60 ደቡብ ኮሪያውያን በማጭበርበር ወንጀል ከካምቦዲያ ተባረሩ

የፎቶው ባለመብት, NEWS 1
በኦንላይን ማጭበርበር ወንጀል ተጠርጥረው በካምቦዲያ የታሰሩ 59 ደቡብ ኮሪያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርጉ።
የደቡብ ኮሪያ መንግሥት የማጭበርበር ወንጀል በሚፈጸምበት ማዕከል ተይዘው ስለሚገኙት ዜጎቹ ለመወያየት የልዑካን ቡድን ወደ ካምቦዲያ ከላከ ከጥቂት ቀናት በኋላ ቅዳሜ ማለዳ ላይ 59 ደቡብ ኮሪያውያን ኢንቼዮን አውሮፕላን ማረፊያ ደረሰዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሠረት በደቡብ ምሥራቅ እስያ ውስጥ በኦንላየን ማጭበርበር ወንጀል ላይ የተሰማሩ 200 ሺህ ገደማ ሰዎች ይገኛሉ።
አንዳንዶቹ ጥሩ ደመወዝ ይከፈላችኋል በተባሉት ሥራ ተታለው ወደዚህ ማጭበርበር ሲገቡ ሌሎች ደግሞ በጉልበት አንዲሳተፉ ተደርገዋል።
ባለሥልጣናቱ ወደ ካምቦዲያ ያቀኑት በደቡብ ኮሪያዊ የማጭበርበር ወንጀል ላይ የተሳተፈ ተማሪ ከደረሰበት ስቅይት በኋላ ሕይወቱ ማለፉ ከተገለፀ በኋላ ነው ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ሌሎች በሌሎች ወንጀሎች ላይ ተሳትፈው የተገኙ አምስት ደቡብ ኮሪያውያንም ከአገር እንዲወጡ ተደርገዋል።
አብዛኛዎቹ የቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር የዋሉት የካምቦዲያ ባለስልጣናት በወሰዱት እርምጃ ሲሆን አምስቱ ደግሞ ከወንጀል መረሙ አምልጠው ለመንግሥት እጃቸውን ሰጥተዋል ሲል ቢቢሲ ኮሪያ ዘግቧል።
ከአውሮፕላን ማረፊያው ወደ ሚመለከተው ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው ምርመራ ይደረግላቸዋል ተብሏል።
ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በቻርተር አውሮፕላን ውስጥ ከገቡ በኋላ ብዙም ሳይቆይ መሆኑን ባለሥልጣኑ ተናግረዋል ሲል የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
በደቡብ ኮሪያ ሕግ መሠረት፣ የአገሪቱ ብሔራዊ ባንዲራን የሚያውለበልበው አውሮፕላን እንደ የኮሪያ ግዛት ይቆጠራል፣ ይህም የሕግ አስከባሪ አካላት የእስር ማዘዣዎችን እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል።
የደቡብ ኮሪያ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ዊ ሱንግ-ላክ እንደተናገሩት ወደ አገራቸው የተመለሱት የቡድኑ አባላት በማጭበርበር ውስጥ "በፈቃደኝነት እና ያለ ፈቃዳቸውም" ተሳትፎ አድርገዋል።
ዊ "አብዛኛዎቹ የወንጀል ድርጊቶችን እንደፈጸሙ ይቆጠራል" ሲሉ ተናግረዋል።
ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የተደረጉት ከሳይበር ወንጀል ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት ከተደረገ በኋላ ነው።
የካምቦዲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሁን ማኔት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ከደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት ጋር "ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በተለይም የኦንላይን ማጭበርበሮችን ለመዋጋት" መወያየታቸውን ተናግረዋል።
"የኦንላይን ማጭበርበሮችን ለመከላከል፣ ለመቀነስ እና ለመዋጋት ካምቦዲያ እና የኮሪያ ሪፐብሊክ ትብብራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን" ሲሉ ጽፈዋል።
የደቡብ ኮሪያውያኑ መመለስ የተሰማው የአሜሪካ መንግሥት በዚህ ሳምንት መጀመርያ ላይ የክሪፕቶ ማጭበርበር ይፈጽማል የተባለውን የካምቦዲያ የቢዝነስ ቡድን 14 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ክሪፕቶ በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ ነው።
በክልሉ በሚገኙ የኦንላይን ማጭበርበሪያ ማዕከላት ከሚካሄዱ ወንጀሎች አንዱ የክሪፕቶ ማጭበርበር ነው።
ሌላው አጭበርባሪዎቹ ፍቅረኛ መስለው በመቅረብ ባህር ማዶ ከሚገኙ ግለሰቦች ገንዘብ የሚያጭበረብሩበት ወንጀልም የሚፈፀመው በእነዚሁ ማዕከላት ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማዕከላቱ በየዓመቱ ለወንጀለኛ ቡድኖች በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ገቢ እንደሚያስገኙ ይገምታል።















