የናይጄሪያ ባለሥልጣናት ‘በኢንዶሚ ኑድልስ’ ላይ ምርመራ ማድረግ ጀመሩ

ኢንዶሚ ኑድልስ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የኢንዶኔዢያው የኢንዶሚ ኑድልስ አምራች የምግብ ምርቱ ምንም አይነት ችግር እንደሌለበት እየተከራከረ ነው

የናይጄሪያ የምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር መሥሪያ ቤት በካንሰር የመያዝ ዕድልን የሚያስከትል ንጥረ ነገር ይዞል በተባለው የኑድልስ ምርት ላይ ምርመራ እያደረጉ ነው።

ተቆጣጣሪው መሥሪያ ቤት “ኢንዶሚ” በተባለው የኑድልስ ምርት ላይ የቀረበውን ጥያቄ ለማጣራት “ፈጣን እርምጃ” እየወሰደ መሆኑን አሳውቋል።

የምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው “የኢንዶሚ ኑድልስ ምርት የተለያዩ ናሙናዎችን እና ቅመማ ቅመሞቹን በመውሰድ” ኢቲሊን ኦክሳይድ የተባለው ለጤና ጎጂ ንጥረ ነገር እንዳለበት ምርመራ እያደረገ ነው።

በተጨማሪም ከተጠቀሰው የኑድልስ ምርት በተጨማሪ ምርመራው በናይጄሪያ ገበያ ውስጥ በሚገኙ በሌሎችም ተመሳሳይ ምርቶች ላይ ምርመራ እንደሚያደርግ አሳውቋል።

የምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር መሥሪያ ቤት ይህንን ምርመራ ማድረግ የጀመረው ባለፈው ሳምንት ማሌዢያ እና ታይዋን ውስጥ “ልዩ የዶሮ ጣዕም” አለው የተባለው ምርት ናሙናዎች ላይ አደገኛው ንጥረ ነገር ተግኝቷል ከተባለ በኋላ ነው።

በሁለቱ የእስያ አገራት ውስጥ በተጠቀሰው የኑድልስ ምርት ላይ ለጤና ጎጂ የሆነው ንጥረ ነገር በመገኘቱ ምርቶቹ ከገበያ እንዲሰበሰቡ ተደርጓል።

ኢንዶሚ የተባለውን ኑድልስ የሚያመርተው የኢንዶኔዢያው ግዙፍ የምግብ አምራች ተቋም የሆነው ኢንዶፉድስ ግን የምግብ ምርቱ ጤናማ መሆኑን በመግለጽ እየተከራከረ ነው።

የናይጄሪያ የምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር መሥሪያ ቤት ጨምሮም የተጠቀሰው የምግብ ምርት አይነት በአገሪቱ ውስጥ እንዲሸጥ ያልተመዘገበ እና ፈቃድ ያላገኘ መሆኑን ገልጿል።

ስለዚህም የኢንዶሚ ኑድልስ ምርት ወደ ናይጄሪያ የሚገባባቸው የወደብ ባለሥልጣናት ምርቱ እንዲገባ እንዳይፈቅዱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።

ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቱ ክስ ከቀረበበት ከኑድልስ ምርት ጋር በተያያዘ “በፋብሪካው እና ለገበያ በሚቀርብበት ሁኔታ ጭምር ምርመራ” በማካሄድ ውጤቱን ይፋ እንደሚያደርግ ገልጿል።

ፓስታ በሚመስለው ኑድልስ በመባል በሚታወቀው የምግብ ምርት ውስጥ ተገኘ የተባለው ኢቲሊን ኦክሳይድ ንጥረ ነገር በምግብ አምራች ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ጥቅም ላይ ይውላል።

ይህ ንጥረ ነገር ከተገቢው መጠን በላይ በምርቶች ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውል ከሆነ በሰዎች ጤና ላይ አደጋን ያስከትላል። ዓለም አቀፉ የካንሰር ጥናት ተቋም እንደሚለው ኢቲሊን ኦክሳይድ ካንሰር አምጪ ከሆኑ ንጥረ ነገሮች መካከል የሚመደብ ነው።