ማንቸስተር ሲቲ ከመመራት ተነስቶ ቶተናሃምን አሸነፈ

ጁሊያን አልቫሬስ ለሲቲ የመጀመሪያውን ጎል ሲጣስቆጥር

የፎቶው ባለመብት, Matt McNulty - Manchester City

የምስሉ መግለጫ, ጁሊያን አልቫሬስ ለሲቲ የመጀመሪያውን ጎል ሲጣስቆጥር

ማንቸስተር ሲቲ ከሁለት ጎል ዕዳ ተነስቶ ቶተንሃምን በመርታት ከመሪው አርሰናል ጋር ያለውን የጎል ልዩነት ማጥበብ ችሏል።

በኤቲሃድ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ደካም የነበሩት ሲቲዎች በሁለተኛው አጋማሽ ተጠናክረው ገብተዋል።

ስፐርስ በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ አከታትለው ሁለት ጎሎች በማስቆጠር ሲቲዎች ላይ ጫና መፍጠር ቢችሉም ማንቸስተር ሲቲ ከእረፍት በኋላ ሌላ ቡድን ሆኖ ቀርቧል።

ዴጃን ኩሉሴቭስኪ የማንቸስተር ሲቲን ስህተት ተከትሎ ያገኛትን ኳስ ወደ ጎል በመቀየር ቶተንሃምን ጨዋታውን እንዲመራ አድርጓል።

ከሁለት ደቂቃ በኋላ ሃሪ ኬን አክርሮ ወደ ጎል የመታትን ኳስ የሲቲው በረኛ ሲተፋት ኤመርሰን ሮያል በግንባሩ ወደግብ ቀይሯታል።

የሲቲ ደጋፊዎች በሁለት ደቂቃ ውስጥ ቆሌያቸው ሲገፈፍ፣ በቡድናቸው አቋም ላይ ያላቸውን ምሬት ሲገልጹ ተሰምተዋል።

ነገር ግን የፔፕ ጉዋርዲዮላ ቡድን አቋሙን አስተካክሎ ለሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታ ወደ ሜዳ ዘልቋል።

በሪያድ ማህሬዝ የተመራ የሲቲ የአጥቂ መስመር በ12 ደቂቃ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር የጨዋታውን ውጤት ገልብጦታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጁሊያን አልቫሬዝ የቶተንሃሙ በረኛ የመለሳትን ኳስ ወደ ጎል በማስቆጠር ለሲቲዎች የመጀመሪያውን ጎል ሲያስቆጥር፣ ኧርሊንግ ሃላንድ ደግሞ ከማህሬዝ ያገኛትን ኳስ በግንባሩ ወደ መረብ በመሸኘት ቡድኑ አቻ እንዲሆን ማድረግ ችሏል።

ሪያድ ማህሬዝ ድንቅ ጎል አስቆጥሮ ሲቲዎች ወደ መሪነት ከመመለሳቸው በፊት ኢቫን ፔሪሲች ወደ ግቡ የሰደዳትን ኳስ ታዳጊው የሲቲ ተጫዋች ሪኮ ሊዊስ አምክኖበታል።

ጉምቱው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ኡጎ ሎሪስ ባለፈው እሑድ ከአርሰናል ጋር በነበረው ጨዋታው ቀላል የሚባል ስህተት መሥራቱ የሚታወስ ነው።

በዚህኛውም ጨዋታ ተመሳሳይ ሊባል የሚችል ስህተት በመሥራት ሲቲዎች ጨዋታውን እንዲመሩ አድርጓል።

በሐሙሱ ጨዋታ ድንቅ የነበረው አልጄሪያዊው ሪያድ ማህሬዝ የቶተንሃሙ በረኛ ባጠበበት አቅጣጫ ኳሷን በመለጋት ሲቲዎች ከሁለት የጎል ዕዳ ተነስተው እንዲመሩ አድርጓል።

ማህሬዝ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ለራሱ ሁለተኛ፣ ለሲቲ ደግሞ አራተኞ ጎል በማስቆጠር የጉዋርዲዮላ ቡድን ጨዋታውን በድል እንዲወጣ አስችሏል።

ሲቲዎች ከእረፍት በኋላ ያሳዩት ብቃት በጣም ድንቅ ሆኖ ሲገኝ ቶተንሃሞችም በበኩላቸው በመጀሪያው አጋማሽ ያሳዩትን ፍልሚያ ሊደግሙ አልቻሉም።

ከማህሬዝ በተጨማሪ የ18 ዓመቱ የሲቲው ሪኮ ሊዊስ ተስፋ ያለው እግር ኳሰኛ መሆኑን ያስመሰከረበት ጨዋታ ነበር።

ማንቸስተር ሲቲ ከሁለት የጎል ተነስቶ ጨዋታ ሲያሸንፍ በቅርብ ጊዜ ታሪኩ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ባለፈው የውድድር ዘመን የመጨረሻ ጨዋታ እንዲሁ በአስተን ቪላ ሁለት ለባዶ ከመመራት ተነስቶ በመርታት ዋንጫውን ማንሳቱ አይዘነጋም።

በሌላ በኩል የትናንትን ምሽቱ ግጥሚያ የቶተንሃም ሆትስፐርስ በረኛ ኡጎ ሎሪስ ብቃት እየወረደ እንደመጣ የታየበት ነበር።

የ36 ዓመቱ ሎሪስ የሰሜን ለንደኑን ክለብ ከ10 ዓመታት በላይ አገልግሏል።

የሐሙሱን ጨዋታ ተከትሎ ሲቲ ከመሪው አርሰናል ጋር ያለውን ልዩነት ወደ 5 ዝቅ አድርጓል።

አርሰናል በሜዳው በሚመጣው እሑድ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠ ሌላኛው የማንቸስተር ከተማ ክለብ ጋር ተጠባቂ ጨዋታ አለው።

አርናል ከማንቸስተር ዩናይትድ ሰንበት ምሽት 1፡30 ይገናኛሉ። ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ 11 ሰዓት ላይ ሲቲ ዎልቭስን ያስተናግዳል።