በጂቡቲ ባለው ከፍተኛ ሙቀት ምክንያት የሦስት ኢትዮጵያውያን ሕይወት አለፈ

ከጅቡቲ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ እየተመለሱ ያሉ የቦቴ መኪናዎች ተደርድረው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በጎረቤት አገር ጂቡቲ ባለው ከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ሦስት የከባድ መኪና አሽርካሪዎች እና የመኪና ጥገና ባለሙያ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ሕይወት እንዳለፈ የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር አስታወቀ።

ተሽከርካሪዎች የሚያጓጉዙት ጭነት ሳይደርስ ወደ ጅቡቲ ተጉዘው ለቀናት እንዲጠብቁ እየተደረገ መሆኑ ለሙቀት እና ለሌሎች ችግሮች እንዲጋለጡ እያደረጋቸው እንደሆነ የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ዘውዱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የወጪ እና ገቢ ምርቶች ዋነኛ በር ወደ ሆነችው ጂቡቲ የሚመላለሱ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች እና መቀመጫውን በአገሪቱ ያደረገ የጥገና ባለሙያ ሕይወታቸው ያለፈው፤ በሰኔ ወር መጀመሪያ በተከታታይ ቀናት ውስጥ እንደሆነ የማኅበሩ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዳመነ ተሾመ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሦስት የማኅበሩ አመራሮች ሕይወታቸው ካለፈው ግለሰቦች ውስጥ አንዱ በላይነህ ክንዴ የግል ትራንስፖርት አሽከርካሪ እንደሆነ እና ቀሪዎቹ ሁለት ግለሰቦች ደግሞ በመንግሥታዊ የልማት ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

ሕይወቱ ያለፈው የጥገና ባለሙያ የመንግሥታዊው የባሕር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ የሆነው ኢትዮጰያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሠራተኛ እና ሌላኛው አሽከርካሪ ደግሞ የአማራ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅት የሆነው ጥቁር አባይ ትራንስፖርት አሽከርካሪ እንደሆነ አመራሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጰያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ እንዲሁም በላይነህ ክንዴ የግል ትራንስፖርት የአሽከርካሪዎቹን ህልፈት ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በጂቡቲ ያለው ወቅታዊው የሙቀት ሁኔታ ከፍተኛ መሆኑን የሚናገሩት የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን፤ በአሁኑ ወቅት ያለው የአየር ሁኔታ አሽከርካሪዎች “ሊቋቋሙት የማይችሉት” እንደሆነ አስረድተዋል።

ጅቡቲ ወደብ ላይ የአፈር ማዳበሪያ የሚጭኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Shipping and Logistics

የምስሉ መግለጫ, ጅቡቲ የደረሰን የአፈር ማዳበሪያ ወደ ኢትዮጵያ ለማጓጓዝ እየጫኑ ያሉ ተሽከርካሪዎች

የአውሮፓውያኑ ሰኔ ወር የአየር ሁኔታ ትንበያ እንደሚያሳየው የጂቡቲ ከተማ ውስጥ የሚጠበቀው ከፍተኛ የሙቀት መጠን 37.9 ዲግሪ ሴሊሺየስ ነው። በዚሁ ተመሳሳይ ወር አዲስ አበባ ውስጥ የሚጠበቀው ከፍተኛ የሙቀት መጠን 21 ዲግሪ ሴሊሺየስ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር ሰኞ ሰኔ 10/2016 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እንዲሁም አሽከርካሪዎች ለሚያሰማሩ የነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች እና የደረቅ ጭነት ባለንብረቶች ማኅበር በጻፈው ደብዳቤ በጂቡቲ ያለው ሙቀት ለአሽከርካሪዎች ህልፈት ምክንያት መሆኑን ገልጿል።

በጂቡቲ ያለው ይህ የሙቀት መጠን እና አሽከርካሪዎች በአገሪቱ ከ10 ቀናት በላይ እየቆዩ መሆናቸውን ቢቢሲ የተመለከተው የማኅበሩ ደብዳቤ አመልክቶ፤ “አሽከርካሪዎች ከአስር ቀናት በላይ በመቆየታቸው በሙቀቱ ምክንያት ባለፉት 15 ቀናት ውስጥ ብቻ የአራት አሽከርካሪዎች ሕይወት ያለፈ መሆኑን ያገልጻል።

እንደ “ስኳር፣ ግፊት እና ልብ ድካም” ያሉ የጤና ችግሮች ያሉባቸው አሽከርካሪዎች “በመድኃኒት እጥረት አደጋ ላይ” እንደሆኑም በደብዳቤው ላይ ተጠቅሷል።

የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን እንደሚገልጹት የእነዚህ ችግሮች “መሠረታዊ” ምክንያት አሽከርካሪዎች “ኢትዮጵያ ውስጥ ጭነታቸውን አራግፈው እንደጨረሱ ትዕዛዝ ደረሰም አልደረሰም በቶሎ” ወደ ጂቡቲ እንዲመለሱ እየተደረጉ መሆኑ ነው።

አሽከርካሪዎቹ ጂቡቲ ከደረሱ በኋላ ጭነታቸው እስከሚመጣ እስከ 15 ቀናት እንደሚጠብቁ የሚናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ ይህም ለችግር እያጋለጣቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ከሞቱት አሽከርካሪዎች አንዱ የሆነው የበላይነህ ክንዴ የግል ትራንስፖርት አሽከርካሪ ጂቡቲ ውስጥ ሕይወቱ ያለፈው ነዳጅ ለመጫን ወረፋ ላይ እያለ መሆኑን የኩባንያው ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደሳለኝ ካሴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአሽከርካሪው ህልፈት ምክንያት “በሙቀት ነው አይደለም ለሚለው የሐኪም ማረጋገጫ” እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ ደሳለኝ፤ ጂቡቲ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ያለው የሙቀት መጠን “ከፍተኛ ደረጃ” ላይ መድረሱን ከአሽከርካሪዎች እንደሚሰሙ ገልጸዋል።

አቶ ደሳለኝ፤ “[የሞቱ መንስኤ] ሙቀት የመሆን ዕድል ይኖረዋል ብዬ ነው የማስበው። ምክንያቱም ሙቀቱ አሁን ያለው በመደበኛው ከሚጠበቀው በላይ ነው። ከእርሱ ጋር ተያያዥነት ይኑረው [ወይም] ተጓዳኝ ነገር ይኖረው ለማረጋገጥ የህክምና ሰርቲፊኬት ያስፈልጋል ” ብለዋል።

የኢትዮጰያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ተሽከርካሪ በጅቡቲ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Shipping and Logistics

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጰያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ተሽከርካሪ በጅቡቲ

መቀመጫውን በጂቡቲ ያደረገው የኢትዮጰያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ የመኪና ጥገና ባለሙያ ደግሞ ሕይወቱ ያለፈው፤ ምሽት ላይ በተኛበት እንደሆነ አንድ የተቋሙ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ምንም ዓይነት ህመም አልነበረውም የሚል ነገር ሰምቻለሁ። ቀን ሠርቶ ነው የዋለው። ማታ ገብቶ ተኛ፣ ጠዋት አልተነሳም” ሲሉ ሁኔታውን ገልጸዋል።

ምንጩ፤ ሠራተኛው ይኖርበት የነበረው ቤት ሙቀት ለመቀነስ የሚያግዙ እንደ የአየር ማቀዝቀዣ (ቬንትሌተር) ያሉ መሳሪያዎች “ያልነበረው መሆኑ” በሙቀት ሕይወቱ እንዲያልፍ ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር ተናግረዋል።

የአማራ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅት በሆነው ንጋት ኮርፖሬት ስር የሚገኘው ጥቁር አባይ ትራንስፖርት አሽከርካሪ የሆነው ግለሰብ ሕይወቱ ያለፈው ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ጉዞ ከጀመረ በኋላ ከጅቡቲ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሆነ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር አስተባባሪው አቶ ዳመነ ገልጸዋል።

“ከጂቡቲ ወደ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሲደርስ ‘ደከመኝ’ ብሎ መኪናው ውስጥ ተኛ፤ በዚያው አረፈ። ተጠባባቂ ህመም ሊኖር ይችላል” ሲሉ ክስተቱን አስረድተዋል። ቢቢሲ ስለ ጉዳዩ ከጥቁር አባይ ትራንስፖርት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረጋቸው ተደጋጋሚ ጥረቶች አልተሳኩም።

የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር በጻፈው ደብዳቤ፤ “አሽከርካሪዎች ጂቡቲ የሚጭኑበት ቀን መረጃ ሲደርሳቸው እንዲንቀሳቀሱ” ማድረግ ሙቀትን ጨምሮ አሽከርካሪዎች ለሚገጥሟቸው ሌሎች ችግሮች መፍትሔ መሆኑን ጠቅሷል።

የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞንም፤ “አሽከርካሪዎች ጂቡቲ ከመድረሳቸው በፊት ባሉ የድንበር ቦታዎች ላይ እንዲያርፉ እና ትዕዛዝ ሲደርሳቸው ብቻ እንዲሄዱ ማድረግ” መፍትሔ መሆኑን በማንሳት ሃሳቡን ያጠናክራሉ። ማኅበሩ፤ ይህንን በተመለከተ አሽከርካሪዎችን ከሚያሰማሩ ኩባንያዎች ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።