በአውስትራሊያ የጠፋው ዓሣ አስጋሪ በአዞ ሆድ ውስጥ ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አውስትራሊያ ውስጥ አንድ ዓሣ አስጋሪ ከጠፋ ከቀናት በኋላ አስከሬኑ በአዞ ሆድ ውስጥ ተገኝቷል።
ይህ ግለሰብ ከጓደኞቹ ጋር ዓሣ ሲያሰግር ከቆየ በኋላ ነው ጠፍቶ የነበረው።
ኬቨን ዳርሞዲ የተባለው ይህ ግለሰብ ለመጨረሻ ጊዜ የታየው በኩዊንስላንድ ግዛት ባለፈው ቅዳሜ ኬኔዲስ ቤንድ የአዞዎች ማዕከል ውስጥ ነበር።
በአካባቢው ለሁለት ቀናት ሙሉ ፍለጋ ከተደረገ በኋላ ፖሊስ ሁለት አዞዎችን በጥንቃቄ ራሳቸውን እንዲስቱ በማድረግ ያለ ስቃይ ከተገደሉ በኋላ ሆዳቸው ሲበረበር በአንዱ አዞ ውስጥ የጠፋው ግለሰብ አስከሬን ተገኝቷል።
ይህ በአዞው ውስጥ የተገኘው አስከሬን በትክክል የጠፋው ኬቨን ዳርሞዲ ስለመሆኑ በሳይንሳዊ መንገድ መረጋገጥ ቢኖርበትም፣ ፖሊስ ግን የ65 ዓመቱ ዓሣ አስጋሪ አስከሬን ስለመሆኑ ጥርጣሬ እንደሌለው አመላክቷል።
ኬቨን ዳርሞዲ የዓመታት ልምድ ያለው ዓሣ አስጋሪ እንደነበረ ባልንጀሮቹ ይመሰክራሉ።
በኬፕ ዮርክ አካባቢም በማኅበረሰቡ ዘንድ በደንብ የሚታወቅ ሰው ነበር።
ሁለቱ አዞዎች ቁመታቸው 4.1 ሜትር እና 2.8 ሜትር ሲሆን እንዲገደሉ የተደረገው ሰኞ ዕለት ነው።
አዞዎቹ የተገኙት ግን ሟች ለመጨረሻ ጊዜ ከታየበት ሥፍራ 1.5 ኪሎ ሜትር ርቆ ባለ ቦታ ነው።
ከሁለቱ አዞዎች ውስጥ የሰው አስከሬን የተገኘው በአንደኛው አዞ ሆድ ውስጥ ብቻ ነው።
ነገር ግን የዱር አራዊትና እንሰሳት ባለሙያዎች ሌላኛውም አዞ በሰውየው ግድያ ውስጥ እጁ ሳይኖርበት አይቀርም ነው የሚሉት።
በአካባቢው የነበሩት የሟች ባልደረቦች ዳርሞዲ ጥቃት ሲደርስበት እንዳልተመለከቱ ተናግረዋል። ነገር ግን የጩኸት ድምጽ መስማታቸውን እና ከዚያ በኋላ ደግሞ የውሃ መንቦራጨቅ ድምጽ መከተሉን መስክረዋል።
“ድምጹን ወደሰማሁበት ቦታ ሮጬ ሄድኩ፤ ነገር ግን እርሱ ከዚያ ቦታ ስለመኖረም ምንም ምልክት አልነበረም። ቱታው ብቻ እዚያ ስፍራ ተቀምጦ ነበር” ብሏል ጆን ፔይቲ የተባለ የሟች ወዳጅ ለኬፕዮርክ ዊክሊ ጋዜጣ።
አዞዎች በአስውስራሊያ ሰሜናዊ ክፍል በቁጥር በርካታ ናቸው።
ነገር ግን ሰዎች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸው ብዙም የተለመደ አይደለም። ዳርሞዲ በአዞ ተበልቶ ሲሞት ከአውሮፓውያኑ 1985 ወዲህ 13ኛው ሰው ነው።
በ2017 አንዲት ጎልማሳ ሴት በፖርት ዳግላስ አካባቢ ጠፍታ የቀረች ሲሆን፣ ምናልባት በአዞ እንደተበላች ይጠረጠራል።
ከዚያ አንድ ዓመት በፊትም እንዲሁ ሌላ ሴት በዴይንትሪ ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ በአዞ ተበልታለች።
አዞን ማደን በሕግ ከተከለከለ ከ1974 ዓመተ ምህረት ወዲህ በኩዊንስላንድ የአውስትራሊያ ግዛት ብቻ የአዞዎች ቁጥር ከ5ሺህ ወደ 30ሺህ አሻቅቧል።












