የማልኮም ኤክስ ቤተሰብ ኤፍቢአይ፣ ሲአይኤንና የኒው ዮርክ ፖሊስን ሊከሱ ነው

ማልኮም ኤክስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የጥቁሮች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ማልኮም ኤክስ ሴት ልጅ የኒው ዮርክ ፖሊስና ሌሎች የደኅንነት ድርጅቶችን ልትከስ እንደሆነ ገለጠች።

ኢልያሳህ ሻባዝ እንደምትለው የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት አባቷን ለግመደል “ያሴሩበትን” ማስረጃ ደብቀዋል።

ከ58 ዓመታት በፊት አባቷ በአሰቃቂ ሁኔታ በጥይት ተመትቶ በወደቀበት ሥፍራ ላይ ቆማ ነው ይህን ዕቅዷን ለጋዜጠኞች የገለጠችው።

ሲአይኤና ኤፍቢአይም በክስ እንደተካተቱበት ከቤተሰቡ ጠበቃ መረዳት ተችሏል።

የ60 ዓመት ሻባዝ አባቷ በጥይት ተደብድቦ ሲሞት የሁለት ዓመት ሕፃን ሆና ተመልክታለች።

ማልኮም ኤክስ፤ ኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ ሃርለም በተሰኘው ሥፍራ ንግግር ሊያደርግ እየተሰናዳ ሳለ ነበር ሶስት የታጠቁ ሰዎች 21 ጊዜ በጥይት የመቱት።

“ለዓመታት ቤተሰባችን የአባታችንን ግድያ በተመለከተ እውነታው እንዲታወቅ ሲታገል ቆይቷል” ስትል አባቷ ከተገደለበት አሁን ግን መታሰቢያ ሥፍራ ከተቀየረበት ቦታ ቆማ ተናግራለች።

ጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የቤተሰቡ ጠበቃ ቤንጃሚን ክራምፕ ጉልበት ያላቸው የአሜሪካ የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች ማልኮም ኤክስን ለመግደል አሲረዋል ሲሉ ከሰዋል።

ጠበቃው ጄ ኤደርጋድ ሁቨር የተሰኙት የቀድሞው የኤፍቢአይ ዳይሬክተርን ስም ደጋግመው አንስተዋል።

ጠበቃ ክራምፕ እንደሚሉት ማልኮም ኤክስ ያለጥፋቱ በመገደሉ ለደረሰው ጥፋት 100 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ቤተሰቡ ይጠይቃል።

“ይህ ቃታውን የሳበው ሰው ጉዳይ ብቻ አይደለም። ቃታውን የሳበው ሰው ይህ ድርጊት እንዲፈፅም ያሴሩትንም ይጨምራል።”

የኒው ዮርክ ከተማ ፖሊስ ጉዳይ በሕግ ስለተያዘ አስተያየት መስጠት አልችልም ሲል ለቢቢሲ ገልጧል። ኤፍቢአይ እና ሲአይኤ ደግሞ እስካሁን ምላሽ አልሰጡም።

ማልኮም ኤክስ ጥቁር አሜሪካዊያን ከነጮች ተለይተው መኖር አለባቸው ብሎ የሚያምነው የኔሽን ኦፍ ኢስላም ቃል አቀባይ ነበር።

ነገር ግን ከኔሽን ኦፍ ኢስላም መሥራች ኤላይጃህ ሞሐመድ ጋር ባለመስማማቱ ለቆ መውጣቱ ይታወሳል።

ማልኮም ኤክስ የተገደለው በ39 ዓመቱ ነው።

የኔሽን ኦፍ ኢስላም አባል የነበረ አንድ ግለሰብ ማልኮም ኤክስን መግደሉን አምኗል።

ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ሁለት በማልኮም ኤክስ ግድያ ተፈርዶባቸው የነበሩ ግለሰቦች የፍትሕ መጓደል ተፈፅሟል ተብሎ በነፃ ተለቀዋል።

ሁለቱ ግለሰቦች የኒው ዮርክ ከተማን ከሰው አንደኛው ግለሰብ 26 ሚሊዮን ሌላኛው ደግሞ 10 ሚሊዮን ዶላር መርታታቸው አይዘነጋም።