ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ ተጨማሪ የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ለመስጠት ጥሪ አቀረበች
የኢትዮጵያ ቴሌኮምዩኒኬሽን ባለሥልጣን በአገሪቱ የቴሌኮም አገልግሎት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ተቋማት ፍላጎታቸውን እንዲያሳውቁ ጥሪ አቀረበ።
ኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍን ለግል እና ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ለማድረግ ከዓመታት በፊት በወሰነችው መሠረት በመንግሥታዊው ኢትዮቴሌኮም በብቸኝነት ተይዞ የነበረውን ዘርፉን ክፍት ማድረጓ ይታወሳል።
በዚህም መሠረት በሳፋሪኮም የሚመራው “ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ” የተሰኘው የኩባንያዎች ጥምረት የመጀመሪያውን ፈቃድ አግኝቶ ባለፈው ዓመት የቴሌኮም አግልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወቃል።
የአገሪቱ የቴሌኮምዩኒኬሽን ባለሥልጣን ከሳፋሪኮም ቀጥሎ አገር አቀፍ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢነት በኢትዮጵያ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርቧል።
ባለሥልጣኑ አርብ ሰኔ 23/2015 ዓ.ም. በይፋ ባቀረበው ጥሪ ላይ ኩባንያዎች በዘርፉ ለመሰማራት ብቁ መሆናቸውን የሚያሳይ ጥያቄያቸውን እስከሚቀጥለው ዓመት መስከረም ወር መጀመሪያ ሳምንት ድረስ እንዲያቀርቡ ጋብዟል።
ጥሪ የቀረበላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ በቴሌኮም አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ በመላው አገሪቱ ሙሉ የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸው ተጠቅሷል።
ኢትዮጵያ የቴሌኮሙን ዘርፍ ለውድድር ክፍት ስታደርግ በመጀመሪያ ላይ ሁለት ፈቃዶችን ለመስጠት አቅዳ የነበረ ሲሆን፣ ከሳፋሪኮም ባሻገር ባለሥልጣኑ በሚፈልገው ሁኔታ ተፎካካሪ የሆነ ኩባንያ ባለማግኘቱ ሁለተኛውን ፈቃድ አዘግይቶት ቆይቷል።
በተጨማሪም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለውን የግዙፉን ኢትዮ ቴሌኮም የተወሰነ ድርሻ ለግል ባለሃብቶች ለማስተላለፍ የነበረውን እቅድም አዘግይቶት እንደነበር ይታወሳል።
በኢትዮጵያ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የቴሌኮም ዘርፍን ተቆጣጥሮ የቆየው ኢትዮ ቴሌኮምን ለመፎካከር ወደ ኢትዮጵያ ገበያ የገባው ሳፋሪኮም አገልግሎት መስጠት የጀመረው በቅርቡ ሲሆን፣ አገልግሎቱን በማስፋፋት ላይ ይገኛል።
ባለፈው ግንቦት ወርም ሳፋሪኮም ኤምፔሳ የሚባለውን የሞባይል የገንዘብ ዝውውር አገልግሎቱን በኢትዮጵያ እንዲሰጥ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ተሰጥቶታል።
ኢትዮጵያ ከ125 ዓመታት በላይ በመንግሥት በብቸኝነት ተይዞ የነበረውን የቴሌኮም ዘርፍ ክፍት በማድረግ የመጀመሪያውን የቴሌኮም ፈቃድ የሰጠችው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር።
በኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ ለመሰማራት በተደረገው ዓለም አቀፍ ጨረታ በኬንያው ሳፋሪኮም የሚመራው ጥምረት በ850 ሚሊዮን ዶላር ማሸነፉ ይታወሳል።
ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ የተሰኘው ይህ ጥምረት በዘርፉ አሉ የሚባሉ ስመ ጥር የቴሌኮም ኩባንያዎችን እና ተቋማትን በቅንጅት የያዘ ሲሆን፣ እነዚህም ሳፋሪኮም፣ ቮዳኮም ግሩፕ፣ ቮዳፎን ግሩፕና ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽን እንዲሁም ሲዲሲ ግሩፕ የተካተቱበት ነው።
ዋነኛው የአገሪቱ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ኢትዮ ቴሌኮም 40 በመቶ ድርሻውን ለውጭ ባለሀብቶች፣ 5 በመቶውን ለኢትዮጵያውያን እና 55 በመቶውን በመንግሥት ይዞታ ይቀጥላል ተብሎ ነበር።
ከሳፋሪኮም ከሚመራው ጥምረት በተጨማሪ በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ለመግባት የሚያስችል ሁለተኛ ፈቃድ እንደሚሰጥ መንግሥት ባሳወቀው መሠረት ነው አሁን ፍላጎት ላላቸው ኩባንያዎች ጥሪ የቀረበው።