ኢትዮጵያ ስለምትሳተፍበት የቻን ውድድር በጥቂቱ

የቻን ዋንጫ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአገር ውስጥ የእግር ኳስ ክለቦች የሚሳተፉ ተጫዋቾችን ብቻ በሚይዙ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል የሚከናወነው ሰባተኛው የቻን ወድድር በአልጄሪያ እየተካሄደ ይገኛል።

ዛሬ ከምሽቱ አራት ሰዓት ኢትዮጵያ አዘጋጇ አልጄሪያን ትገጥማለች።

ኢትዮጵያ በምድብ ‘ሀ’ ከአዘጋጇ አልጄሪያ፣ ሊቢያ እና ሞዛምቢክ ጋር የተመደበች ሲሆን፣ ያሳለፍነው ቅዳሜ ከሞዛምቢክ ጋር ያደረገችው ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል።

ዛሬ ምሽት ደግሞ ኢትዮጵያ ከአልጄሪያ ጋር የምታደርገው ጨዋታ ይጠበቃል።

ባለፈው ሳምንት አርብ የተጀመረው የዘንድሮ የቻን ውድድር ለሦስት ሳምንታት የሚዘልቅ ሲሆን 17 ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፉበታል።

አልጄሪያ እና ሞሮኮ በገበት ዲፕሎማሲያዊ መካረር ምክንያት በውድደሩ የመጨረሻ ቀናት ሞሮኮ ራሷን ከውድድሩ አግልላለች።

በፖለቲካዊ አለመግባባት ምክንያት አልጄሪያ የአየር ክልሏን ለሞርኮ ዝግ ብታደርግም፣ የሞርኮ ብሔራዊ ቡድን በልዩ በረራ በቀጥታ ወደ አልጄሪያ እንጓዝ የሚለው ጥያቄ ወድቅ መደረጉን ተከትሎ ነው ብሔራዊ ቡደኑ ራሱን ከውድድሩ ያገለለው።

የዘንድሮ የቻን ወድድር የታሳተፊዎች ቁጥር ከ16 ወደ 18 ያደገበትም ነው።

ከወድድሩ መጀመር ቀደም ብሎ በሞሮኮ ያረፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሞሮኮ ብሔራዊ ቡደን ጋር ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን አድርጎ በሁለቱም ተሸንፏል።

ውድድሩን 19 የመሐል ዳኞች፤ 21 ረዳት ዳኞች እና 12 የቪዲዮ [ቪኤአር] ረዳት ዳኞች ይሳተፉበታል። በዘንድሮው ቻን ከሚሳተፉት 52 ዳኞች መካከል ሦስት ሴት ዳኞች ይገኙበታል።

ኢትዮጵያዊው በአምላክ ተሰማ በቪድዮ ዳኝነት እንደሚሳተፍ ተዘግቧል። ይህም ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በቪዲዮ የታገዘ ዳኝነት የሚካሄድበት ነው።

እንደ አውሮፓውያኑ ከ2009 ጀምሮ ሲካሄድ በቆየው የቻን ውድድር ኢትዮጵያ ስትሳተፍ ዘንድሮ ሦስተኛዋ ነው።

አልጄሪያ ውድድሩን ስታዘጋጅ የመጀመሪያዋ ሲሆን፣ ጨዋታዎቹ በመዲናዋ አልጀርስ እንዲሁም በአናባ፣ ኮንስታንቲን እና ኦራን ከተሞች ይካሄዳሉ።

ከዚህ ቀደም ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሞሮኮ እያንዳንዳቸው ሁለት ጊዜ በማሸነፍ ግንባር ቀደም ሲሆኑ፣ ቱኒዝያ እና ሊቢያ እያንዳንዳቸው አንድ ጊዜ በማሸነፍ ይከተላሉ።

በካፍ የሚዘጋጀው ቻን እአአ በ2009 ስምንት ብሔራዊ ቡድኖች ብቻ ያሳተፈ ሲሆን፣ በስድስተኛው የውድድሩ ዙር ወደ 18 ብሔራዊ ቡድኖች አድጓል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ሩዋንዳ በተካሄደው ውድድር ከምድብ መሳናበቷ ይታወሳል።

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በርካታ ወጣት ተጫዋቾች የተሞላ ሲሆን ጉምቱ የሚባሉት ጌታነህ ከበደና ሱራፌል ዳኛቸው የመሳሰሉ ተጫዋቾች በቡድኑ አልተካተቱም።

ጌታነህ ከበደ ብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾቹን ይፋ ከማድረጉ በፊት ከብሔራዊ ግዴታ ራሱን ማግለሉን አሳውቋል።