እስራኤል በኢራን ላይ ሌሊቱን ስለፈጸመችው ጥቃት እስካሁን የምናውቀው

የኢራን ዋና ከተማ ቅዳሜ ማለዳ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የኢራን ዋና ከተማ ቅዳሜ ማለዳ ላይ

እስራኤል ባለፉት ወራት በዙሪያዋ ያሉትን በኢራን የሚደገፉ ታጣቂ ቡድኖችን እና የኢራን አብዮታዊ ዘብ ወታደራዊ መኮንኖችን ዒላማ አድርጋ በፈጸመቻቸው ከባድ ጥቃቶች ምክንያት መካከለኛው ምሥራቅ ውጥረት ውስጥ ገብቷል።

እስራኤል ከሐማስ ጋር ባለፈው ዓመት ጋዛ ውስጥ የምታደርገው ጦርነት ተባብሶ እንደቀጠለ ሲሆን፣ ካለፈው ወር ጀምሮ ደግሞ ከሊባኖሱ ሄዝቦላህ ጋር በሌላ ግንባር ጦርነት ውስጥ ገብታለች።

ከእነዚህ ጦርነቶች ጎን ለጎን ደግሞ ከኢራን ጋር በርቀት በሚደረግ የሚሳዔል እና የጦር አውሮፕላን ጥቃቶች ውስጥ ገብታለች።

እስራኤል በዙሪያዋ የሚገኙትን ሐማስን፣ ሔዝቦላህን እና የየመን ሁቲዎችን በማስታጠቅ እና በመደገፍ የምትከሳት ኢራን ከሚገጥሟት ፈተናዎች ሁሉ ጀርባ አለች ብላ ታመናለች።

ለዚህም የታጣቂ ቡድኖቹን አመራሮች ብቻ ሳይሆን እነሱን የሚያማክሩትን የኢራን ከፍተኛ የጦር ጄኔራሎችን ሶሪያ እና ሊባኖስ ውስጥ ገድላለች።

ለዚህም ምላሽ ኢራን ድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶችን ሁለት ጊዜ በእስራኤል ላይ ፈጽማለች።

ባለፈው ዓመት ሚያዝያ እና ባለፈው መስከረም ወር ኢራን በእስራኤል ላይ ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ሚሳዔሎችን፣ ሮኬቶችን እና አጥፍቶ ጠፊ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን አዝንባባታለች።

ለዚህም ምላሽ እስራኤል በኢራን የተለያዩ ክፍሎች ላይ ጥቃቶችን ፈጽማለች።

በጋዛ እና በሊባኖስ ውስጥ ከሚገኙት የኢራን ወዳጅ ከሆኑት ሐማስ እና ሔዝቦላህ ጋር እስራኤል ጦርነት ውስጥ ከገባች በኋላ አርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ሌሊት በኢራን ላይ ጥቃት ስትፈጽም ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ይህ ጥቃት እንደሚፈጸም እስራኤል በይፋ ስታስታውቅ ቆይታ ከአሜሪካ የስለላ ተቋማት በኩል ይህንን የሚያመለክቱ መረጃዎች ባለፈው ሳምንት ሾልከው ከወጡ በኋላ መዘግየቱ ይነገራል።

አሜሪካ እስራኤል ራሷን የመከላከል መብት እንዳላት በመግለጽ በኢራን ላይ የአጸፋ ጥቃት እንድትፈጽም በተዘዋዋሪ ያበረታታች ሲሆን፣ ነገር ግን ቀጠናዊ ግጭትን ሊያስከትል ይችላል በሚል እስራኤል የኢራንን የኑክሌር ማዕከላትን እና የነዳጅ ማምረቻዎችን እንዳትመታ በፕሬዝዳንቷ በኩል አሳስባለች።

ቅዳሜ ማለዳ እስራኤል “የኢራንን ወታደራዊ ዒላማዎች በመለየት ውጤታማ” ጥቃት መፈጸሟን አስታውቃለች። ነገር ግን በጥቃቱ የተመቱት ዒላማዎች የትኞቹ እንደሆነ እና የደረሰው ጉዳት መጠን ግልጽ አልተደረገም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአሁኑ የእስራኤል ጥቃት የተፈጸመው መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ኢራን ወደ 200 የሚጠጉ ተወንጫፊ ሚሳዔሎችን በእስራኤል ላይ ከተኮሰች በኋላ ነው።

የኢራን ጥቃት የተፈጸመው እስራኤል ኢራን ውስጥ ፈጸመችው በተባለ ጥቃት የሐማስ መሪ ኢስማኤል ሃኒያን እንዲሁም ሊባኖስ ውስጥ በፈጸመችው የአየር ድብደባ የሄዝቦላህ መሪ ሐሳን ናስራላህን እና የኢራን አብዮታዊ ዘብ ቁዱስ የተባለው ኃይል አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል አባስ ኒልፎሩሻንን ከገደለች በኋላ ነው።

ከዚህ ጥቃት በኋላ እስራኤል ኢራንን ክፉኛ እንደምትበቀላት ብትገልጽም ምንም ዓይነት ዝርዝር ሳትሰጥ ቆይታለች።

ባለፈው ሳምንት ‘ሚድል ኢስ ስፔክቴተር’ የተባለ ከኢራን ጋር ግንኙነት ያለው የቴሌግራም ቻናል ከአሜሪካ የመረጃ ተቋማት ያገኘውን መረጃ መሠረት አድርጎ ይፋ እንዳደረገው እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ለመጸፈም የሚሳዔል እና የአየር ኃይሏን እያዘጋጀች መሆኑን የሳተላይት እና የስለላ ምንጮች ያሰባሰቡት መረጃ ግምገማ አመልክቶ ነበር።

አርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ሌሊት በእስራኤል ጥቃት የተፈጸመው በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን፣ ኹዜስታን እና ኢላም በተባሉ ግዛቶች ውስጥ በሚገኙ ወታደራዊ ተቋማት ላይ መሆኑን ኢራን አረጋግጣ ነገር ግን ሠራዊቷ ጥቃቱን ማክሸፉን እና ውስን ጉዳት መድረሱን አስታውቃለች።

እስራኤል ጥቃት የፈጸመችው በኢራን ላይ ብቻ አይደለም፤ ሶሪያ ውስጥም ሌሊቱን ፍንዳታዎች መሰማታቸው ተዘግቧል። ነገር ግን እስራኤል ለጥቃቶቹ ኃላፊነት አልወሰደችም።

የሶሪያ አየር መከላከያ ኃይሎች ሚሳዔሎችን ከአየር ላይ መትተው መጣላቸውን ሮይተርስ እና ኤኤፍፒ የዜና ወኪሎች የሶሪያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃንን ጠቅሰው ዘግበዋል።

አሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት ውስጥ ተሳትፎ እንደሌላት በመግለጽ፤ ነገር ግን ጥቃቱን “ራስን የመከላከል እርምጃ” ሲል የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ገልጾታል።

የእስራኤል የመከላከያ ኃይል ጥቃቱን ተከትሎ እንዳስታወቀው በጥቃቱ ዒላማ የሆኑት በኢራን የተለያዩ ግዛቶች ውስጥ የሚገኙ ሚሳዔል ማምረቻ ተቋማት፣ ከመሬት ወደ አየር የሚተኮሱ የሚሳዔል ማስወንጨፊያዎች እና የአየር ኃይል ይዞታዎች ናቸው ብሏል።

ጨምሮም ጥቃቱ የተፈጸመው እስራኤል መረጃዎች ካሏት በኢራን ውስጥ ከሚገኙ ዒላማዎች መካከል በተመረጡት ላይ ብቻ መሆኑን አመልክቶ “አስፈላጊ ከሆነም ተጨማሪ ዒላማዎችን በመለየት” ጥቃት እንደሚፈጽም አስታውቋል።

እስራኤል ተጨባጭ ስጋቶች ይደቅኑብኛል ያለቻቸውን ወታደራዊ ዒላማዎችን በሌሊት የፈጸመችው ሦስት ዙር ጥቃት ኢራን በቅርቡ ለፈጸመችባት ጥቃት “የተከፈለ ዋጋ ነው” ብላለች።

ስለጥቃቱ ቀደም ብለው እንዲያውቁ የተደረጉት አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም፣ ኢራን አሁን ለተፈጸመባት የእስራኤል ጥቃት አጸፋ እንዳትፈጽም ያሳሰቡ ሲሆን፣ ኢራን ግን በእስራኤል ለተፈጸመባት ጥቃት ራስን በመከላከል መርኅ ምላሽ እንደምትሰጥ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል አሳውቃለች።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ እስራኤል የአሁኑን ጥቃት ከመፈጸሟ አስቀድማ በሦስተኛ አገር በኩል ኢራን ዳግም በእስራኤል ላይ የአጸፋ እርምጃ እንዳትወስድስ አስጠንቅቃ እንደነበር የእስራኤል የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

እስራኤል ሌሊቱን በፈጸመቻቸው ተከታታይ የአየር ጥቃቶች ሁለት የኢራን አብዮታዊ ዘብ ወታደሮች መገደላቸውን የአገሪቱ ዜና አገልግሎት አስታውቋል።

ነገር ግን ዒላማ በተደረጉት ተቋማት ላይ ስለደረሰው ጉዳት እስካሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም የኢራን መንግሥት ግን የተሰነዘረው ጥቃት መክሸፉን እና ያደረሰው ጉዳትም ውስን መሆኑን ከመግለጽ ውጪ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።

በኢራን ላይ የተፈጸመውን የእስራኤል ጥቃት ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኳታር እና ግብፅ አውግዘውታል።

ከኢራን የተፈጸመበታን ጥቃት ባላት ሕጋዊ ራስን የመከላከል መብት ተጠቅማ ምላሽ እንደምትሰጥ የገለጸች ሲሆን፣ ኢራን በድጋሚ እስራኤል ላይ ጥቃት የምትሰነዝር ከሆነ ሌላ ዙር የምላሽ ከእስራኤል በኩል እንደሚጠብቃት ታወቀ ነው።

አራንም በግዛቷ ውስጥ አገራትን አቆራርጣ እስራኤል የፈጸመችባትን ጥቃት በዝምታ የምታልፈው አይሆንም። ከዚህ በፊት እንደታየው ከቀናት ወይም ከሳምንታት ዝግጅት በኋላ አጸፋ ልትመልስ ትችላልች።