እስራኤል ኢራንን ለማጥቃት የምታደርገውን ዝግጅት ያጋለጡት ምሥጢራዊ ሰነዶች ምን ይዘዋል?

ኢራን መስከረም 21 ወደ እስራኤል ከተኮሰቻቸው ሚሳዔሎች መካከል በደቡባዊ እስራኤል የወደቀ የሚሳዔል ስባሪ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ኢራን መስከረም 21 ወደ እስራኤል ከተኮሰቻቸው ሚሳዔሎች መካከል በደቡባዊ እስራኤል የወደቀ የሚሳዔል ስባሪ

የአሜሪካ መርማሪዎች ሁለት እጅግ ምሥጢራዊ የሆኑ የስለላ ሰነዶች በማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ላይ እንዴት ሾልከው ሊወጡ እንደቻሉ ለማወቅ እየሞከሩ ነው።

ባለፈው አርብ በቴሌግራም የመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያ ላይ የወጡት እነዚህ ምሥጢራዊ ሰነዶቹ እስራኤል ኢራንን ለማጥቃት እንዳቀደች አሜሪካ ያደረገችውን ግምገማ በዝርዝር የያዙ ናቸው።

ግምገማው የሳተላይት ምሥሎችን እና ሌሎች የስለላ መረጃዎችን በመተንተን የተዘጋጀ ሲሆን፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከተሠራጨ በኋላ መነጋገሪያ ሆኗል።

የዋይት ሐውስ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ሰኞ ዕለት እንደተናገሩት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሾልከው የወጡት ሰነዶች ጉዳይ “በጽኑ አሳስቧቸዋል” ብለዋል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ሰነዶቹ ሾልከው ሊወጡ የቻሉት በመረጃ መረብ ጠለፋ ወይስ ሆን ተብሎ እንዲሾልኩ ተደርገው እንደሆነ እስካሁን እንዳላወቁ ኪርቢ ተናግረዋል።

እስራኤል መስከረም 21/2017 ዓ.ም. ኢራን ለፈጸመችባት መጠነ ሰፊ የተወንጫፊ ሚሳዔሎች ጥቃት አጸፋ በመመለስ ክፉኛ ኢራንን እንደምትበቀል ባለፉት ሦስት ሳምንታት ስትዝት ቆይታለች።

ኢራን ጥቃቱን የፈጸመችው እስራኤል በመስከረም 17/2017 ዓ.ም. ሊባኖስ ውስጥ ባካሄደችው የአየር ጥቃት ለገደለቻቸው የወዳጇ የሄዝቦላህ መሪ ሐሳን ናስራላህ ግድያን ለመበቀል ነው ብላ ነበር።

ሾልከው የወጡት ሰነዶች ትክክለኛ ናቸው?

በርካታ ወታደራዊ ተንታኞች ሰነዶቹ በርዕስነት የተጠቀሙት ሐረግ ተአማኒነት ያለው እና ከዚህ በፊት ይፋ ከሆኑ ተመሳሳይ ምሥጢራዊ ሰነዶች ጋር ተመሳሳይነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የሰነዶቹ አናት ላይ “ብርቱ ምሥጢር” የሚል ሲሆን፣ በተጨማሪም “የውጭ መንግሥትን የሚመለከት የስለላ መረጃ” የሚል በምህጻረ ቃል የተቀመጠባቸው ናቸው።

ሰነዶቹ “አምስቱ ዓይኖች” በሚባሉት እና በመደበኛነት የመረጃ ልውውጥ በሚያደርጉት በአሜሪካ፣ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በካናዳ፣ በአውስትራሊያ እና በኒውዚላንድ የስለላ ተቋማት መካከል የተሠራጩ ሳይሆኑ አይቀሩም እየተባለ ነው።

በሰነዶቹ ውስጥ ያሉት መረጃዎች በተለያየ መንገድ በሳተላይት የተሰበሰቡ መሆናቸውን የሚያመለክቱ ምህፃረ ቃላት እና የምሥጢር ቃላት የተካተተባቸው መሆናቸው ስለትክክለኛነታቸው ማስረጃ ሆኗል።

ሰነዶቹ ምን ይነግሩናል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሁለቱ ሰነዶች በአንድ ላይ የአሜሪካ ብሔራዊ የጂኦስፓሻል-ኢንተለጀንስ ኤጀንሲ በጥቅምት 5 እና 6/2017 ዓ.ም. ያሰባሰባቸውን መረጃዎች ትንተና መሠረት በማድረግ እስራኤል ኢራን ውስጥ የሚገኙ ዒላማዎችን ለመምታት የምታደርገውን ዝግጅት በተመለከተ የቀረበውን የአሜሪካ ግምገማ ተካቶባቸዋል።

በሰነዶቹ ላይ በዋነኛነት የተጠቀሱት ጎልደን ሆራይዘን እና ሮክስ የተባሉ ሁለት ከአየር ወደ ምድር የሚወነጨፉ የባሊስቲክ ሚሳኤሎች ሥርዓቶች ናቸው።

ሮክስ የተባለው ሚሳዔል ራፋኤል በተባለው የእስራኤል ኩባንያ የተሠራ ሲሆን፣ ከመሬት በላይ እና በታች የሚገኙ የተለያዩ ዒላማዎችን ለመምታት የሚችል የረዥም ርቀት የሚሳዔል ሥርዓት ነው። ጎልደን ሆራይዘን የተባለው ደግሞ ወደ 2,000 ኪሎ ሜትሮች የሚሸፍን ሚሳዔል ሥርዓት ነው።

ይህም የእስራኤል አየር ኃይል ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ላይ በኢስፋሃን አቅራቢያ በሚገኝ የኢራን ራዳር ጣቢያ ላይ የፈጸመው ዓይነት፣ ነገር ግን እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው በአየር የሚወነጨፉ የሚሳዔል ጥቃቶችን የመፈጸም ተመሳሳይ ዕቅድ እንዳለው የሚያመለክት ነው።

እነዚህን መሳሪያዎች ከኢራን ድንበሮች ርቀው ከሚገኙ ስፍራዎች በማስወንጨፍ ከርቀት ዒላማዎችን በመምታት የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች እንደ ዮርዳኖስ ባሉ አንዳንድ የቀጣናው አገራት የአየር ክልል ውስጥ ማቋረጥ እንዳይኖርበት ያደርጋሉ ተብሏል።

ሾክልከው የወጡት ሰነዶች ጨምረውም እስራኤል የኑክሌር ጥቃትን ለመከላከል ያሏትን የጦር መሳሪያዎች ለመጠቀም የሚያስችል ዝግጅት እያደረገች ስለመሆኗ ምንም ዓይነት ምልክቶች አለመኖራቸውን ጠቁመዋል።

የቅርብ ወዳጇ እስራኤል የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንደታጠቀች አሜሪካ እስካሁን ድረስ በምንም ዓይነት መልኩ በይፋ ገልጻ አታውቅም፤ ይህም በእስራኤል ጥያቄ መሠረት የተደረገ ነው። ስለዚህም አሁን በዋሽንግተን በኩል በወጡት ሰነዶች ላይ ስለኑክሌር ጦር መሳሪያ መጠቀሱ አሳፋሪ ሆኗል።

ካርታ

ሰነዶቹ ምን የደበቁት ነገር አለ?

እነዚህ ሰነዶች እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት እያደረገች ለመሆኗ ውጪ፤ ጥቃቱ መቼ ሊፈጸም እንደሚችል እና በኢራን ውስጥ ዒላማ ሊሆኑ ስለሚችሉት ስፍራዎች ምንም ያሉት ነገር የለም።

ነገር ግን እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ በአገሪቱ የኑክሌር ምርምር ተቋማት ላይም ሆነ የነዳጅ ዘይት ማምረቻ ማዕከላት ላይ መሆን እንደሌለበት አሜሪካ በገልጽ ስታስጠነቅቅ ቆይታለች።

በዚህም የእስራኤል ጥቃት ሊሆኑ የሚችሉት ዒላማዎች የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ እና የእሱ አጋር የሆነው ባሲጅ የተባለው የሚሊሻ ቡድን ይዞታዎች ናቸው።

እነዚህ ሁለቱ ወታደራዊ ተቋማት የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የጀርባ አጥንት ሲሆኑ፣ የአገሪቱን ወታደራዊ ኃይል በውጭ አገራት በማሰማራት እንዲሁም በአገር ውስጥ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን በማፈን ይታወቃሉ።

የአጸፋ ጥቃቱን በተመለከተም ብዙዎች እስራኤል እንደዛተችው የበቀል እርምጃዋን በአሁኑ ወቅት ልትፈጽም ትችላለች ብለው ነበር።

ባለፈው ሚያዝያ ኢራን ሶሪያ ውስጥ ለተገደሉባት የአብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ አዛዥ በቀል በእስራኤል ላይ 300 የሚሆኑ የድሮኖች እና የሚሳዔሎች ጥቃቶችን የፈጸመችው ከ12 ቀናት በኋላ ነበር።

አሁን የእስራኤል የአጸፋ ጥቃት የዘገየው ምናልባትም በከፊል ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ በሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በፊት ግጭቱ እንዳይባባስ አሜሪካ ባላት ስጋት ምክንያት ሊሆን ይችላል።

ሰነዶቹ ሆን ተብሎ እንዲሾልኩ ተደርገው ነው?

ምናልባትም እስራኤል በኢራን ላይ የቀደችውን ጥቃት ለማደናቀፍ የሚፈልግ አንድ ሰው ሆን ብሎ ሰነዶቹን አሹልኳቸው ሊሆን ይችላል።

ኢራን ግዙፍ እና የተራቀቀ የበይነ መረብ ወታደራዊ ዘርፍ አቅም ስላላት ሰነዶቹን የመመዝበር ጥቃት ፈጽማ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ የሚኖር ከሆነ ምርመራ እየተደረገ ነው።

እነዚህ ሾልከው የወጡት ምሥጢራዊ ሰነዶች እንደታሰበው ሃቀኛ ከሆኑ፣ ምንም እንኳን በአሜሪካ እና በእስራኤል መካከል ያለው ጠንካራ ወታደራዊ ግንኙነት እንዳለ ቢሆንም፣ በአሜሪካ በኩል ዝርዝር ማብራሪያ እስካልተሰጠ ድረስ ዋሽንግተን አሁንም በአጋሯ ላይ ስለላ እያካሄደች እንደሆነ ያመለክታል።

ሰነዶቹ የእስራኤል አየር ኃይል በኢራን ላይ አንዳች ዓይነት የረዥም ርቀት የበቀል ጥቃት ለመፈጸም ያዘጋጃቸው ዕቅዶች በጥሩ ሁኔታ እየሄዱ መሆናቸውን እና ይህንንም ተከትሎ የሚጠበቀውን የኢራን የአጸፋ ምላሽን ለማስቀረት ያለውን ዝግጅት በዝርዝር ይዘዋል።

ነገር ግን እስራኤል በኢራን ላይ ያቀደችውን ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ በቀውስ ውስጥ ያለውን መካከለኛው ምሥራቅ ወደ ከባድ ውጥረት የሚያስገባው ይሆናል።

‘ሚድል ኢስት ስፔክቴተር’ በተባለው ለኢራን ቅርብ ነው በተባለ የቴሌግራም ቻናል ላይ ይፋ የሆነው የአሜሪካ የስለላ መረጃ፣ የእስራኤል ወታደራዊ ዝግጅትን በተመለከተ አሜሪካ ያሰባሰበችው በመሆኑ በእስራኤል ባለሥልጣናት በቀላሉ የሚታይ አይሆንም።

እንዲሁም ይህ ክስተት በአሜሪካ በኩል ባለው የምሥጢራዊ መረጃ አጠባበቅ ደኅነንት ላይ ጥያቄን ያስነሳ ሲሆን፣ ሰነዶቹ ለኢራን ቅርብ በሆነው የማኅበራዊ ትስሰር ገጽ ይፋ መሆኑ ደግሞ ሌላ ውዝግብን ሊያስከትል ይችላል።