ኢትዮጵያ ፡ የአዞ ቆዳና ሥጋ ለምን ገበያ ራቀው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ከምታገኝባቸው ነገሮች መካከል አንዱ የአዞ ሥጋና ቆዳ ነው። አሁን ላይ ግን ምርቱ ቢኖርም ለዓለም ገበያ ማቅረብ አልተቻለም ሲሉ የደቡብ ክልል ባህል ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ለማ መሰለ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
በደቡብ ክልል የባህል ቱሪዝም ቢሮ ሥር የሚተዳደረው የአዞ እርባታ ጣቢያው የተመሠረተው በ1976 ዓ.ም ነው።
"ዋናው ዓላማው የናይል አዞ ዝርያን ማቆየት ነው" የሚሉት አቶ ለማ በሂደት ግን ዝርያውን ከማቆየት ባሻገር ቆዳውንና ሥጋውን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታስቦ ዘመናዊ ቄራ ተዘጋጅቶ ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአዞ ቆዳንም ሆነ ሥጋውን ለገበያ ማቅረብ አልተቻለም ይላሉ። በዚህ ዓመትም ታጅለው የተዘጋጁ 1500 ቆዳዎች ቢኖሩም ገዥ እንደጠፋ ያስረዳሉ። ሥጋውም ቢሆን ገዥ በማጣቱ መልሶ ለአዞ ምግብነት ውሏል።
የአዞ ቆዳ ለውጭ ገበያ በሚቀርብበትም ጊዜ ገቢው እምብዛም ባይሆን በዓመት ወደ 5 ሚሊየን ብር ገደማ ያስገኝ ነበር። ይህ ማለት ደግሞ ቢያንስ ለእርባታ ጣቢያው በዓመት ከመንግሥት ከሚበጀተው 8 ሚሊየን ብር ገደማ ከግማሽ በላዩን ራሱ ይሸፍን ነበር ማለት ነው።
"የአዞ ቆዳ በሴንቲ ሜትር ነው የሚሸጠው፤ አንደኛ ደረጃ ቆዳ አንድ ሴንቲ ሜትር በአራት ዶላር ይሸጣል፤ በመሆኑም የአንድ አዞ ቆዳ አርባ ሴንቲ ሜትር ቢሆን 40 ዶላር ይሸጣል" ሲሉ የመሸጫ ዋጋውን ያስረዳሉ። ሥጋው ግን ከተሸጠ ብዙ በመቆየቱ ዋጋውን እንኳን በውል እንደማያስታውሱት ያስረዳሉ።
በአሁኑ ሰዓት 3ሺህ የሚሆኑ አዞዎች በአርባ ምንጭ እርባታ ጣቢያው እንደሚገኙ የነገረን ደግሞ የጣቢያው ባለሙያ አቶ መሠረት ደምለው ነው። እነዚህ አዞዎች ዕድሜያቸው ከ1 እስከ 29 ዓመት የሚደርስ ነው። ከእነዚህ መካከል ለእርድ የደረሱም ይገኙበታል።
ብዙ ጊዜ ለእርድ የሚመረጡት ዕድሜያቸው ከ4 እስከ 8 ዓመት የሆናቸው ሲሆኑ ከዚያ ከፍ የሚሉት ደግሞ ለቱሪስት መስህብነት ያገለግላሉ።
በአዞዎች ሥነ ሕይወት ከ120 እስከ 150 ዓመት ድረስ መኖር ቢችሉም በእርባታ ጣቢያው ውስጥ በዚህ የዕድሜ ክልል የሚገኙ አዞዎች ግን የሉም። ምክንያቱም እዚህ የእድሜ ደረጃ እስከሚደርሱ አይጠበቁም።
አዞ ለእርድ እንዴት ይዘጋጃል?
በጎችን ስንገዛ ወገባቸውን በእጃችን ጨበጥ ለቀቅ እያደርግን እንደምንለካው ሁሉ አዞዎችም ለእርድ መድረሳቸው የሚረጋገጠው ደረታቸውን በመለካት ነው።
በዚህም መሠረት የደረት ስፋታቸው ከ25-50 ሴንቲ ሜትር የደረሱ አዞዎች ለገበያ ደርሰዋል ይባላል። አዞዎች ለገበያ መድረሳቸው የሚረጋገጠው በደረት ስፋታቸው ብቻም ሳይሆን ዕድሜያቸውም ከግምት ውስጥ ይገባል።
ለእርድ የተመረጠው አዞ አበላለቱ በተለይ ከአሳ ጋር የመመሳሰል ባህሪ አለው።
በመጀመሪያ ለእርድ የተዘጋጀው አዞ ካለበት ቦታ ላይ እያለ ይገደላል። አዞ አደገኛ በመሆኑ ዝም ተብሎ አይገደልም ታዲያ። አሳን መብላት በብልሃት እንደሚባለው ለእርሱም ብልሃት አለው።
ጭንቅላቱ መሃል (አናቱ) ላይ ለእርሱ መግደያ ተብሎ በተዘጋጀ ብረት ይወጋል። ምክንያቱም በዚህ መልኩ ካልተወጋና ካልሞተ በስተቀር መያዝም ሆነ ቆዳውን መግፈፍ አይቻልም።
አዞ የዱር እንስሳ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አደጋ እንዳያደርስ በተለይ በመያዝ ሂደቱ ላይ የተለያዩ ጥንቃቄዎች ይደረጋሉ። ይሁን እንጂ የሚያርዷቸውም እዚያው ሲንከባከቧቸው የሚውሉ ባለሙያዎች በመሆናቸው እምብዛም ጉዳት አያደርሱም።
መሞቱ ከተረጋገጠ በኋላ እዚያው እርባታ ጣቢያው ወደሚገኝ የአዞዎች ቄራ ይጓዛል። እዚያም ደሙ እንዲንጠፈጠፍ ከተደረገ በኋላ ታርዶ ቆዳው ይገፈፋል።
ቢቢሲ፡ የአዞ ሥጋ ብልት አለው እንዴ?
አቶ መሠረት፡ ዝም ብሎ በክፍል በክፍል ይወጣል...የሚፈለገው የትኛው አካባቢ ነው በሚለው ላይ ተመስርቶ ሥጋው እየተለየ ይወጣል። አንዳንድ ሥጋ ፈላጊዎች ከቄራ ሠራተኞች ጋር ተነጋግረው የሚፈልጉትን ይወስዳሉ።
ቢቢሲ፡ በአብዛኛው ግን የሚፈለገው የትኛውን የሥጋ ክፍል ነው?
አቶ መሠረት፡ ሳቅ …ፍርንባው፣ ይሄ ከደረቱ ክፍል ያለው አለ አይደል…እርሱን ብዙ ሰው ይወደዋል።
ቢቢሲ፡ የአዞ ጥሬ ሥጋ ይበላል እንዴ? እንዴት ነው ቁርጡ?
አቶ መሠረት፡ በባህላችን የእኛ ሰው ጥሬውንብዙም አይመገብም ፤ነገር ግን በጥብስ መልክ የሚመገቡ አሉ።
ቢቢሲ ፡ ኢትዮጵያዊያን?
አቶ መሠረት፡ አዎ!
ቢቢሲ፡ እንዲያው ግን ከቀዩ አሊያም ከነጩ ይደረግልኝ ብሎ ማማረጥ ይቻላል?
አቶ መሠረት፡ ሳቅ… እንደውም ሥጋው ወደ ነጭ ያደላ ነው፤ ከአሳ ሥጋ ብዙ አይለይም፤ ግን ያው ሥጋ ተመጋቢ ስለሆነ ነጩ ይበዛል.. ስብ ነው። ቢሆንም ግን ከጀርባው አካባቢ ቀይ ሥጋም አለው።
በአዞ እርባታ ጣቢያው የተለያዩ የውጭ አገር ዜጎች ጎራ ብለው ሥጋቸውን አስመዝነው ይዘው ይሄዳሉ እንጂ የአዞ ሥጋ ተጠብሶ የሚበላበት ምግብ ቤት የለም ይላሉ አቶ መሠረት።
ገበያው ደርቶ አዞ የታረደ ከሆነ በሚመች መልኩ ሂደቱን ጨርሶ ማቀዝቀዣ በተገጠመላት መኪና ተደርጎ ይላካል። ገበያ ከሌለው ግን ቆዳው ተገፎ ሥጋውን መልሰው ለአዞዎቹ ይመግቧቸዋል።
እርሳቸው በሥራ ላይ በቆዩበት ሁለት ዓመታት ውስጥ ወደ ውጭ አገር ከሚላከው የአዞ ሥጋ ይልቅ በተዘዋዋሪ ሰዎች ቦታው ድረስ በማቅናት ገዝተው የሚሄዱት የተሻለ እንደሆነና በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የአዞ ሥጋ ወደ ውጭ እንዳልተላከ ይናገራሉ።
በቂ የሥጋ ማቀነባበሪያ መሳሪያዎች ባለመኖራቸው ምክንያት ደረጃውን ጠብቆ መስራት ስላልተቻለ ተቋርጧል።
የአዞ ቆዳ ከደረቱ ክፍል በኩል በጥንቃቄ ተገፎ በጨው ታጅሎ እስከ ብዙ ጊዜ ማቆየት ይቻላል። ገበያ ካልተገኘ እስከ ሁለት ወርና ሦስት ወርም ሊቆይ ይችላል። ገበያ ካልተገኘ ቆዳ ልማት ኢንስቲቲዩት ይገባል።
አንድ የአዞ ቆዳ ከ2500-3000 ብር (104 የአሜሪካ ዶላር) ድረስ ይሸጣል፤ በዚህ ዓመትም 1500 የአዞ ቆዳዎችን ደረጃቸውን ለይተው ለኢትዮጵያ ቆዳ ልማት ኢንስቲቲዩት መላካቸውን ባለሙያው ገልፀዋል።
ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የቆዳ ስፋትም ከ20 ሴንቲ ሜትር እስከ 50 ሴንቲ ሜትር ቢሆንም ጥራቱ በስፋቱ ብቻ አይወሰንም። አንዳንዴ 50 ሴንቲ ሜትር ስፋት ኖሮት በጥራቱ ሁለተኛ ደረጃ ሊሆን ይችላል።
ምክንያቱ ደግሞ አዞው ከዚህ ቀደም ያጋጠመው በሽታ ካለ እና ቆዳው በሚገፈፍበት ወቅት እንከን ካለው የአዞ ቆዳው ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚያሳድር ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ የአዞ ሥጋንና ቆዳን ወደ ውጭ በመላክ የምታገኘው የውጪ ምንዛሬ እየተቀዛቀዘ መምጣቱን የሚናገሩት ባለሙያው ከዚህ ቀደም ወደ ፈረንሳይ፣ ጣሊያንና አውስትራሊያ በአብዛኛው የአዞ ሥጋ ይላክ እንደነበር ያስታውሳሉ።
የአዞ ቆዳና ሥጋ ገበያ ለምን አልደራም?
ከዓመታት በፊት ያጋጠመው የዓለም ኢኮኖሚ መውደቅ ላለፉት አራትና አምስት ዓመታት የአዞ ገበያው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳሳረ አቶ ለማ ያስረዳሉ። በመሆኑም አዞዎችን ከጫሞና ከአባያ ሐይቅ በማምጣትና እንቁላሎችን በማስፈልፈል የአዞ እርባታውን ሂደት ማስቀጠል አልተቻለም። በዚህም ሳቢያ ላለፉት አምስት ዓመታት የአዞ ቆዳ መሸጥ አለመቻሉን ይናገራሉ።
"አብዛኛውን ጊዜ የሚገዙት የውጭ ድርጅቶች ናቸው" የሚሉት ኃላፊው የውጭ ገበያውን በማጥናት የዓለም ገበያ ፍላጎትን ማወቅ አለመቻላቸውንም እንደ ተጨማሪ ምክንያት ያስቀምጣሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ አቅርቦታቸው ውስን በመሆኑ 2 ሺህ የአዞ ቆዳዎችን ብቻ ለመግዛት የሚመጣ ኩባንያ አለመኖሩንም ያነሳሉ። በመሆኑም በጥቃቅን ደረጃ ምርቱን የወሰዱ ድርጅቶች ቢኖሩም በብዛት ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ግን አልተቻለም።
ኃላፊው እንደሚሉት በአባያና ጫሞ ሐይቅ ብቻ የሚገኙትን የናይል አዞ ዝርያዎች ጠብቆ ለማቆየት ሲባል ለአዞ እርባታ ጣቢያው ብዙ በጀት ይመደባል። በመሆኑም ለቀለብ ብቻ በዓመት አንድ ሚሊዮን ብር ይወጣል። ከሌሎች ወጪዎች ጋር ሲደመር በዓመት እስከ 8 ሚሊየን ብር ገደማ በጀት ይመደባል።
ይሁን እንጂ ይህንን የሚያካክስ ገንዘብ ከቆዳና ከሥጋ ምርቱ ባይገኝም ከቱሪዝም የተወሰነ ገቢ ይገኛል። ቢሆንም ግን ከቱሪዝም በዓመት የሚገኘው ከ1.5 እስከ 2 ሚሊዮን ብር ከወጪው ጋር የሚመጣጠን አለመሆኑን ኃላፊው አክለዋል።
"የመንግሥት ዋናው ትኩረት ዝርያውን መጠበቅ ላይ ቢሆንም ንግዱን ግን ሌላ የግል ድርጅት እንዲሰራ ቢመቻቻች ውጤቱ አመርቂ ሊሆን ይችላል" ሲሉ አቶ ለማ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። ይህንንም በተለመለከተ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን አዲስ ዕቅድ እያዘጋጁ እንደሆነም ገልፀውልናል።














