አሜሪካ በፍልስጤማዊቷ ጋዜጠኛ ግድያ ላይ የምርመራ ውጤቷን ይፋ አደረገች

 ሺረን አቡ አቅላ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ፍልስጤማዊቷ- አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ሺረን አቡ አቅላን የገደለው ጥይት መነሻው እስራኤል ወይስ ፍልስጥኤም ነው በሚለው ላይ አሜሪካ የምርመራ ውጤቷን ይፋ አደረገች።

በምርመራ ውጤቱ መሰረት ጋዜጠኛዋን የገደለው ጥይት በከፍተኛ ሁኔታ በመጎዳቱ ትክክለኛ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አልተቻለም ተብሏል።

ሆኖምየጋዜጠኛዋን ግድያ አስመልክቶ በሁለቱም ወገኖች የተደረጉ ምርምሮች ከእስራኤል ጦር በተተኮሰ ጥይት ሳትገደል አልቀረችም የሚል ድምዳሜ ላይ አሜሪካ ደርሳለች ። ጥይቱ ሆን ብሎ ሳይሆን ሳይታሰብ የተተኮሰም ነው ተብሏል።

የአንጋፋዋ አልጀዚራ ጋዜጠኛ ግድያ በአለም ላይ ከፍተኛ ድንጋጤ እና ቁጣን ፈጥሯል።

ፍልስጤማውያን ለግድያው እስራኤልን ጥፋተኛ ቢያደርጉም እስራኤል በበኩሏ አሁን ባለው ሁኔታ ጥፋተኝነቱን እስካሁን መወሰን አይቻልም ብላለች።

ጥይቱን ያስረከቡት ፍልስጤማውያን ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ እለት እየሩሳሌም ለሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ሲሆን እስራኤልም በዚህ ምርመራ እንድትገለል አጥብቀው ጠይቀዋል።

በእስራኤል ቁጥጥር ስር ባለችው ዌስት ባንክ ግዛት ባለችው ጄኒን የነበረውን የእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ ስትዘግብ ህይወቷ ያለፈውን አቡ አቅላን የገደለውን ጥይት ለመልቀቅ ፍልስጤማውያን በመጀመሪያ ፍቃደኛ አልነበረም።

እስራኤል ቀደም ሲል የገደላትን ወታደር መሳሪያ መለየቷን አስታውቃለች። ሆኖም የእስራኤል መከላከያ ሰኞ እለት እንዳስታወቀው ጥይቱ በመጎዳቱ የመሳሪያው ሁኔታ ሊታወቅ አልቻለም ተብሏል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ቢሮ እንዲሁም የዓይን እማኞች እና የጋዜጠኞች ምርመራ ለጋዜጠኛዋ ግድያ የእስራኤል ወታደሮች ተጠያቂ ናቸው የሚል ድምዳሜ ላይ ቢደርሱም እስራኤል በበኩሏ ፍልስጤማውያን ታጣቂዎች ከተጠያቂነት ነጻ ሊሆኑ አይገባም በሚል ትከራከራለች።