የኢትዮጵያ መንግሥት ከብራዚል እና ቻይና ጋር ያደረጋቸው ፍርደኞችን የማስተላለፍ ስምምነቶች ፓርላማ ቀረቡ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ የነበረው ስብሰባ

የፎቶው ባለመብት, HOPR

የፌደራል መንግሥቱ ከብራዚል እና ቻይና ጋር ፍርድኞችን ለማስተላለፍ ያደረጋቸው ስምምነቶችን ለማጽደቅ የተዘጋጁ አዋጆች ለተወካዮች ምክር ቤት ቀረቡ።

በተለያየ ጊዜ የተፈረሙት እነዚህ ስምምነቶች በሥራ ላይ እንዲውሉ "በሁለቱም አገራት መጽደቁን የሚያመለከት" ሰነድ በዲፕሎማቲክ መስመር ልውውጥ መደረግ አለበት።

በስምምነቶቹ መሠረት በአንደኛው አገር ወንጀል ፈጽሞ የቅጣት ውሳኔ የተላለፈበት ግለሰብ ወደ ሌላኛው የስምምነቱ ፈራሚ አገር ሊዘዋወር ይችላል።

ስምምነቱን ለማጽደቅ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ፤ ስምምነቶቹ "ፍርደኞች ቅጣታቸውን በአገራቸው መፈፀማቸው ታርመው ወደ ማኅበረሰቡ የሚቀላቀሉበትን ሒደት የሚያግዝ" መሆኑን ያትታል።

ነሐሴ 2016 ዓ. ም. ከቻይና ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት፤ ኢትዮጵያ የቻይና መንግሥት የሚያቀርባቸውን "የትብብር ጥያቄዎች የመፈፀም ወይም ተገቢውን ምላሽ የመስጠት ግዴታ" አለባት።

ይህ ግዴታ ከብራዚል መንግሥት ጋር በተደረገው ስምምነት ላይም ተካትቷል።

ኅዳር 2017 ዓ. ም. ከብራዚል ጋር የተፈረመው ስምምነት ማብራሪያ "ብዙ ብራዚላዊያን ከተለያዩ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ውስጥ በሕግ ጥላ ሥር የሚገኙ መሆናቸውን" ይገልጻል።

ከዚህ በተጨማሪም "ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ወንጀሎች ተፈርዶባቸው በብራዚል ማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙበት ዕድል ሰፊ በመሆኑ" ፍርደኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እንደሚያስችል ማብራሪያው ላይ ሰፍሯል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሌላ በኩል ከቻይና መንግሥት ጋር የተደረገው ስምምነት "ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ወንጀሎች ተፈርዶባቸው በቻይና ማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን" ይጠቅሳል።

እንዲሁም "ብዙ ቻይናውያን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙና ከተለያዩ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ውስጥ በሕግ ጥላ ሥር የሚገኙ በመሆናቸው" ስምምነቱ "ጠቀሜታ" እንደሚኖረው ያትታል።

በሁለቱም ስምምነቶች ፍርደኛን ለማዘዋወር ጥያቄ ለማቅረብ መሟላት የሚገባቸው መስፈርቶች በዝርዝር ተቀምጠዋል።

ከእነዚህ መስፈርቶች መካከል አንደኛው፤ ግለሰቡ የተቀባይ አገር ዜጋ ወይም መደበኛ ነዋሪ መሆን ቀዳሚው ነው።

በውሳኔ ሰጪ አገር የተሰጠው ውሳኔ "የመጨረሻ ፍርድ እና ተፈፃሚ መሆን የሚችል መሆኑ" በስምምነቱ ላይ የተቀመጠ ሌላኛው መስፈርት ነው።

ግለሰቡ የተፈረደበት የወንጀል ድርጊት በተቀባይ አገር ሕግ መሠረት እንደ ወንጀል የሚቆጠር ሊሆን እንደሚገባውም ስምምነቱ ላይ ተመላክቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ፍርደኛው እንደሁም ተቀባይ አገር እና ፍርድ ሰጪ አገር ስለሚከናወነው ዝውውር መስማማት እና ፈቃደኛ መሆን አለባቸው።

በፍርድ ሰጪ አገር የተሰጠ የቅጣት መጠን አፈጻጸም ተግባራዊ የሚደረገው፤ ፍርደኛው በምን ሁኔታ ሊታሰር እንደሚገባ፣ በገደብ ወይም በይቅርታ ስለሚለቀቅበት፣ ቅጣት ቀሪ ስለሚደረግበት ሁኔታ ተግባራዊ የሚሆነው የተቀባይ አገር ህግ ነው።

ቅጣት በማስፈጸም ሂደት ውስጥ "ለአፈፃጸም የሚያስችግር እስካልሆነ ድረስ በፍርድ ሰጪ ሀገር የተሰጠው ፍርድ እና የቅጣት መጠን ቆይታ. . . ቅጣቱ ቀሪ የሚሆንበትን ጊዜ ከግምት በማስገባት" ተፈጻሚ መሆን እንዳለበት ተደንግጓል።

ተቀባይ አገር "ከፍርድ ሰጪ የሚደርሳትን ቅጣን የመቀየር፣ የማስቀረት፣ በይቅርታ የመልቀቅ እንዲሁም ሌሎች ቅጣትን የመቀነስ ወይም ቀሪ ማድረግ" ይችላል።

በተጨማሪም "ተቀባይ አገር ፍርደኛው በይቅርታ ወይም ምሕረት የሚለቀቅ ከሆነም ለፍርድ ሰጭ አገር የማሳወቅ ግዴታ አለበት" የሚል አስገዳጅ ድንጋጌ በስምምነቶቹ ውስጥ ተካትቷል።