በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጎጂዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያምናሉ።
የደኅንነት ባለሙያው ፖል ትልልቆቹ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የ‘ሴክስቶርሽን’ ወንጀልን ለማስቆም በቂ ሥራ እየሠሩ አይደለም ይላሉ።
“ወንጀሎቹ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በኢንስታግራም እና በስናፕቻት ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የተዛመቱ ሲሆን፣ እነዚህ መድረኮች ወንጀለኞችን በመከታተሉ ረገድ በተጠናከረ ሁኔታ ሊሠሩ ይገባል” ሲሉም ለቢቢሲ አስረድተዋል።
“ሾልከው የወጡ ወሲባዊ ይዘቶችን እና ሪፖርት የማቅረቢያ አማራጭን ጨምሮ ይህንን ለመታገል ጥረታችንን እያጠናከርን ነው። በተጨማሪም ለታዳጊዎች በመተግበሪያችን ትምህርት እየሰጠን ነው” ሲል እነዚህ ወንጀሎች ይፈጸሙበታል የተባለው ስናፕቻት የተሰኘው ማኅበራዊ ሚዲያ ለቢቢሲ ገልጿል።

የኢንስታግራም ባለቤት የሆነው ሜታ በበኩሉ “ግላዊ የሆኑ ምሥሎችን ለማጋራት የሚያስፈራሩ ሰዎችን በተመለከተ ተጠቃሚዎች ሪፖርት ማድረግ የሚችሉበት የተለየ አማራጭ ቀርቧል” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
አክሎም “በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ወደ ኢንስታግራም በሚመጡበት ወቅት ተከታዮቻቸውን እና የሚከተሏቸውን ዝርዝር ማንነት የሚደብቅ እንዲሁም የመልዕክት መላላኪያቸውም ጥብቅ በሆነ መንገድ እንዲሆን አድርገናል” ብሏል።
ቲክ ቶክ በበኩሉ ማኅበራዊ ሚዲያው ዲዛይን የተደረገበት መንገድ “ታዳጊዎች ላይ ጉዳት ለማድረስ ለሚያስቡ በማይመች መልኩ እንዲሆን ተደርጎ ሲሆን፣ ወሲባዊ ይዘቶችን ለገንዘብ ማግኛ በሚል እንደ ማስፈራሪያነት የሚያበረታቱ ማንኛውን ነገሮች አንታገስም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።













