በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ባለችው ሱዳን ከ430 በላይ ሰዎች በኮሌራ ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በምተገኘው ሱዳን ባለፈው ወር ከ430 በላይ ሰዎች በኮሌራ ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 14,000 መድረሱንም አመልክቷል።
ጨምሮም የኮሌራ ወረርሽኝ በተከሰተባቸው የአገሪቱ ግዛቶች ውስጥ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ባለበት ሁኔታ በሽታውን ለመቆጣጠር የሚቻለውን ሁሉ ሲያደርግ እንደነበረ ገልጿል።
በሱዳን የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ቶም ፔሪሎ እንዳሉት አንድ ዓመት ባለፈው እና አስከ 150 ሺህ ሰዎች በገደለው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ኮሌራ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ህክምና ማግኘት በጣም ውስብስብ ነው።
የህክምና በጎ አድራጎት የሆነው ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) “በተፋላሚ ኃይሎቹ ምክንያት ሥራቸው እንቅፋት ስለሚገጥመው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ከሚያስፈልገው በታች ነው” በማለት በአገሪቱ ያለውን ሁኔታ ገልጾታል።
ሱዳን ከሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በአገሪቱ ጦር ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል በተቀሰቀሰ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፣ ያለው ሁኔታ በዓለም ላይ አስከፊ ወደ ሆነ የሰብአዊ ቀውስ የሚያመራ ነው በማለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስጠንቅቋል።
በጦርነቱ ምክንያት ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከመኖሪያቸው ለመፈናቀል የተገደዱ ሲሆን፣ ገበሬዎች ሰብል ማምረት የሚያስችል ሁኔታ ውስጥ ባለመሆናቸው ሰፊ ቦታን የሚሸፍን ረሃብ ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
በምዕራባዊቷ የአገሪቱ ግዛት ዳርፉር ውስጥ አረብ ባልሆኑ ማኅበረሰቦች ላይ የዘር ማጥፋት ሳይፈጸም አይቀርም የሚል ማስጠንቀቂያ ሲወጣ ቆይቷል።
ኮሌራ በፍጥነት ሥር የሚሰድ እና ከሰው ሰው የሚተላለፍ በሽታ ሲሆን፣ በተቅማጥ አማካኝነት የታማሚዎችን የሰውነት ፈሳሽ በማሟጠጥ ለሞት ሊያበቃ እንደሚችል የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
ነገር ግን በሽታው በአንጻራዊነት በቀላሉ የሚድን ቢሆንም ፈጣን ህክምና ማግኘት ግን በእጅጉ አስፈላጊ ነው።
የሱዳን የጤና ሚኒስትር ሃይታም ሞሐመድ ኢብራሂም ባለፈው ነሐሴ ወር ላይ በአገሪቱ የኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱን አውጀው ነበር።
ከሚካሄደው ጦርነት በተጨማሪ ለወረርሽኙ መባባስ የጣለው ከባድ ዝናብ እና የተከተለው ጎርፍ እንዲሁም በተፈናቃዮች ካምፕ ውስጥ ያለው መጨናነቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።
የድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በሱዳን የአስቸኳይ ጊዜ አስተባባሪ ኤስፔራንዛ ሳንቶስ እንዳሉት እነዚህ ሁኔታዎች ለኮሌራ መስፋፋት “እጅግ አመቺ ሁኔታን ፈጥረዋል” ብለዋል።
በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች የወረርሽኙን መስፋፋት ለመቆጣጠር ትምህርት ቤቶች፣ የገበያ ስፍራዎች እና የንግድ ማዕከላት እንዲዘጉ ታዘዋል።
በድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን የወጣ አዲስ ሪፖርት በአገሪቱ ያለው የጤና ሥርዓት ከአገልግሎት ውጪ በመሆኑ የተነሳ ነፍሰጡር ሴቶች እና ህጻናት ክፉኛ እንደተጎዱ አመልክቷል።
ካለፈው ጥር አስከ ነሐሴ ድረስ ባለው ጊዜ በደቡብ ዳርፉር አካባቢ 114 የእናቶች እና የሕጻናት ሞቶች የተመዘገቡ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናት የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል - ብሏል ሪፖርቱ።












