ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ለነጭ ተማሪዎች በማዳላት ክስ ቀረበበት
ስመ ጥሩው የአሜሪካው ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ በአብዛኛው ለነጭ ተማሪዎች አዳልቶ ቅድሚያ በመስጠት ክስ ቀረበበት።
ከዩኒቨርስቲው ጋር የቀደመ ትስስርና ግንኙነት ላላቸው ቤተሰቦች ያዳላል የሚል ህጋዊ መከራከሪያዎች ቀርበውበታል።
በተለይም ይህ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በዩኒቨርስቲው ለመማር በሚያመለክቱ ተማሪዎች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ መንጸባረቁም ተመልክቷል።
ተሟጋች ቡድኖች የአይቪ ሊግ ዩኒቨርስቲው በውርስ የሚተላለፍ የቅበላ ስርዓትን እንዲያስወግድ ለመንግሥት ፊርማ በማሰባሰብ ጠይቀዋል።
የሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ፖሊሲ ለነጮች እና ሃብታሞች መሳሪያነት በማገልገልም ሲፈረጅ ቆይቷል።
ይህ ቅሬታ የተሰማው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሃርቫርድ እና ሌሎች የአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች ዘርን መሰረት ያደረገ ቅበላን እንደ ቁልፍ ጉዳይ ለመመዘኛነት እንዳያውሉ ከወሰነ ከቀናት በኋላ ነው።
ሐሙስ እለት የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለአስርት አመታት የቆየውን አፈርማቲቭ አክሽን የተባለውን እርምጃም 6 ለ3 በሆነ ድምጽ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ ሽሮታል።
አፈርማቲቭ አክሽን በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ያለውን ብዝኃነት ለመጨመርና እና የተጎዱ ማህበረሰቦችንም ከፍ ለማድረግ ጠቃሚ ፖሊሲ እንደሆነም በርካቶች ሲከራከሩ ቆይተዋል።
ነገር ግን ዋና ዳኛ ጆን ሮበርትስ ሃርቫርድ እና ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች የሚጠቀሙበት ሂደት “አሸናፊዎችን እና ተሸናፊዎችን የሚመርጡት በቆዳ ቀለማቸው ነው” ሲሉም አስተያየታቸውን አስፍረዋል።
በዚህ ውሳኔም በመነሳሳት በቦስተን መቀመጫውን ያደረገ ለትርፍ ያልተቋቋመ የህግ ባለሙያዎች ቡድን ሰኞ እለት በሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ላይ የፌደራል የሲቪል መብቶች ቅሬታን አቅርቧል።
ዩኒቨርስቲው “በመቶዎች ለሚቆጠሩ በአብዛኛው ለነጭ ተማሪዎች ልዩ ቅበላ ያደርጋል። እነዚህ ተማሪዎች ያከናወኗቸው ነገሮች ኖረው ሳይሆን ይልቁንም በቤተሰቦቻቸውና በዘመዶቻቸው ማንነትና ከነሱ ጋር ባላቸው ግንኙነት ነው” ሲልም ቅሬታው አትቷል።
ቅሬታው የቀረበው በሲቪል መብቶች ህግ የሰፈሩ አንቀጽንም በመተላለፍ ለትምህርት ዲፓርትመንት ሲቪል መብቶች ቀርዘቧል።
ሃርቫርድ በጉዳዩ ላይ የሰጠው አስተያየት የለም።