የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት በቡድን 20 ስብሰባ ባለመሳተፋቸው "የሚጎዱት ራሳቸው ናቸው" ሲሉ ትራምፕን ተቹ

ራማፎሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ "ራስን የማግለል ፖለቲካ አይሠራም" ሲሉ በሚቀጥለው ሳምንት በጆሃንስበርግ ከተማ በሚካሄደው የቡድን 20 አገራት ስብሰባ ላይ እንደማይሳተፉ የገለጹትን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተቹ።

ትራምፕ፤ በሰፊው ውድቅ የተደረገውን 'ነጮች በደቡብ አፍሪካ እየተሳደዱ ነው' የሚል ክስ በምክንያትነት በመጥቀስ፤ አንድም የአሜሪካ ባለሥልጣን ስብሰባውን እንደማይሳተፍ ተናግረዋል።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ግን አሜሪካ ከስብሰባ መቅረቷ "የሚጎዳው ራሳቸውን ነው" ማለታቸውን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ ዘግቧል። የአሜሪካ ባለሥልጣናት መቅረት ስብሰባውን ከመካሄድ እንደማያግደው ገልጸዋል ተብሏል።

አሜሪካ "የዓለም ትልቋ ኢኮኖሚ እንደመሆኗ መጫወት የነበረባቸውን እጅግ ወሳኝ ሚና መተዋቸውን" በማንሳትም ወቅሰዋል።

ትራምፕ፤ በሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ኅዳር 13 እና 14/2018 ዓ. ም. የሚካሄደው የቡድን 20 አገራት ስብሰባ በደቡብ አፍሪካ መዘጋጀቱን "ፍጹም አሳፋሪ" ሲሉ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ተችተዋል።

ከዚህ ቀደም ደቡብ አፍሪካ የቡድን 20 አገራት አባል መሆን እንደሌለባት የተናገሩት ትራምፕ፤ በስብሰባው ራሳቸው ከሚሳተፉ ይልቅ ምክትል ፕሬዝዳንታቸውን ጄዲ ቫንስን መላክ እንደሚመርጡ ገልጸው ነበር።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ግን የደች ሰፋሪዎች እንዲሁም የፈረንሳይ እና ጀርመን ስደተኞች ዝርያ ያላቸው ነጭ አፍሪካነሮችን በመለከተ የሚያነሱትን ውንጀላ አጠናክረዋል። "አፍሪካነሮች እየተገደሉ እና እየታረዱ እንዲሁም መሬት እና እርሻቸው በሕገ ወጥ መንገድ እየተወሰደባቸው ነው" ብለዋል።

"ይሄ የሰብአዊ መብት ጥሰት እስከቀጠለ ድረስ አንድም የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣን አይሳተፍም" በማለትም አክለዋል።

ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚፈቀድላቸው ስደተኞች ቁጥር ለመገደብ እየሞከሩ ያሉትን ትራምፕ፤ አፍሪካነሮች ግን ወደ አገሪቱ መምጣት እንደሚፈቀድላቸው ከዚህ ቀደም ተናግረዋል።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ራማፎሳ፤ "[በስብሰባው] ከመሳተፍ መታቀብ የትኛውንም ትልቅ ተጽዕኖ ያለውን ነገር አያሳካም፤ ምክንያቱም የተለያዩ ጉዳዮችን ወደፊት የሚያስቀጥሉ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ" ማለታቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።

የዓለም ትልቅ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆኑ አገራት የተሰባሰቡበት የቡድን 20 የወቅቱ ሊቀ መንበር ደቡብ አፍሪካ ነች። ስበሰባው በአፍሪካ ሲካሄድ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

በየዓመቱ የተለያዩ አገራት የቡድን 20 መሪነትን ሥልጣን የሚረከቡ ሲሆን፤ ሊቀ መንበር የሆነው አገር የስብሰባውን አጀንዳዎች መቅረጽ ይችላል። አገራቱ ከሚወያዩባቸው ዋነኛ አጀንዳዎች መካከል የወቅቱ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ይጠቀሳል።

ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ የአዘጋጅነት ኃላፊነቱን የምትረከበው አሜሪካ ነች።

ዶናልድ ትራምፕ በስብሰባው ላለመሳተፍ የወሰኑ ብቸኛው መሪ አይደሉም። የትራምፕ የቅርብ አጋር ሆኑት የአርጀንቲናው ፕሬዝዳንት ኻቪየር ሚሌ ስብሰባው ላይ እንደማይገኙ፤ በምትኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን እንደሚልኩ መናገራቸውን የኤኤፍፒ ዘገባ ያሳያል።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት፤ ነጮች ላይ ዘርፍ ማጥፋት ተፈጽሟል የሚለው ውንጀላ "በሰፊው ውድቅ የተደረገ እንዲሁም ተጨባጭ በሆነ ማስረጃ ያልተደገፈ" እንደሆነ ይናገራል። ያለ ካሳ መሬቱን የተቀማ ነጭ ገበሬ እንደሌለም ገልጿል።