የስፔን ፖሊስ በውሃ ውስጥ አደንዛዥ ዕፅ የሚያዘዋውሩ ድሮኖችን ያዘ

የፎቶው ባለመብት, የስፔን ፖሊስ
የስፔን ፖሊስ በውሃ ውስጥ አደንዛዥ ዕፅን ለማዘዋወር ይጠቅማሉ ተብለው የተሰሩ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) መያዙን አስታውቋል።
ድሮኖቹ አደንዛዥ ዕፁን የሚያዘዋውሮት ከሞሮኮ እንደሆነም ተነግሯል።
ስም ያልተሰጣቸው እነዚህ ድሮኖች እስከ 200 ኪሎ ግራም ክብደት የመሸከም አቅም አላቸው። ይህንኑ በተመለከተ ፖሊስ 14 ወራትን ምርመራ ከደረገ በኋላ በካዲዝ፣ ማላጋ፣ እና ባርሴሎና ከተሞች ስምንት ሰዎችን አስሯል።
ይህም ድሮኖቹን የሚያመርተውንና ከእዚያም ለአከፋፋዮች በማስረከብ አደንዛዥ ዕፁ ወደ አውሮፓ እንዲገባ የሚያስችለውን የቡድኑን አስኳል በታትነዋል ብሏል።
የስፔን ፖሊስ ያለ ሰው እርዳታ መንቀሳቀስ የሚችሉና በባሕር ውስጥ መጓዝ ሚችሉ ድሮኖችን ሲያገኝ ይህ የመጀመሪያው መሆኑን ገልጿል።
“እነዚህ መሣሪያዎች አዘዋዋሪዎች ከፍተኛ መጠን ያለው አደንዛዥ ዕፅን ከርቀት በጅብራልታር በኩል ለማዘዋወር ይጠቅሟቸዋል” ብሏል ፖሊስ።
የጅብራልታር ወሽመጥ ሞሮኮን እና ስፔንን የሚያገናኝ ጠባብ መስመር ነው።
ከድሮኖቹ መካከል አንደኛዋ ሙሉ በሙሉ ተሰርታ ያለቀች ሲሆን ሁለቱ ደግሞ የተወሰነ የሚገጣጠም አካል የቀራቸው ናቸው።
ሁለቱ በሂደት ላይ የነበሩት ድሮኖች ለፈረንሳይ የዕፅ አዘዋዋሪ ቡድኖች ሊሰጡ የሚችሉ እና ምናልባትም ኮኬይን ሊያዘዋውሩ የሚችሉ እንደሆኑ ተገምቷል።
ፖሊስበመግለጫው14 ኪሎ ግራም ሃሺሽ፣ 8 ኪሎ ግራም ማሪዋና፣ ከ157 ሺህ በላይ ዩሮ እና ስድስት የቅኝት ድሮኖችን መያዙንም አስታውቋል።
ድሮኖቹ ጅፒኤስ የተገጠመላቸው ሲሆን ተቆጣጣሪዎቹ ከየትኛውም የዓለም ክፍል ሆነው ኢንተርኔት በተገጠመለት መሣሪያ እየተቆጣጠሯቸው ሊሆን ይችላል ተብሏል።
ከተጠርጣሪ ታሳሪዎቹ መካከል ሁለቱ አባትና ልጅ ሲሆኑ የአውሮፕላን አብራሪነት ፈቃድ ያላቸው ናቸው። ቡድኑ በአየር፣ በምድርና ውሃ ትራንስፖርት ላይ የተራቀቀ እውቀት ያላቸው ሰዎች ጥምረት ያለው ለመሆኑ የአባትና ልጁ የዕውቀት ደረጃ አንድ ማሳያ ተደርጓል።
በእነዚህ የትራንስፖርት አማራጮችም አደንዛዥ ዕፅን የሚያዘዋውሩ እና ዴንማርክ፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ እና ስፔን ለሚገኙ የወንጀል ቡድኖችም እነዚህን በቴክኖሎጂ የተራቀቁ የትራንስፖርት አማራጮች የሚያከፋፍል ነው የሚል ክስ ለቡድኑ ቀርቦበታል።
ፖሊሶቹ 13 የተለያዩ መኪናዎችንም ይዘዋል። መርማሪዎች በውሃ ውስጥ የሚጓዝ መኪና ሲይዙ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።
በእዚህ ዓመት ከፊል ሰርጓጅ የሆነ መርከብ 4 ቶን ኮኬይን ተሸክሞ ወደ ማዕከላዊ አሜሪካ ሲያመራ በኮሎምቢያ ፖሊስ ተይዟል።
የስፔን ፖሊስም ባለፈው ዓመት 9 ሜትር ርዝመት ያለው ሰርጓጅ ጀልባ በማላጋ ከተማ መጋዘን ውስጥ እንዳለ ይዟል።
ሞሮኮ ከፍተኛ ካናቢስ አምራች እና የስፔን ቅርብ ጎረቤት ነች። በተጨማሪም ስፔን ከፍተኛ ኮኬይን ከሚያመርቱት የደቡብ አሜሪካ የቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿ አገራት ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላት።
ይህ ተዳምሮ ስፔን ወደ አውሮፓ አደንዛዥ ዕፅ እንዲዘዋወር ትልቅ ጠቀሜታ አላት።
በተለይ 15 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለውና አፍሪካ እና አውሮፓን የሚለያየው የጅብራልታር ወሽመጥ ለአዘዋዋሪዎች ተመራጩ ነው።
ባለፈው ዓመት ፖሊስ ከ100 በላይ ሰዎችን በፈጣን ጀልባ ካናቢስ እኣሻገራችሁ ነው በማለት ከስሶ አስሯቸው ነበር።












