የኬንያ ምርጫ ውጤት ለምን ተፈራ? ውጤቱስ ምን ይዞ ይመጣል?

የፎቶው ባለመብት, AFP
ናይሮቢ ሰሞኑን ናይሮቢን አትመስልም። ከቀልቧ አይደለችም። እንደወትሮዋ ንቃት አይታይባትም።
ጠባብ ጎዳናዎቿ ሰፍተዋል። ተሸከርካሪዎች ቤት ሰንብተዋል። ሲቢዲ (CBD) የሚባለው የናይሮቢ ማዕከላዊ ክፍል የሆነውና በርካታ ሱቆች የሚገኙበት ቦታ ዝግ ነው። የሚታትሩት ነጋዴዎቿ ወደ ትውልድ መንደራቸው ገብተዋል።
በአገሬው ‘ቦዳ-ቦዳ’ የሚባሉት የዶቅዶቄ ሞተረኞች በብዛት በጎዳናዎች ሽው እልም ይላሉ።
እነርሱ ደግሞ በብዛት በወጣቶች የሚዘወሩ ናቸው። ወትሮም ስማቸውም በበጎ አይነሳም። አይበለውና ድኅረ ምርጫ ነውጥ ቢነሳ ሚናቸው ይጎላል።
ብቻ ሰሞኑን ናይሮቢ፣ ናይሮቢን አትመስልም፡፡
በዲፕሎማቲክ መዲናነት አዲስ አበባን የምትፎካከረዋን ከተማ አትመስልም።
ናይሮቢ የብዙ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ናት።
ኤምባሲዎች ዜጎቻቸውን፣ ተቋማት ሠራተኞቻቸውን አርፋችሁ ቤት ተቀመጡ ሲሉ መክረዋል።
ያለ ምክንያት አልሰጉም። የ2007 ቁስል አልጠገገም።
ያኔ ‘አትነሳም ወይ!’ ብለው ግጭት የቆሰቆሱት ፖለቲከኞች ናቸው ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ሲጠበቁ የምርጫ ዕጩዎች ሆነው የቀረቡት።
የኬንያ ምርጫ ቦርድ ከዛሬ ነገ ውጤት አሳውቃለሁ እያለ ሲምል እነሆ ዛሬ 6ኛ ቀኑ ነው።
ምናልባት ዛሬ (ሰኞ ከሰዓት) ውጤት ሊገለጽ ይችላል። ከነገ ወዲያ ለመዘግየት ግን ሕግ አይፈቅድለትም።
እጅግ ዘመናዊና ቀልጣፋ የተባለው የድምጽ አሰጣጥና ቆጠራ ለምን ዘገየ?
ከዓለም ምርጫ ሂደቶች እጅግ ውድ ከሚባሉት አንዱ የሆነው የኬንያ ምርጫ ውጤትስ ይህን ያህል ለምን አስጨነቀ?

የጎሣ አሰላለፍ
በዚህ ምርጫ ሁለቱ አውራዎች ራይላ ኦዲንጋና እና ዶክተር ዊሊያም ሩቶ ናቸው። ራይላ ከሉዎ፣ ሩቶ ከካሌንጂ ጎሣ ይመዘዛሉ።
በኬንያ ኪኩዩ ጎሣን ቸል ብሎ ምርጫ ማሸነፍ ፈተና ነው። ሁለቱም ፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎች ኪኩዩ ጎሣዎችን በተጣማሪ ተወዳዳሪነት ያሰለፉትም ለዚህ ሊሆን ይችላል።
በዚህ ምርጫ ራይላና ኦዲንጋ ብቻ አይደሉም ለፕሬዝዳንትነት ዕጩ ሆነው የቀረቡት።
እነሱን ያጀቡ ሁለት ሌሎች ዕጩዎችም አሉ። አንደኛው ፕሮፌሰር ሌላኛው ፓስተር ናቸው።
ስለ ፕሮፌሰሩ ትንሽ ብናወራ ይሻላል።
ፕሮፌሰር ዋጃኮያ ይባላሉ።
ነገረ ሥራቸው ቧልት ይበዛዋል። አገሬ ኬንያን እጸ ፋሪስ ነግዳ የዓለም ልዕለ ኃያል አደርጋታለሁ ብለው ሲዝቱ ከርመዋል።
ወጣቶች ካልሆኑ አብዛኛው ሕዝብ ከቁም ነገር አይወስዳቸውም።
እንዲያውም ፕሮፌሰሩ ለብዙዎች በአስጨናቂ የጎሣ ፖለቲካ ውስጥ የተወለዱ የሳቅ ምንጭ ናቸው።
ስድስት የሕግ ዲግሪዎችን ሰብስበዋል። ስለ ምጡቅነታቸው አውርተው አይጠግቡም። ማኅበራዊ ሚዲያው ከእርሳቸው ጋር በተሳሰሩ ቀልዶች የተሞላ ነው።
ኤልኤልቢ ዲግሪዎቻቸው ቁምሳጥን ጠቦታል። የዋዛ ዲግሪዎች አይደሉም ታዲያ።
ፖለቲከኞች ምርጫ ሲቃረብ አስቸኳይ ዲግሪ በውድ ዋጋ በሚሸምቱበት አገር እሳቸው ደረጃና ጥራቱን የጠበቀ ዲግሪ ይዘው ነው የቆዩት። ያውም ከአሜሪካና ከዩናይትድ ኪንግደም ዩኒቨርስቲዎች።
ድሮ የጎዳና ተዳዳሪ ነበርኩ ይላሉ። እጅግ አስቸጋሪ ሕይወት መርቻለሁ ይላሉ። ድህነትን ራሱ ስለእኔ ብትጠይቁት ይነግራችኋል ይላሉ። አፈር ልሼ ነው የተነሳሁት ይላሉ።
ስለዚህ ከድህነት መንጭቄ የማወጣችሁ እኔ እንጂ በቅንጦት ያደጉት እነ ኦዲንጋ አይደሉም ይላሉ።
“መንገዱስ?” ሲባሉ መጀመርያ የኬንያን ዕዳ እንክፈል ይላሉ።
“ዕዳውን እንዴት እንክፈል?” ሲባሉ የሚያቀርቡት ሐሳብ ግን ወለፈንዲ ነው።
በቅድሚያ ፕሬዝዳንት ስሆን ከናይሮቢ ወደ ሞምባሳ የሚሄደውና የባቡር ሐዲድ ነቃቂዬ ወዲያ እጥለዋለሁ ብለዋል።
ይሄ ሐዲድ ቢሊዮን ዶላር የተከሰከሰበት የኬንያ ውዱ መሠረተ ልማት ነው። ከባድ የቻይና ዕዳ አለበት። በደምሳሳው ካየን የአገሪቱ ሃብት ተሰብስቦ 62 ከመቶው ዕዳ ለመክፈል ነው የሚውለው። አገሪቱ እስከ አፍንጫዋ ነው በዕዳ የተነከረችው።
ይህ ፕሮፌሰሩን ብቻ ሳይሆን የኬንያን ሕዝብ የሚያቆስል እውነታ ነው።
ኬንያን ከተከመረባት የቻይና ዕዳ ለማላቀቅ ሁነኛ መላ ይዣለሁ የሚሉት ፕሮፌሰሩ የስንዴ ማሳን እያለማን አንጃጃል ነው የሚሉት።
ሻይ ቅጠል ማልማት የትም አያደርስም እመኑኝ ነው የሚሉት።
ይህን ቀልድ አቁመን ቶሎ ማሪዋና [ሃሺሽ] ዕጽ ተክለን ለዓለም እንሸጥ፤ እናንተ ብቻ ምረጡኝ፣ የብልጽግና ጎዳናን እኔ እመራችኋለሁ ነው የሚሉት።
እስከ አሁን ባለው ውጤት ከሚሊዮን ድምጾች የሺዎችን ድምጽ አግኝተዋል።
ካገኙት ድምጽ ይልቅ ያገኙት የቧልት ሰሌዳ ሚም (meme) ሳይበልጥ አይቀርም እያሉ ይሳለቁባቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Wajackoyah
የአሁኑ ምርጫ ውጤት ለምን አስፈሪ ሆነ?
አንደኛው ስጋት አራት ጊዜ ሞክረው ለ5ኛ ጊዜ እየተፎካከሩ ያሉት ራይላ ኦዲንጋ ቢሸነፉ ውጤቱን አሜን ብለው ይቀበላሉ ወይ የሚለው ጥያቄ ነው።
ኦዲንጋ በተሰናባቹ ኡሁሩ ኬንያታ መደገፋቸው ደግሞ ሌላ ፍርሃትን ፈጥሯል።
ሁለቱ ኃያላን ፖለቲከኞች ምክትል ፕሬዝዳት ሆነው ለቆዩት ዊሊያም ሩቶ ያላቸው አሉታዊ አመለካከት ነገሩን አስፈሪ አድርጎታል። እንካ ሰላንቲያቸው እስከ መዘላለፍ የሄደ ነበር።
ሁለተኛው ስጋት የኬንያ ምርጫ በአመዛኙ የጎሣ መስመርን የሚከተል መሆኑ ነው።
በአመዛኙ የፖለቲካና የምጣኔ ሃብት ቁጥጥር አላቸው የሚባሉት ኪኩዮዎች የእኩል ሥልጣን ተጋሪ አይደለንም ብለው ቅሬታ በገባቸው ሌሎች ጎሣ ፖለቲከኞች በበጎ አይታዩም።
ራይላ እና ሩቶ እስከ አሁን እያሳዩ ያሉት ውጤት የፖልቴርጋትንና የኃይሌ ገብረሥላሴን የሲድኒ 10ሺህ ትንቅንቅን የሚያስታውስ ነው።
ፖልቴርጋት በኃይሌ ሲበለጥ በብስጭት ክንዱን በኃይሌ ጀርባ ከመሰንዘር ያለፈ ነገር አላደረገም።
በዚህ ምርጫ ተሸናፊው መሸነፉን አምኖ ደጋፊዎቹን በሰላም ቤት ግቡ ይላል? ወይስ ክንዱን በተፎካካሪው ላይ ያነሳል የሚለው ነው አሁን አሳሳቢው ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጸሎት እና ፖለቲካ
ዕለተ እሁድ ለኬንያዊያን የማይዛነፍ የጸሎት ቀን ነው።
ታዲያ አብያተ ክርስቲያናት ከጌታ ቃል ጋር የፖለቲካ ቃልም ጣል ማድረጋቸው የነበረ ነው።
የብዙ አገሬው ጋዜጦች ቱባ የፖለቲካ ዜና ምንጭም የሰንበት ጸሎት የሆነው ለዚህ ነው።
ትናንት እሁድ ራይላ እና ሩቶ ጸሎት ላይ ነበሩ። በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት።
ራይላ በካረን ሰፈር ቅዱስ ፍራንሲስ ቤተ ክርስቲያን ጸሎት አድርሰዋል።
ሰላማዊ የድምጽ አሰጣጥ በመጠናቀቁ ጌታን አመስግነዋል።
ምርጫ ቦርድ ውጤት ከገለጸ በኋላም ሰላሙ እንዲቀጥል እግዚአብሔርን እማጸናለሁ ብለዋል።
ራይላ ኦዲንጋ በቅርቡ በነበራቸው አንድ ቅስቀሳ “እኛን ከሶማሊያና ከኢትዮጵያ…አታወዳድሩን” ሲሉ ነበር። እኛ የአገር ውስጥ ሰላም ያለን ሕዝቦች ነን ማለታቸው ነው በሚል ተተርጎሟል።
ወደነቀፏቸውን አገሮች ሸርተት እንደማይሉ ማረጋገጫ የለም።
ተቀናቃኛቸው ሩቶም ካረን ሰፈር በሚገኘው መኖርያ ቤታቸው ውስጥ ባስገነቡት ቤተ ክርስቲያን ከደጋፊዎቻቸው ጋር አምልከዋል።
እጃቸውን ወደ ሰማይ ዘርግተው “በሰላም ምርጫ ያስጀመርከን ልዑል እግዚአብሔር በሰላም አስጨርሰን” ብለዋል፤ ዐይናቸውን ጨፍነው።
ተርታው ሕዝብም አሜን ብሏል።
ችግሩ በኬንያ ፖለቲከኞች ዘንድ ጸሎት ማድረስና ነውጥ መቀስቀስ የሚፃረሩ ነገሮች አለመሆናቸው ነው። መሳ ለመሳ ያስኬዷቸዋል።
የቄሳርን ለቄሳር የሚሉ ፖለቲከኞች በኬንያ ገና አልተወለዱም።












