ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፌስቡክ ባለቤት ሜታ እንደ ትዊተር ያለ አዲስ ማሕበራዊ ሚዲያ ሐሙስ ይፋ ሊያደርግ ነው
የፌስቡክ ባለቤት የሆነው ሜታ፤ ትዊተር የተሰኘውን መተግበሪያ የሚቀናቀን ማሕበራዊ ሚዲያ ሐሙስ ይፋ ያደርጋል።
ትሬድስ የሚል ስም የተሰጠው መተግበሪያ ለአይፎን ተጠቃሚዎች ቀድሞ የሚቀርብ ሲሆን ከኢንስታግራም ጋር የሚገናኝ እንደሆነ ተገልጧል።
ሜታ አዲሱን ማሕበራዊ ሚዲያ “ፅሑፍን መሠረት ያደረገ የመወያያ መድረክ” ብሎታል።
መተግበሪያው ይፋ ከመሆኑ በፊት የወጡ ፎቶዎች እንደሚያሳዩት አዲሱ መተግበሪያ ትዊተርን የመሰለ ነው።
የሜታው አለቃ ማርክ ዛከርበርግና የትዊተር ባለቤት ኢላን መስክ ፉክክራቸው ቀጥሏል።
ሁለቱ ልጥጥ ቱጃሮች ባለፈው ወር በቡጢ ይዋጣልን ብለው ቀጠሮ ቢይዙም አሁን አሁን ጭጭ ማለት አብዝተዋል።
አዲሱን መተግበሪያው የተመለከተው ኢላን መስክ “ፈጣሪ ይመስገን ይህን የሚመራው ጤናማ ሰው ነው” ሲል ዛከርበርግን በነገር ሸንቆጥ አድርጓል።
በተያያዘ የቴክኖሎጂ ዜና ትዊተርዴክ የተሰኘው የትዊተር መረጃ መሰብሰቢያ መድረክ ከሚቀጥለው ወር በኋላ ክፍያ እንደሚጠይቅ ተሰምቷል።
ይህ እርምጃ መስክ ተጠቃሚዎች ሰማያዊ እርማት እንዲያገኙ ለማስገደድ ያደረገው እንደሆነ ተገምቷል።
ሰማያዊ እርማት [ትዊተር ብሉ] ማለት ተጠቃሚዎች በወር 8 ዶላር ሲከፍሉ የሚያገኙት ‘ቬሪፊኬሽን’ (ማረጋገጫ) ነው።
ባለፈው ቅዳሜ ቢሊየነሩ ከዚህ በኋላ ተጠቃሚዎች በከፈሉት መጠን ነው የሰዎችን ‘ትዊት’ ማየት የሚችሉት ሲል አነጋጋሪ ሕግ አውጥቶ ነበር።
ትሬድስ የተሰኘው አዲሱ መተግበሪያው ማንኛውም ሰው በነፃ ሊጠቀመው የሚችል ይመስላል።
ሰዎች እዚህ ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ እንዳሻቸው ያለምንም ገደብ መለጠፍ እንደሚችሉም ተገልጧል። “ትሬድስ ማለት ማሕበረሰቡ ያሻውን ርዕስ እያነሳ ስለዛሬና ነገ አነጋጋሪ ጉዳዮች የሚወያይበት ነው” ይላል የመተግበሪያው መግለጫ።
የሜታ ሥሪት የሆነው ትሬድስ ከስልክዎ መረጃ ይወስዳል፤ ያሉበትን ቦታ ያጣራል፤ የገዙትንና በይነ መረብ ላይ የፈለጉትን ማየት ይችላል።
ባለፉት ዓመታት ትዊተርን መስለው የቀረቡ በርካታ ማሕበራዊ ድር አምባዎች ሳይሳካላቸው ቀልጠዋል።
ለምሳሌ ዶናልድ ትራምፕ የፈጠሩት ትሩዝ ሶሻልን መጥቀስ ይቻላል።
ሌላኛው የትዊተር ተቀናቃኝ ሆኖ የመጣው ብሉስካይ ነው። ባለፈው ቅዳሜ ኢላን መስክ የሰዎችን አጠቃቀም ሲገድብ በርካታ ሰዎች ወደ ብሉስካይ አቅንተው ነበር።
ነገር ግን ትሬድስ የተሰኘው አዲሱ የዛከርበርግ ምርት ትዊተር በእጅጉ የሚቀናቀን ሊሆን እንደሚችል ግምት አለ።
ማርክ ዛከርበርግ የሌሎች ኩባንያዎችን ምርት አስመስሎ በመሥራት ስኬታማ ነው።
ሪል የተሰኘው ቴክኖሎጂ ከቲክቶክ እንደተቀዳ ብዙዎች ያምናሉ። ስቶሪ [ፌስቡክ ስቶሪ፤ ኢንስታግራም ስቶሪ. . . ] ደግሞ ስናፕቻትን ይመስላል ሲሉ ያሙታል።
ሜታ ከትዊተር ጋር ለመፎካከር አቅም አለው።
ትሬድስ የተሰኘው አዲሱ ሥሪት ከኢንስታግራም ጋር የሚገናኝ ስለሆነ ከዜሮ አይደለም የሚጀምረው።