በአዲስ አበባ "የትግራይ ተወላጆች" እስር እየተፈጸመባቸው መሆኑን እማኞች እና የመብት ተሟጋች ተቋም ገለጹ

ፒክ አፕ መኪና ላይ ቁጭ ያሉ ፖሊሶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአዲስ አበባ ከተማ የትግራይ ተወላጆች "ማንነትን መሠረት ያደረገ እስር" እየተፈጸመባቸው እንዲሁም "ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለቀናት እየታሰሩ" መሆኑን ከእስር የተለቀቁ ነዋሪዎች እና የታሳሪ ቤተሰብ ተናገሩ።

ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች የተሰኘው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም በበኩሉ በአዲስ አበባ "ቢያንስ በስድስት ክፍለ ከተማዎች" ውስጥ የትግራይ ተወላጆች "የዘፈቀደ እስር" እንደተፈጸመባቸው ማረጋገጡን አስታውቋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የተለቀቁ ነዋሪዎች፣ የቤተሰብ አባል የታሰረባቸው ግለሰብ እንዲሁም ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ይህ ዓይነቱ እስር መፈጸም የጀመረው "ከሁለት ሳምንት ወዲህ" እንደሆነ ገልጸዋል።

የቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ምክትል ዳይሬክተር አቶ መብርሂ ብርሃነ፤ "ይህ እስር [መፈጸም] ከጀመረ ሁለት ሳምንት ይሆነዋል። አፈሳው በጣም በርትቶ ከቀጠለ ግን አስር ቀን ይሆነዋል" ሲሉ የሚመሩት ተቋም ባደረገው ክትትል የደረሰበትን አስረድተዋል።

የቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ይህንን እስር አስመልክቶ ትናንት ሰኞ ሰኔ 23/2017 ዓ.ም. ባወጣው አጭር ሪፖርት፤ ከትግራይ ክልል የመጡ እና በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች "በስማቸው፣ በአነጋገር ሁኔታቸው፣ በቋንቋቸው እየተለዩ መሆኑን ታስረው ከተፈቱ ምስክሮች አረጋግጠናል" ብሏል።

ምክትል ዳይሬክተሩ እንደሚያስረዱት ተቋሙ ይህንን ሪፖርት ለማዘጋጀት "በየካ፣ በለሚኩራ፣ በቦሌ፣ በልደታ፣ በአዲስ ከተማ እና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች" ክትትል አድርጓል።

ነዋሪዎቹ በመጀመሪያ "በፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ ከታሰሩ በኋላ ወደ ፖሊስ መመሪያዎች እንደሚዘዋወሩ" ተቋሙ ባደረገው ክትትል እንደ ደረሰበት ተናግረዋል።

አቶ መብርሂ እስር እንደተፈጸመባቸው ከዘረዘሯቸው ቦታው መካከል በየካ ክፍለ ከተማ ፈረንሳይ፣ ኮተቤ፣ 02 እና ሾላ አካባቢዎች እንዲሁም በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ሲኤምሲ አካባቢ ይገኙበታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በቦሌ ክፍለ ከተማ 22፣ አዲሱ አስፓልት እና አደይ አበባ አካባቢዎች እንዲሁም በልደታ ክፍለ ከተማ አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ከተጠቀሱት መካከል ናቸው።

ምክትል ዳይሬክተሩ፤ "ይህ እስር በተለይ ትኩረት እያደረገ ያለው ወጣቶች ላይ ነው። ከመንገድ ላይ፣ ከመዝናኛ ቦታዎች ሊሆን ይችላል ተወስደው ይታጎራሉ፤ ፍርድ ቤት አይቀርቡም፤ ጠያቂ የላቸውም፤ ለምን እንደታሰሩ እንኳን የሚነግራቸው ሰው የለም" ብለዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት ታስረው የተለቀቁ ነዋሪዎች እና አንድ የቤተሰብ አባል የታሰረባቸው ግለሰብም ተመሳሳይ ሁኔታዎችን ጠቅሰዋል።

ቢቢሲ ያነጋራቸው ነዋሪዎች የታሰሩት ወይም የቤተሰብ አባላቸው የታሰረው መንገድ ላይ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ነው።

ሰኔ 14/2017 ዓ.ም. ተይዞ ከአንድ ሳምንት እስር በኋላ የተለቀቀ አንድ ነዋሪ፤ በቁጥጥር ስር የዋለው ቀን ስምንት ሰዓት አካባቢ መንገድ ላይ በነበረበት ሰዓት ፖሊሶች አስቆመውት መታወቂያ ከጠየቁት በኋላ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግሯል።

"ስሜን እንዳዩት፤ የአባቴ ስም የትግራይ ስለሆነ 'ወደዛ ተለይ' አሉኝ። [...] ትንሽ ቆይቶ ወሰን አካባቢ ወዳለ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱን። መንገድ ላይ እየሄድን [የተያዝነው ሰዎች] አራት ደረስን" ሲሉ ሁኔታውን አስታውሷል። ወደ ፖሊስ ጣቢያው ሲደርስ "ብዙ የትግራይ ተወላጆች" ታስረው ማግኘቱንም ገልጿል።

"ስንገባ ወደ 40 የሚሆን ሰው ነበር። ያደረ፣ የዛኔ ታፍሶ የመጣ፣ በኋላም የታፈሱ አሉ። ከሥራ ቦታ ያመጧቸው ነበሩ። መወልወያ የሚያዞሩ፣ ከቤቱ ያመጡት አንድ [ልብስ] ሰፊ አስታውሳለሁ። ከሲኖትራክ መኪና አውርደውም ያመጧቸውም አሉ" ብሏል።

በማግስቱ ሾላ አካባቢ ወደሚገኘው የየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ መወሰዳቸውን የሚናገረው ነዋሪው፤ በፖሊስ መምሪያው ውስጥ ከሌሎች አካባቢዎችም ታስረው የመጡ "የትግራይ ተወላጆችን" ጋር መቀላቀሉን አስረድቷል።

ታስሮ ከቆየባቸው በአንዱ ቀን "ሲቪል የለበሰ ኃላፊ" መጥቶ "የትግራይ ተወላጆች" እንዲሁም ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ ታሳሪዎች ተለይተው እንዲቆሙ ማድረጉን የሚገልጸው ነዋሪው፤ በዚህ ሰዓት "ከአንድ መቶ በላይ የትግራይ ተወላጆች" አንድ ላይ ተሰብስበው እንደነበር ምልከታውን አጋርቷል።

በዚሁ ፖሊስ መምሪያ ውስጥ ወንድሙ የታሰረበት ሌላ ነዋሪም በተመሳሳይ ታሳሪውን ሊጠይቅ በሄደበት ሰዓት "ትግረኛ ቋንቋ የሚናገሩ በርካታ ጠያቂዎችን" መመልከቱን ተናግሯል።

ባለፉት ቀናት ሁለት ጊዜ ተይዞ እንደነበር የሚናገር ሌላ ነዋሪ ደግሞ፤ የፖሊስ አባላት የእርሱን እና የጓደኛውን መታወቂያ ከተመለከቱ እንዲሁም ስልክ ከበረበሩ በኋላ "እንግልት" እንደተፈጸመባቸው ገልጿል።

"[ምሽት] ሦስት ሰዓት የያዙን እስከ ስምንት ሰዓት ቆየን። ሌላም ፖሊስ ይመጣል፣ ይመካከራሉ፣ 'አስር ሺህ ብር አምጡ' ይሉናል" ሲል የደረሰበትን አስረድቷል።

ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰዱ በኋላ ሌሊት አስር ሰዓት አካባቢ እንደተለቀቁ አስረድቷል። በትናንትናው [ሰኞ] ዕለትም መንገድ ላይ እየሄደ ሳለ በድጋሚ በፖሊሶች ተይዞ እንደነበር የሚገልጸው ነዋሪው፤ የተያዘበት ቦታ ተመሳሳይ ስለነበር "አስረድቶ" መለቀቁን ጠቅሷል።

ገርጂ እና ጎሮ በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች ከታሰሩ ሁለት ሳምንት የሆናቸው ቢያንስ ሦስት "የትግራይ ተወላጅ" ጓደኞች እንዳሉትም አክሏል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ከእስር የተለቀቁ ነዋሪዎች እና የታሳሪ ቤተሰብ አባል ታሳሪዎች ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ እና በምን ጉዳይ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር እንደዋሉ አለመገለጹን ይናገራሉ።

ከሁለት ሳምንት በፊት ወንድሙ የታሰረበት ግለሰብ፤ "ፍርድ ቤት አልቀረበም። ገብተህ ለመጠየቅም የሚያናግርህም የለም" ሲል ሁኔታውን ገልጿል።

ከአንድ ሳምንት እስር በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ የተለቀቀ ሌላ ነዋሪ በበኩሉ፤ በፖሊስ አባላት እና መርማሪዎች ሲሰጣቸው የነበረው ምክንያት የታሰሩት "በወቅታዊ ሁኔታ" እና "ከላይ በመጣ ትዕዛዝ" እንደሆነ የሚገልጽ እንደሆነ አመልክቷል።

የቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ምክትል ዳይሬክተሩ አቶ መብርሂም በተመሳሳይ ተቋማቸው ባደረገው ክትትል የታሰሩ "የትግራይ ተወላጆች ወደ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ" እንዳረጋገጠ ተናግረዋል።

"'ጥርጣሬ ሳይኖር ሰው መታሰር የለበትም' የሚል እምነት አለ። ነገር ግን ጥርጣሬ ሳይኖር እንኳ ቢታሰር መቅረብ ያለበት ወደ ፍርድ ቤት ነው" ብለዋል።

በከተማዋ እየተፈጸመ ነው የተባለው እስር "ትኩረት ማግኘቱን እና በማኅበራዊ ሚዲያ መሠራጨቱን ተከትሎ"፤ ከቅዳሜ ወዲህ ባሉት ቀናት የተፈቱ ነዋሪዎች እንዳሉ ምክትል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ቢቢሲ ጉዳዩን በተመለከተ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የአዲስ አበባ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ፤ ስለጉዳዩ ገለጻ ከተደረገላቸው በኋላ ቀጠሮ ቢሰጡም ቢቢሲ ኃላፊውን በድጋሚ ማግኘት አልቻለም።