የሞስኮ አየር ማረፊያ በረራዎች በድሮን ጥቃት ተስተጓጎሉ

ዩክሬን በሞስኮ በሰው አልባ አውሮፕላኖች (በድሮን) የታገዘ ጥቀት መፈጸሟን የሩስያ የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በዚህም ጥቃት ምክንያት ከሞስኮ ቩኑኮቮ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ይነሱ የነበሩ በረራዎች አቅጣጫ እንዲቀይሩ መደረጉ ተገልጿል።

በዛሬው ጥቃት አምስት ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ ውለዋል ተብሏል። ጥቃቱ በዋና ከተማዋ ዙሪ ያሉ መጠነ ሰፊ አካባቢዎችንም ኢላማ ማድረጋቸው ተነግሯል።

የሩስያ የመከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ሁሉም ሰው አልባ አውሮፕላኖች ተመትተው መውደቃቸውንና ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱን ነው።

ዩክሬን በድሮን ተፈጸመ ለተባለው ጥቃት ኃላፊነቱን አልወሰደችም።

ከሞስኮ ሶስት ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያዎች አንዱ በሆነው በቩኖኮቮ አየር ማረፊያ ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳም በአሁኑ ወቅት መነሳቱም ተገልጿል።

አውሮፕላኖቹ አቅጣጫ እንዲቀይሩ በመደረጉም ከቱርክ፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ከግብጽ የተነሱ በረራዎች ተስተጓጉለዋል ተብሏል።

እንደ ሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር ከሆነ በሞስኮ የአየር ቀጠና ስር እየበረሩ ከነበሩት ሰው አልባ አውሮፕላኖች መካከል አራቱ በአየር መቃወሚያ ተመትተዋል።

አምስተኛው ከመከስከሱ በፊት በኤሌክትሮኒክ መንገድ እንዲከሽፍ መደረጉን ነው።

“የኪየቭ መንግሥት ዓለም አቀፍ በራራዎችን የሚያስተናግድ አየር ማረፊያን ጨምሮ የሲቪል መሰረተ ልማት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ለመፈጸም ያደረገው ሙከራ አዲስ የሽብር ተግባር ነው” ሲሉ የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ በቴሌግራም ላይ አስፍረዋል።

በቴሌግራም የወጡ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እንዳሳዩት ከድሮኖቹ አንዱ ወይም ቁርጥራጮቹ በክሪቮሼይኖ ግዛት ውስጥ ባለ ህንጻ ላይ መውደቁን ነው። ህንጻውም በእሳት ተያይይዟል።

ከከተማዋ በስተደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በሚገኘውና ከቩኖኮቭ አየር ማረፊያ በ36 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ኩቢንካ ግዛት ውስጥ ሌላ ሰው አልባ አውሮፕላን መከስከሱን የሃገሪቱ የመንግሥት ሚዲያ ዘግቧል።

ቢቢሲ ይህንን መረጃ በግል ለማጣራት ሙከራ እያደረገ ይገኛል።