መካከለኛው ምሥራቅ - ሄዝቦላህ፣ እስራኤል እና ኢራን ቀጣይ እርምጃቸው ምን ሊሆን ይችላል?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ የረዥም ጊዜ መሪ የነበሩት ሐሳን ናስራላህ በእስራኤል የአየር ጥቃት ተገድለዋል። ይህ ደግሞ የቀጣናውን ውጥረት አክርሮታል።
ይህ የእስራኤል እርምጃ በተለያዩ ግጭቶች የላሸቀውን ቀጣና ወደለየለት መጠነ ሰፊ ጦርነት እንዳይመራው ተሰግቷል። አሜሪካ እና ኢራንም እጃቸውን ሊሰነዝሩ ይችላሉ።
የአካባቢው ሁኔታ ወደየት ሊያመራ ይችላል?
ይህን ጥያቄ ለመመለስ ሦስት ጉዳዮችን መዳሰስ ይኖርብናል።
ሄዝቦላህ ምን ሊያደርግ ይችላል?
ሄዝቦላህ ከሰሞኑ የተለያዩ ጥቃቶች እየተሰነዘሩበት ይገኛል።
የቡድኑ ወታደራዊ ዕዝ ክፉኛ የተጎዳ ይመስላል። ነባር ከሚባሉት አዛዠች ግማሽ ያህሉ ተገድለዋል። ፔጀርስ እና ዎኪ ቶኪ በተባሉት የግንኙነት መሣሪያዎች የደረሰው አደጋ የቡድኑን ሰንሰለት የበጣጠሰ ነው። አብዛኛው የጦር መሣሪያ ክምቹትም በእስራአተል አየር ድብደባ ከጥቅም ውጪ ሆኗል።
መቀመጫቸውን አሜሪካ ያደረጉት የመካከለኛው ምሥራቅ ፀጥታ ተንታኝ ሞሐመድ አል-ባሻ “የናስራላህ መገደል ቡድኑ ላይ የሚያደርሰው ኪሳራ ከፍተኛ ነው” ይላሉ።
አክለውም “ግድያው ቡድኑን ከጥቅም ውጪ የማድረግ አቅም ያለው፤ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ክንፉን የሚያፈራርስ ሊሆን” እንደሚችል ይተነትናሉ።
ነገር ግን ይህ ፀረ-እስራኤል የሆነ ቡድን ሙሉ በመሉ ከጥቅም ውጪ ይሆናል አሊያም ከእስራኤል ጋር ለሚደረግ የሰላም ድርድር ይቀመጣል ብሎ መጠበቅ የማይታሰብ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ከመሪው መገደል በኋላ ሄዝቦላህ ትግሉን እንደሚቀጥል አስታውቋል። አሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች አሉት። አብዛኞቹ ሶሪያ በነበረው ጦርነት ልምድ አካብተው የመጡ እንዲሁም ለበቀል የተነሳሱ ናቸው።
ቡድኑ አሁንም ከባድ የሚባል የጦር መሣሪያ አለው። አብዛኞቹ የጦር መሣሪያዎች ረዥም ርቀት የሚጓዙ፣ አልመው የሚመቱ እና ዋና ከተማዋን ቴል-አቪቭን ጨምሮ ሌሎች የእስራኤል ከተሞች ድረስ መወንጨፍ የሚችሉ ናቸው።
በሕይወት ያሉ የቡድኑ አመራሮች እኒህ መሣሪያዎች ከመደምሰሳቸው በፊት ጥቅም ላይ እንዲያውሏቸው ጫና እንደሚደርስባቸው እሙን ነው።
ነገር ግን ሄዝቦላህ እኒህን መሣሪያዎች ተጠቅሞ የእስራኤል የአየር መቃወሚያ ጥሶ ሰላማዊ ዜጎችን ከገደለ የእስራኤል ምላሽ አሁን ከምናየውም የከፋ ሊሆን ይችላል። እስራኤል ሊባኖስ ላይ መአት ልታወርድ ትችላለች። ከዚህ ጥቃት በኋላ እስራኤል ኢራንን ዝም ትላታለች ማለትም ዘበት ነው።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ኢራን ምን ልታደርግ ትችላለች?
የናስራላህ ግድያ ሄዝቦላህ ላይ ያደረሰው ኪሳራ ኢራንንም የጎበኘ ነው። ቴህራን ናስራላህን ለመዘከር የአምስት ቀናት ሐዘን አውጃለች።
አልፎም ሌሎች የደኅንነት እርምጃዎችንም ወስዳለች። ለምሳሌ መሪዋ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ እንዳይገደሉ በመስጋት አድራሻቸውን ደብቃለች።
ኢራን መሰል ኪሳራ ሲገጥማት ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ባለፈው ሐምሌ የሐማስ የፖለቲካ ክንፍ መሪ የነበሩት ኢስማኢል ሃኒያ የተገደሉት ዋና ከተማዋ ቴህራን ውስጥ ሳሉ ነበር።
አሁን በቀጣናው እየሆነ ያለው ነገር የኢራን አገዛዝ ሰዎች እርምጃ እንዲወስዱ ሊያስገድዳቸው ይችላል።
ኢራን ሄዝቦላህ እና ሐማስን ጨምሮ የየመን ሁቲዎችን እንዲሁም በኢራቅ እና ሶሪያ ያሉ ሌሎች ታጣቂ ቡድኖችን ትደግፋለች። ቴህራን እኒህ ቡድኖች በእስራኤል እና በአካባቢው ባሉ የአሜሪካ ካምፖች ላይ ጥቃት እንዲከፍቱ ልታደርግ ትችላለች።
ነገር ግን ኢራን የትኛውንም ዓይነት እርምጃ ብትወስድ ቀጣናውን ወደ ከፍ ጦርነት ከመክተት የሚመልሰው አይመስልም።
እስራኤል ምን ልታደርግ ትችላለች?
ከናስራላህ ግድያ በፊት የእስራኤልን አቅም የተጠራጠሩ ሰዎች አሁን ሊገረሙ ይችላሉ።
እስራኤል ወዳጇ አሜሪካንን ጨምሮ 12 አገራት ያወጡትን የ21 ቀናት የተኩስ አቁም ዕቅድ ተቀብላ አፈሙዟን የምታበርድ አትመስልም።
የእስራኤል ጦር ኃይል አሁን በማፈግፈግ ላይ ያለው ሄዝቦላህን በማጥቃት የሚሳዔል ክምቹን ማውደም ይፈልጋል።
ቢሆንም ይህ የሄዝቦላህን የሚሳዔል ክምችት ሙሉ በሙሉ የማውደም ዕቅድ ሊሳካ የሚችል የእስራኤል ጦር የእግረኛ ዘመቻ በምድር ላይ ሲሰነዝር ብቻ ነው ብለው የሚያምኑ ብዙዎች ናቸው።
የእራኤል የመከላከያ ኃይል አሊያም አይዲኤፍ ወታደሮች በእስራኤል እና ሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ ልምምድ ሲያደርጉ የሚያሳይ ምሥል ወጥቷል። የልምምዱ ዓላማ ወደ ሊባኖስ ለመግባት ይመስላል።
ነገር ግን ሄዝቦላህ ያለፉትን 18 ዓመታት በተለይ ደግሞ ካለፈው የሁለቱ አገራት ጦርነት ማብቂያ ጀምሮ ለሚመጣው ጦርነት ሲዘጋጅ ነበር።
ናስራላህ ከመገደላቸው በፊት ባደረጉት ንግግር የእስራኤል ጦር ወደ ደቡብ ሊባኖስ ዘልቆ ከገባ “ታሪካዊ ዕድል” ይፈጠራል ሲሉ ለተከታዮቻቸው ተናግረው ነበር።
የእስራኤል ጦር ወደ ሊባኖስ መግባት ላይከብደው ይችላል። ነገር ግን ተመልሶ ለመውጣት ወራት እንደሚፈጅበት ይገመታል።












