የዛላንበሳ ድንበር ዳግም መከፈት እና የፈጠረው ስሜት

ሁለት ሴቶች ተቃቅፈው ሲሳሳሙ

የፎቶው ባለመብት, Girmay Gebru / BBC

የምስሉ መግለጫ, ቤተሰቦች እና ጓደኛሞች ከአምስት ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ሲገናኙ

እሁድ ዕለት የዛላንበሳ ድንበር ከአምስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከፍቶ የአካባቢው ማኅበረሰቦቹ ተገናኝተዋል።

በ2013 ዓ.ም. በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ክልል መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ እና እርሱን ተከትሎ በነበረው ፖለቲካዊ ውጥረት የዛላንበሳ ድንበር ተዘግቶ ነበር።

እሁድ ዕለት በሁለቱ ማኅበረሰቦች አማካኝነት ድንበሩ ተከፍቶ ነዋሪዎች ሲገናኙ ለሰላም እና ዕርቅ ተምሳሌታዊ ጊዜ ነበር።

በኢትዮጵያ ዛላንበሳ ከተማ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ባሉበት ቤተሰቦች እና ወዳጅ ዘመዶች ዳግም ተገናኝተዋል።

የድንበሩን የተወሰነ ክፍል እንደገና ለመክፈት እርምጃ የተወሰደው ከሁለቱም መንግሥታት ይፋዊ ድጋፍ ሳይደረግ በአካባቢው የማኅበራዊ አንቂዎች እና የማኅበረሰብ ተወካዮች አነሳሽነት መሆኑ ተሰምቷል።

ነገር ግን ከድንበሩ መከፈት ጀርባ እንዳሉ የተገለፁት አካላት የትግራይ ክልል መንግሥት እና የኤርትራ ባለሥልጣናት ይኹንታን ማግኘታቸውን አመልክተዋል።

ድንበሩ ተከፍቶ ዳግም ነዋሪዎች ሲገናኙ ብዙዎችን በስሜት የሞላ ሲሆን ረጅም ጊዜ የቆየ ሲሉም ገልፀውታል።

ለአምስት ዓመታት በዓለም አቀፍ ድንበሩ ምክንያት የተለያዩ ቤተሰቦች እና ወዳጆች በወታደሮች የሚጠበቀውን አካባቢ አቋርጠው መገናኘት አልቻሉም ነበር።

በርካታ የዛላንበሳ እና የአካባቢዋ ነዋሪዎች የሁለት ዓመት ደም አፋሳሽ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. በፕሪቶርያ ሰምምነት አማካኝነት ቢጠናቀቅም ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳት አስተናግደዋል።

በርካቶች ቤት ንብረታቸውን ጥለው የሸሹ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከዛላንበሳ 30 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው አዲግራት ከ55 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ይኖራሉ።

ምንም እንኳ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ካበቃ ዓመታት ያለፉት ቢሆነም ድንበሩ ግን በሁለቱ አገራት መንግሥታት መካከል በተፈጠረው ቅራኔ ምክንያት ዝግ ሆኖ ቆይቷል።

እሁድ ዕለት በድንበሩ መከፈት የተገናኙት ሰዎች "ያለፈው ይበቃል፤ በሰላም ጠረጴዛ ዙርያ ቁጭ እንበል እና የተሻለ መፃዒ ጊዜ አንገንባ" ሲሉ ተሰምተዋል።

የትግራይ ክልልን እና የኤርትራን ባንዲራ የሚያውለበልቡ ነዋሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Girmay Gebru / BBC

በዛላንበሳ አካባቢ በሁለቱ አገራት ሕዝቦች መካከል የንግድ ልውውጥም ዳግም ተጀምሯል።

አንዲት የትግራይ እናት "እንደ ሕዝብ፣ መብላት መነገድ እንፈልጋለን። እንዲሁም እንደ ከዚህ ቀደሙ በማኅበራዊ ሕይወት መገናኘት እንፈልጋለን። የእነርሱ ቤተሰቦች እዚህ አሉ፤ የእኛ ቤተሰቦች እዚያ አሉ። የምንፈልገው ሰላም ነው" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ነገር ግን በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት ለመጠገን በርካታ ሥራዎች መስራት ይጠይቃል።

የዛላንበሳ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፤ መብራት፣ ስልከ እንዲሁም የባንክ አገልግሎት ተቋርጧል።

አብዛኛው መሠረተ ልማት በኢትዮጵያ መንግሥት የተዘረጋ ሲሆን ጥገና ለማካሄድም ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ እንደሚጠይቅ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

የውሃ፣ ጤና እንዲሁም የትምህርት ተቋማትም ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የአካባቢው ማኅበረሰብ እና ለጋሾች ቀስ በቀስ እየገነቧቸው ይገኛሉ።

ኤርትራ ነጻነቷን ካገኘች ሦስት አስር ዓመታት ያለፈ ሲሆን የሁለቱ አገራት ግንኙነት ውጥረት የሞላበት ድንበሩም ለበርካታ ዓመታት ተዘግቶ የቆየ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን ሲመጡ ከፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ታሪካዊ የሰላም ስምምነት ከፈረሙ በኋላ ለአጭር ጊዜም ቢሆን የሁለቱ አገራት ድንበር ተከፍቶ ነበር።

ስምምነቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኖቤል ሰላም ሽልማት እንዲያገኙ አድርጓል።

ይህ እርምጃ መጀመርያ ላይ ተስፋን የፈነጠቀ ቢሆንም የትግራይ ጦርነት መቀስቀስ ግን ነገሮችን ሙሉ በሙሉ ቀይሯል።

የኦርቶዶክስ እና የሙስሊም ሃይማኖት አባቶች

የፎቶው ባለመብት, Girmay Gebru / BBC

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለመገኘት ከኤርትራ ሰንዓፌ መምጣቱን የተናገረው ነብያት ወልደገርጊስ "ዛሬ የጀመርነው ሰላምና ዕርቅ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እርግጠኛ ነኝ" ብሏል።

ዛላንበሳን ጥለው ለአምስት ዓመታት በአዲግራት የስደተኞች መጠለያ የሚኖሩት ወ/ሮ አምለሰት "ዛሬ የተዘጋውን ቤቴን ለማየት መጣሁ። ከአሁን በኋላ ልጆቼን ይዤ በቤቴ መኖር እቀጥላለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በአንድ ወቅት በጋራ ይኖሩ የነበሩ ቤተሰቦች በጦርነቱ ምክንያት እንዴት እንደተለያዩ ያስታውሳሉ።

የሁለቱም ማኅበረሰቦች ተወካዮች "ሰላም እና እርቅ ተጀምሯል" ሲሉ ያወጁ ሲሆን፣ ነዋሪዎች ወደ ቤታቸው ተመልሰው ሕይወታቸውን ዳግም መገንባት እንዲጀምሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ይኹን እንጂ አሁንም ተግዳሮቶች አሉ።

የተዘረፉ ንብረቶች፣ የወደሙ ቤቶች እና የአገልግሎቶች አለመኖር በሺዎች ለሚቆጠሩ የተፈናቀሉ ቤተሰቦች ሕይወትን ዳግም መልሶ ለማቋቋም ቀላል አያደርግም።

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ይህ በአካባቢው ማኅበረሰቦች መካከል የተደረሰ ስምምነት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግሥታት መካከል፣ በአዲስ አበባ እና በአሥመራ እንዴት እንደሚተረጎም ግልጽ አይደለም።