የዛምቢያው ፕሬዝዳንት ለተቀናቃኛቸው ወስነው የነበሩ ሦስት ዳኞችን ከሥራ አባረሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዛምቢያው ፕሬዝዳንት ሃኪዬንዳ ሂቺሌማ በዳኝነት ሥራቸው ላይ ተገቢ ያልሆነ ተግባር ፈጽመዋል ያሏቸውን የአገሪቱን ሦስት ከፍተኛ ዳኞች ከሥራ አባረሩ።
በፕሬዝዳንቱ የተሰናበቱት የአገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ዳኞች ከስምንት ዓመት በፊት በተካሄደው እና የአሁኑ ፕሬዝዳንት በተሸነፉበት ምርጫ ላይ ያቀረቡትን ቅሬታ ውድቅ አድርገውት ነበር።
በተጨማሪም ዳኞቹ አሸናፊው ፕሬዝዳንት ኤድጋር ሉንጉ ለሁለት የምርጫ ዘመን በሥልጣን ላይ ከቆዩ በኋላ ለሦስተኛ ዙር እንዲወዳደሩ በተፈቀደበት አወዛጋቢ ውሳኔ ውስጥም ተሳትፈው ነበር።
ዳኞቹ በፕሬዝዳንቱ ከመባረራቸው በፊት እገዳ ተጥሎባቸው የነበረ ሲሆን፣ ይኸው ዕገዳ እንዲነሳላቸው ለዳኞች ጉባኤ ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ መሆኑን ተከትሎ ነው።
ዳኞቹ ከሥራ የተባረሩት የአገሪቱ የፍትህ ቅሬታዎችን የሚመለከተው ኮሚሽን “በአስቸኳይ እንዲሰናበቱ” ባቀረበው ሃሳብ መሠረት መሆኑን ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ አመልክቷል።
መግለጫው ጨምሮም “በዛምቢያ ሕገ መንግሥት መሠረት ዳኞችን የማሰናበት ሥልጣን ለፕሬዝዳንቱ የተሰጠ በመሆኑ” ውሳኔው መተላለፉን ገልጿል።
በፕሬዝዳንቱ ከዳኝነት ሥራቸው የተሰናበቱት ሦስቱ የዛምቢያ ከፍተኛ ዳኞች በውሳኔው ላይ የሰጡት አስተያየት የለም።
የፍትህ ቅሬታዎችን የሚመለከተው ኮሚሽን ሦስቱ ዳኞች በተሰጣቸው ኃላፊነት አማካኝነት ተገቢ ያልሆኑ ከባድ ጥፋቶችን ፈጽመዋል በሚል በአንድ ግለሰብ የቀረበባቸውን ክስ ሲመርምር ቆይቷል።
ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ኮሚሽኑ ዳኞቹ ከስምንት ዓመት በፊት በተካሄደው ምርጫ ላይ ያሳለፉት ውሳኔ ተገቢ አልበነረም በሚል በአንድ ጠበቃ የቀረበለትን ክስ ውድቅ አድርጎት ነበረ።
ከሁለት ዓመት በኋላ ምርጫ ለማስተናገድ እየተዘጋጀች ባለችው ዛምቢያ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ሂቺሌማ እና ቀድሞው ፕሬዝዳንት ሉንጉ እንደሚፎካከሩ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በዚህም የተነሳ በአገሪቱ ፖለቲካዊ ውጥረት እየጨመረ መሆኑ ይነገራል።
የፕሬዝዳንቱ ውሳኔን በተመለከተ በአገሪቱ ዜጎች መካከል የተደበላለቀ አስተያየት እየተሰጠ ነው።
ውሳኔው ሕጋዊ ነው ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ እና ደጋፊዎቻቸው ለእራሳቸው በሚጠቅም መልኩ እርምጃ ወስደዋል ሲሉ የአገሪቱን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ዜጎች ተችተዋል።
ላውራ ሚቲ የተባሉ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ተንታኝ እንዳሉት “በ2016 (እአአ) የተካሄደውን ምርጫ በተመለከተ ዳኞቹ ተገቢ ያልሆነ ውሳኔ አሳልፈዋል። ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ የበቀል የሚመስል ውሳኔ መስጠታቸው በጣሙን አሳሳቢ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነገር ግን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጠበቃ የሆኑት ማኬቢ ዙሉ እርምጃውን “ሕገወጥ” በማለት “ሥራ አስፈጻሚው በፍትህ አካሉ ነጻነት ላይ ጣልቃ ለመግባት ያለመ ነው” ሲሉ ከሰው “የትኛውም ዳኛ ሕግ የመተርጎም ሥራውን በማከናወኑ ሊቀጣ አይገባም” ብለዋል።
በዛምቢያ ሕገ መንግሥት መሠረት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትን ጨምሮ ሁሉም ዳኞች በአገሪቱ የሕግ አገልግሎት ኮሚሽን ተመርጠው በፕሬዝዳንቱ ሚሾሙ ሲሆን፣ በአገሪቱ ብሔራዊ ምክር ቤትም ተቀባይነት ማግኘት አለባቸው።












