ቻይና ውበታቸውን ተጠቅመው ከሚያማልሉ ሰላዮች እንዲጠበቁ ዜጎቿን አሳሰበች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቻይና “ልዩ የሆነ አካላዊ ውበትን” ተጠቅመው ከሚያማልሉ የውጭ አገር የስለላ ተቋማት ወኪሎች እንዲጠነቀቁ ለዜጎቿ ማሳሰቢያ ሰጠች።
የቻይና አገር ደኅንነት ሚኒስቴር እንዳለው የውጭ አገር ሰላዮች አማላይ አካላዊ ውበት ያላቸውን ሰዎች ተጠቅመው ከቻይናውያን የአገር ምሥጢር እየወሰዱ ነው ብሏል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንዳለው አንድ ሊ ሲ የተባለ የቻይና ዜጋ ለሥራ በተጓዘበት አገር የምሽት መዝናኛ ቤት እንዲገባ ከተደረገ በኋላ የሌላ አገር ሰላዮች የስም ማጥፋት ማስፈራሪያ በመሰንዘር ምሥጢር አሳልፎ መስጠቱእን አመልክቷል።
ሚኒስቴሩ ለዜጎቹ ካስተላለፈው ማሳሰቢያ በተጨማሪ የውጭ አገር ሰላዮች ቻይና ውስጥ በስለላ ተግባር ተሳትፈው መያዛቸውን ገልጿል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ቤይጂንግን አንድ ዩናይትድ ኪንግደም ዜጋ ለአገሩ የደኅንነት ተቋም ኤምአይ6 ሲሰልል ቻይና በቁጥጥር ስር ማዋሏን ማሳወቋ ይታወሳል።
በቻይና ጉዳዮች ጥናቶችን የሚሠራው የካርኑጌ ቻይና ባልደረባ የሆኑት ኢያን ቾንግ ግን የደኅንነት ተቋሙ ይህን ማስጠንቀቂያ ሊያወጣ የቻለው የቻይና ባለሥልጣናት የውጭ አገራት የስለላ ተቋማት ስጋት ስለፈጠሩባቸው እንጂ በስለላ ዓለም አዲስ ነገር ተፈጥሮ አይደለም ይላሉ።
“ሰዎችን በማማለል የማጥመድ ስልት ከሌሎች ጊዜያት በበለጠ አሁን የተስፋፋ አይመስለኝም። የስለላ ሥራ የገንዘብ ጥማት፣ ፆታዊ ፍላጎት፣ ብስጭትንም ይሁን ችልተኝነት የሰው ልጆች ድክመት አካላ ሆኖ ኖሯል” በማለት ኢያን ቾንግ ይናገራሉ።
ሚኒስቴሩ ሊ የተባለው ግለሰብ በአንድ አስጎብኚ አማካይነት ወደ የምሽት መዝናኛ ስፍራ ካመራ በኋላ “ለምሽቱ በርካታ ሴቶችን እንዲመርጥ” ተጠይቋል።
ለቻይና መንግሥት ተቋም የሚሠራው ሊ በዚያ ምሽት ሲያደርገው የነበረው እንቅስቃሴ ክትትል እየተደረገበት እንደሆነ የተረዳው የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች ድንገት ወደ ነበረበት ክፍል ገብተው እርቃኑን ፎቶግራፍ ሲያነሱት ነው ብሏል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ።
ተቋሙ ይህ ክስተት በየትኛው አገር እንዲሁም መቼ እንደተፈጠረ ያለው ነገር የለም።
ሊ ፎቶግራፍ ያነሱት የውጭ አገር ሰላዮች የስለላ ተቋማቸውን የማይቀላቀል ከሆነ ፎቶግራፎቹን አደባባይ ላይ እንደሚያወጡት እንዳስፈራሩት ተገልጿል።
ሊ በፍርሃት የተለያዩ መረጃዎችን የያዘውን የሥራ ላፕቶፕ ከምፒዩተር አሳልፎ ሰጥቷል።
“በዚህ ሁኔታ የ10 ዓመታት ምሥጢር የያዘው ላፕቶፕ ኮምፒዩተር በሰላዮች እጅ ገብቷል።”
ሚኒስቴሩ ሊ ወደ ቻይና ከተመለሰም በኋላ በውጭ አገር ሰላዮቹ የሚደርስበት ጫና እና ማስፈራሪያ መቀጠሉን ገልጿል።
ግለሰቡ በአሁኑ ሰዓት በቁጥጥር ውሎ ዝርዝር የሆነ ጥብቅ ምርመራ እየተደረገበት እንደሆነም የደኅንነት ተቋሙ አመልክቷል።












