ዩኬ የህጻናት ደፋሪዎች ወላጅነት መብትን ይነጥቃል የተባለ ህግ ልታወጣ ነው

ህጻን ልጅ የያዘ ግለሰብ

ዩናይትድ ኪንግደም በከባድ ወሲባዊ ጥቃቶች የተከሰሱ ህጻናት ደፋሪዎች በልጆቻቸው ላይ ያላቸውን መብትይነፍጋል የተባለ አዲስ ህግ ልታወጣ ነው።

ለዚህ አዲስ ህግ መነሻ የሆነው አንዲት እናት ህጻናትን ደፋሪ ነው የተባለው የቀድሞ ባለቤቷ ከልጃቸው ጋር እንዳይገናኝ ለማድረግ 30 ሺህ ፓውንድ ለህጋዊ ክፍያ ማውጣታቸውን ቢቢሲ መዘገቡን ተከትሎ ነው።

ይህንንም ታሪክ የሰሙት የሌበር ፓርቲ ተወካይ ሃሪየት ሄርማን በህጉ ላይ ማሻሻያ አቅርበዋል።

ህጉ የከፋውን ወሲባዊ ጥቃት ከ13 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን የመድፈርን ወንጀል ይሸፍናል ተብሏል።

በወሲባዊ ጥቃቶች ጥፋተኛ የሆኑ በህጻናት ላይ ወሲባዊ ዝንባሌ ያላቸው ግለሰቦች (ፒዶፋይልስ) የወላጅነት መብታቸውን ወዲያውኑ የሚገፈፍ ይሆናል ሲሉም ሃሪየት ሄርማን ገልጸዋል።

“የወላጅነት መብታቸው እንዲመለስ ለማድረግ ወደ ቤተሰብ ፍርድ ቤት ሄደው የወላጅነት መብታቸው የሚመለሰው ለልጃቸው የሚጠቅም መሆኑን ማሳመን ከቻሉ” ነው የሚሉት ፖለቲከኛዋ “በህጻናት ደፋሪዎች ላይ ይህ መሆኑ የማይመስል ነገር ነው” ብለዋል።

ቢቢሲ መረዳት እንደቻለው የፍርድ ቤቶች፣ የማረሚያ ቤቶች፣ የአመክሮ እና የህገመንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለው ሎርድ ቻንስለር በህግ ማሻሻያው ላይ መስማማታቸውን ነው።

“ህጉ የሌሎችን ልጆች ከደፋሪ የሚጠብቅ ቢሆንም የራሳቸውን ልጆች ግን አለመጠበቁ ገራሚ ነው” ሲሉም ፖለቲከኛዋ አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት እየተተገበረ ያለው ህግ በህጻናት ላይ ወሲባዊ ዝንባሌ ኖሯቸው ጥፋተኛ የሆኑ አባቶች በልጃቸው ላይ ያላቸውን መብት ይጠብቃል።

“ይህ በግልጽ ስህተት ነው። ምክንያቱም ግንባር ቀደም መሆን ያለበት የህጻናቱ መብት እንጂ የአባት መብት አይደለም” ሲሉም አስረድተዋል።

የሌበር ፓርቲ ምከትል ሊቀመንበር የነበሩት ሃሪየት ሄርማን በቢቢሲ ቱደይ ፕሮግራም ላይ የቤታንን ታሪክ ከሰሙ በኋላ የህጉን ማሻሻያ እንዳቀረቡ አስረድተዋል።

የተፈረደበት ህጻናት ደፋሪ የወላጅነት መብቱ ሳይነካ መቅረቱ የህጉን “አስገራሚ ችግር” አጉልቶ ያሳየና እንደ ቤታን ያሉ እናቶች ልጆቻቸውን ለመጠበቅ ረዥም የፍርድ ቤት እሰጣ ገባ ውስጥ እንዲገባ ማስገደዱንም አይቻለሁ ብለዋል።

ፖለቲከኛዋ ፍርድ ቤቶች እና ህጉ “ህጻናትን ለእናታቸው ከመተው ይልቅ ህጻናትን ለመጠበቅ ወደፊት መራመድ አለባቸው” ብለዋል።