በማጭበርበር የተገኘ 14 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቢትኮይን ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በበይነ መረብ በተፈጸመ ማጭበርበር የተገኘ ነው የተባለ ከ14 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ቢትኮይን መያዙን የአሜሪካ መንግሥት አስታወቀ።
'ፕሪንስ ግሩፕ' የተባለ የካምቦዲያ የንግድ ተቋም መስራች የሆነው ቼን ዢ በማጭበርበር ወንጀሉ ተከሷል።
የካምቦዲያ እና ዩናይትድ ኪንግደም ዜግነት ያለው ግለሰቡ፤ በኒው ዮርክ ፍርድ ቤት በበይነ መረብ ማጭበርበር እና ሕገ ወጥ ገንዘብን ወደ ሕጋዊ መስመር በማስገባት ተከሷል።
የንግድ ሥራው በአሜሪካ እና ዩኬ ዕገዳ ተጥሎበታል። በለንደን ያሉ 19 ቅንጡ መኖሪያዎችም ታግደዋል።
ከመኖሪያዎቹ አንደኛው 133 ሚሊዮን ዶላር ያወጣል።
ቢቢሲ ከ 'ፕሪንስ ግሩፕ' ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
የአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ እንዳለው በአገሪቱ ታሪክ ትልቁ የፋይናንስ ማጭበርበር ነው። ከዚህ ቀደም ከፍተኛ መጠን ያለው ቢትኮይን በቁጥጥር ሥር ውሎም አያውቅም።
ተጠርጣሪው እስካሁን ባይያዝም በንግድ ተቋሙ አማካይነት የበይነ መረብ ማጭበርበር በመፈጸም ተከሷል።
ተቋሙ፤ በቤት ግንባታ እና በፋይናንስ አገልግሎት ላይ የተሰማራ ነው። በእስያ ትልቁ የሆነ የወንጀል ቡድን እንደሆነም ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።
በካምቦዲያ የቤት ግንባታ እየተከናወነ እንደሆነ በማስመሰል ግለሰቡ ብዙዎችን ማጭበርበሩን ቢቢሲ የተመለከታቸው የፍርድ ቤት ሰነዶች ይጠቁማሉ።
ግብረ አበሮቹ 1,250 ተንቀሳቃሽ ስልኮች በመጠቀም 76,000 ማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ከፍተው ወንጀሉን መፈጸማቸው ተጠቁሟል።
የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ዐቃቤ ሕግ ጆን ኤ ኢስንበርግ እንዳሉት፤ 'ፕሪንስ ግሩፕ' "ከሰዎች እንግልት የሚያተርፍ" ተቋም።
ተቋሙ እስር ቤት የሚመስሉ ቅጥር ግቢዎች ውስጥ ሠራተኞችን በመሰብሰብ ወንጀል እንዲፈጽሙ እንደሚያስገድድ ተናግረዋል።
ተጠርጣሪዎቹ ውድ ሰዓቶች፣ ጀት እና ሌሎችም ቅንጡ መገልገያዎች እንደሚገዙም ተደርሶበታል። በኒው ዮርክ ከተካሄደ ጨረታ የፒካሶን ሥዕልም ገዝተዋል።
ቼን ዢ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ 40 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት ሊፈረድበት ይችላል።
ግለሰቡ በማዕከላዊ ለንደን 100 ሚሊዮን ፓውንድ የሚያወጣ ቢሮ ያለው ሲሆን በመኖሪያ ቤቶቹ አንደኛው 12 ሚሊዮን ፓውንድ ይገመታል።
'ፕሪንስ ግሩፕ' የወንጀል ቡድን ነው ተብሎ በአሜሪካ ታግዷል።
የዩኬ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የቬት ኩፐር "የምስኪን ሰዎችን ሕይወት አመሰቃቅለዋል" ብለዋል።
የወንጀል ቡድኑ የቁማር ቤቶች እና ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ መስመር ውስጥ የሚያስገቡ ስውር ማዕከሎችም ከፍቷል።
ከ 'ፕሪንስ ግሩፕ' ጋር በትስስር የሚሠሩት 'ጂኒ ቤይ ግሩፕ'፣ 'ጎልደን ፎርቹን ሪዞርትስ ወርልድ' እና 'ባዬክስ ኤክስቼንጅ' ዕድግ ተጥሎባቸዋል።
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያስረዳው፤ ተቋማቱ በካምቦዲያ በከፈቷቸው ማዕከሎች ሰዎችን በግዳጅ በማሠራት ብዝበዛ ፈጽመዋል።
በሐሰተኛ የፍቅር ግንኙነት ሰዎችን እንደሚያጠምዱ እና ወንጀሉን 'በኢንዱስትሪ ደረጃ' ሲፈጽሙ እንደነበር ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።
የዩኬ ፀረ የበይረ መረብ ማጭበርበር ኃላፊ ሎርድ ሀንሰን "ሰዎች ዕድሜ ልካቸውን ያጠራቀሙትን ሃብት ተነጥቀዋል። ይሄንን መሰል ወንጀል አንታገስም" ብለዋል።















