አርሴናል ከኒውካስል፣ ቼልሲ ከዩናይትድ. . . ፕሪሚየር ሊግ እና የኤፍኤ ካፕ የዋንጫ ጨዋታ ግምቶች

144ኛው የኤፍኤ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ እሑድ በክሪስታል ፓላስ እና በማንቸስተር ሲቲ መካከል ይከናወናል።

የፕሪሚየር ሊጉ ቀጣይ ጨዋታዎችም አርብ፣ እሑድ እና ሰኞ እንዲከናወኑ መርሃ ግብር ተይዞላቸዋል።

የሊጉ ሻምፒዮን እና ወራጅ ቡድኖች ቀደም ብለው ቢታወቁም በሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ የሚደረገው ትንቅንቅ አጓጊ ሆኗል።

የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን እነዚህን ጨዋታዎች እንደሚከተለው ገምቷል።

የኤፍኤ ካፕ የዋንጫ ጨዋታ

ቅዳሜ

ክሪስታል ፓላስ ከ ማንቸስተር ሲቲ

ማንቸስተር ሲቲ ዘንድሮ ውጤታማ ባይሆንም ለኤፍኤ ካፕ ፍጻሜ ከመድረሱም በላይ በሻምፒዮንስ ሊግ የሚያሳተፈው ዕድል በእጁ ላይ ይገኛል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኢትሃድ ላይ ሁለቱ ቡድኖች ተገናኝተው ፓላስ ሲቲን ቢፈትንም 5 ለ 2 ተሸንፏል።

ውጤቱ ጨዋታውን ባይገልጸው ለፍጻሜው ጨዋታ ፓላሶችን የሚያነቃቃ ይሆናል።

ግምት፡ 3 – 2

የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ግምቶች

አርብ

አስቶን ቪላ ከ ቶተንሃም

በሚቀጥለው ሳምንት የሚከናወነው የዩሮፓ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ለቶተንሃም እና ማንቸስተር ዩናይትድ የዓለም ዋንጫን ያህል ነው።

አንጅ ፖስትኮግሉ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን ማሳረፍ የሚፈልጉ ቢሆንም ለፍጻሜው ጨዋታ ግን ተጫዋቾቻቸው በሚፈለገው አቋም ላይ ሆነው እንዳይቀርቡ ሊያደርግ የሚችልበት ዕድልም አለ።

ችግር የሚሆነው ተጫዋቾቹ ከተጎዱ የአሰልጣኙ ጫና ይበረታል።

በዚህ ምክንያት ቶተንሃም ጨዋታውን አያሸንፍም።

ቪላ ትኩረቱን በሌላ ጨዋታ ላይ ካደረገ ቡድን መጫወቱ ትልቅ ዕድል ፈጥሮለታል።

ግምት፡ 2 – 0

ቼልሲ ከ ማንቸስተር ዩናይትድ

ቼልሲ አጥቂው ኒኮላስ ጃክሰን በቅጣት ስለማይሰለፍ የፊት መስመሩን ማን እንደሚመራ እረግጠኛ አይደለንም።

ማንቸስተር ዩናይትድ በሊጉ ውጤት ማግኘት ቢከብደውም ከዩሮፓ ሊግ ጨዋታዎች በፊት ተጫዋቾችን በተደጋጋሚ ሲቀይር ታይቷል።

ቡድኑ በሊጉ የሚያስመዘግበው ውጤት በዚህ ጨዋታም የሚቀየር አይመስልም።

ግምት፡ 1 – 0

እሑድ

ኤቨርተን ከ ሳውዝሃምፕተን

ሳውዝሃምፐተን ባለፈው ሳምንት ከማንቸስተር ሲቲ ጋር አቻ ለመለያየት ችሏል።

ቡድኑ አንድ ነጥብ በማግኘቱ ተጫዋቾቹ ደስታቸውን መግለጻቸው አስገራሚ ነበር።

ኤቨርተን ባለፈው ሳምንት በመጀመሪያው አጋማሽ ቢበለጥም በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽሎ 3 ለ 1 ማሸነፍ ችሏል።

ቤቶ ጎል አስቆጥሮ ኤቨርተን ሦስት ነጥብ የሚያሳካበት ጨዋታ ይሆናል።

ግምት፡ 2 – 0

ዌስት ሃም ከ ኖቲንግሃም ፎረስት

ኖቲንግሃም በሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ ይህ ወሳኝ ጨዋታው ይሆናል።

በዚህ ጨዋታ ነጥብ ከጣሉ ለሻምፒዮንስ ሊግ ያላቸው ተስፋ ሙሉ ለሙሉ ያከትማል።

ዌስት ሃም ባለፈው ሳምንት ወደ ኦልድትራፎርድ አቅንቶ ከማሸነፉ በፊት በጥሩ አቋም ላይ አልነበረም።

በዚህ ጨዋታ ማን ሊያሸንፍ እንደሚችል መገመት ከባድ ነው።

ግምት፡ 1 – 1

ብሬንትፎርድ ከ ፉልሃም

ብሬንትፎርድ ያለፉትን አራት ጨዋታ በማሸነፉ ሰፊ ዕድል ይሰጠዋል።

ፉልሃም ደግሞ ማንንም ማሸንፍ እንደሚችል አሳይቷል።

በዚህ ምክንያት ጨዋታው በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል።

ግምት፡ 2 – 2

ሌስተር ሲቲ ከ ኢፕስዊች ታወን

ሌስተር ባለፈው ሳምንት ከፎረስት ጋር ጥሩ ተጫውተዋል።

በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ አንድሬ አይው በ94ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ጎል ሁለቱ ቡድኖች አቻ ተለያይተዋል።

18ኛ ደረጃን ለመያዝም ፉክክር የሚያደርጉበት ጨዋታ ነው።

ጂሚ ቫርዲ በሜዳቸው ለመጨረሻ ጊዜ ለሌስተር የሚሰለፍበት ጨዋታ ይሀናል።

ግምት፡ 2 – 1

አርሴናል ከ ኒውካስል ዩናይትድ

ይህ ጨዋታ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ የሚደረግ ፉክክር ነው።

ኒውካስል ዘንድሮ አርሴናልን ሦስት ጊዜ አሸንፏል።

መድፈኞቹ ውጤታቸውን ለመቀየር ስለሚፈልጉ ጠንካራ ፉክክር የሚታይበት ይሆናል።

ካለው ጎል ልዩነት አንጻር አርሴናል አንድ ነጥብ ካገኘ በሻምፒዮንስ ሊግ መሳተፉን ያረጋግጣል።

ግምት፡ 1 – 1

ሰኞ

ብራይተን ከ ሊቨርፑል

የሊቨርፑልን አሰላለፍ ማወቅ ስለማይቻል ለመገመት ከባድ ጨዋታ ነው።

ብራይተን በዩሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ለመሳተፍ ጨዋታውን ማሸነፍ ይኖርበታል።

ብራይተን ባለፈው ሳምንት ጥሩ ተጫውቶ ዎልቭስን አሸንፏል።

ግምት፡ 2 – 1