ቴክኖሎጂ፡ የሞባይል ኔትዎርክ የመጨረሻው ቴክኖሎጂ 5ጂ ለኢትዮጵያ ምን ይፈይዳል?

ኢትዮጵያ ትናንት አምስተኛውን ትውልድ [5ጂ] የሞባይል ኔትዎርክን ወደ ሥራ አስገብታለች።

5ኛው ትውልድ ወይም 5ጂ ዓለም የደረሰበት የመጨረሻው ፈጣን የሞባይል ኔትዎርክ ቴክኖሎጂ ነው።

"የመጨረሻው ፈጣን" ማለት 2 ሰዓት የሚፈጅ ፊልምን በሰከንዶች ውስጥ ማውረድ [ዳውን ሎድ] ማድረግ የሚያስችል ነው። ትናንት በኢትዮጵያ ወደ ሥራ የገባው ይህ ቴክኖሎጂ፣ ለቅድመ ገበያ [ለማስተዋወቅ] በአዲስ አበባ በተመረጡ አካባቢዎች ላይ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

የቅድመ ገበያ አገልግሎቱ በወዳጅነት አደባባይ፣ በአንድነት ፓርክ፣ ቸርቸል ጎዳና እና በፖስታ ቤት አካባቢ "የ5ጂ ዞን" በሚል አግልግሎት መስጠት መጀመሩን በኢትዮ ቴሌኮም የቴክኖሎጂ ኃላፊ የሆኑት ታሪኩ ደምሴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኃላፊው እንዳሉት ይህ አገልግሎት በአንድ ዓመት ውስጥ ከቅድመ ገበያ ወደ ሙሉ አግልግሎት የሚገባ ሲሆን፣ አሁን ያሉት 6 የአገልግሎት ጣቢያዎች በአዲስ አበባ እና በክልሎች "በሚኖረው ፍላጎት" መሠረት በአንድ ዓመት ውስጥ ወደ 150 ያድጋሉ።

አካባቢዎቹ "ሕዝብ በብዛት የሚንቀሳቀስባቸውና ከፍተኛ የሞባይል ዳታ የመጠቀም ፍላጎት ያለባቸው ስለሆኑ" ለዚህ አገልግሎት መመረጣቸውን ኃላፊው አስረድተዋል።

አሁን ላይ ወደ ሥራ በገቡት ስድስት ጣቢያዎች አማካኝነት በአንድ ጊዜ እስከ 30 ሺህ ሰው አገልግሎት ሊያገኝ እንደሚችልም ኃላፊው ጠቅሰዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞቹ አገልግሎታቸውን በዲጂታል እንዲያደርጉ ለማስቻል፣ ምርታማነትን ለማሳደግ እና የቴሌኮም አገልግሎት ላይ ያላቸውን ተሞክሮ በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ በሚል የ4 ጂ ኤልቲኢ ኢንተርኔት አገልግሎት በአዲስ አበባ የጀመረው እአአ በ2015 ነበር።

ከዚያም ወደተለያዩ አካባቢዎች በማስፋፋት አገልገሎት እየሰጠ ይገኛል።

የቴክኖሎጂ ኃላፊው የ5ጂ አገልግሎትን ለማግኘት ቴሌኮሞች ከሚዘረጉት ኔትዎርክ ባሻገር ኔትዎርኩን የሚደገፍ የቴክኖሎጂ ቁሶች እንደሚያስፈልግ በመግለጽ፣ "አገልግሎትን መሠረት ያደረገ" ክፍያ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።

አቶ ታሪኩ፣ ይህን አገልግሎት ወደ ሙከራ ትግበራ ለማስገባት ከወር ያነሰ ጊዜ እንደፈጀ እና "ከ4ጂ እና 4ጂ አድቫንስድ ከሁለት እስከ ሦስት እጥፍ የሚሆን ወጪ እንዳስወጣ" ተናግረዋል።

5ጂ ለኢትዮጵያ ምን ይፈይዳል?

ኢትዮጵያ "ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት በከፍተኛ ሩጫ ላይ ያለች አገር ናት" ያሉት ኃላፊው፣ ይህንን አላማ ለማሳካት ደግሞ 5ጂ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ይህ አገልግሎት የርቀት ሕክምና ወይም ቴሌሜዲስንን ለማስፋፋት፣ ሰፋፊ እርሻዎችን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ፣ የማዕድን ዘርፉን በቴክኖሊጂ ለማጎልበት እና ኢንዱስትሪን ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

በዚህም መነሻነት አሁን ላይ ኢትዮጵያ የ2ጂ ኔትዎርክ ዝርጋትን በመግታት በ3ጂ፣ 4ጂ፣ 4ጂ አድቫንስድ እና በአዲሱ 5ጂ ላይ እየሠራች እንደሆነም ኃላፊው ገልጸዋል።

እንደ ኃላፊው ከሆነ 66 በመቶ የአገሪቱ አካባቢ በ3ጂ ቴክኖሎጂ የተሸፈነ ሲሆን 4ጂ እና 4ጂ አድቫንስድ 136 ከተሞችን ተደራሽ አድርጓል።

ይሁን እንጂ አዲሱና የመጨረሻው ቴክኖሎጂ 5ጂ ፈጣን አገልግሎት ይሰጣል በሚል ቢሞገስም፤ የአውሮፕላን የግንኙነት ሥርዓትን ይረብሻል የሚል ትችት ይቀርብበታል። ታላላቅ አየር መንገዶችም ሲቃወሙት ተስተውሏል።

ባለፈው ጥር ወር ላይ የአሜሪካ ግዙፍ 10 አየር መንገዶች 5ጂ (አምስተኛው ትውልድ) የሞባይል ኔትዎርክ በበረራዎች ላይ "ጉልህ የሆነ መስተጓጎል" ይፈጥራል ሲሉ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።

አየር መንገዶቹ የቴሌኮም አግልግሎት አቅራቢዎች ከአየር ማረፊያዎች ቢያንስ በ3 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ የ5ጂ ኔትዎርክ አገልግሎት እንዳይኖር ጠይቀዋል።

አየር መንገዶቹ 5ጂ ኢንተርኔት አገልግሎት በተለይ በአስቸጋሪ የአየር ጠባይ ውስጥ የአውሮፕላን በረራ ሥርዓትን ያውካል የሚል ስጋት አላቸው።

ታዲያ ይህ ጉዳይ ለኢትዮጵያስ ስጋት አይሆንም ወይ? ስንል በኢትዮ ቴልኮም የቴክኖሎጂ ኃላፊው አቶ ታሪኩ ጥያቄ አቅርበንላቸው ነበር።

አቶ ታሪኩ እንደሚሉት ቴክኖሎጂውን ለመጀመር ሲያስቡ ይህንን ግምት ውስጥ አስገብተዋል።

"አሜሪካ አካባቢ በበረራ ወቅት በአውሮፕላን እና መሬት መካከል ለመገናኘት የሚጠቀሙበትና የ5ጂ ኔትዎርክን የሚጠቀሙበት ፍሪኩዌንሲ የተቀራረበ በመሆኑ በደንብ መጠናት አለበት የሚል ነገር አለ። እኛ ግን እየተጠቀምነበት ያለው ሎወር ባንዱን ነው። በመሆኑም ይህ ስጋት እንዳልሆነ በኛ በኩል በደንብ አይተነዋል። ከአየር መንገዶችም ጋር ውይይት እያደረግን እየተግባባን ነው" ሲሉ አስረድተዋል።

5ጂ እጅግ ዘመናዊና ፈጣን የሆነ የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ብዙዎች እየተጠቀሙበት ካለው የ4ጂ ኢንተርኔት 5ጂ በሃያ እጥፍ ገደማ የፈጠነ እንደሆነ ይነገራል።

ኖሎጂው እንዴት ነው የሚሠራው?

ራድዮ ስፔክትረም የተሰኘ አዲስ ቴክኖሎጂን የሚጠቀመው 5ጂ መጀመሪያ ጥቅም ላይ የሚውለው በኔትዎርክ አቅራቢ ድርጅቶች ነው። ድርጅቶቹ ይህን የሚያደርጉት አሁን ከፍተኛ ፍጥነት ያለውን 4ጂ ኢንተርኔት ለማበልፀግ እንዲረዳቸው ነው።

የ5ጂ ፍጥነት እንደሚጠቀሙት ስፔክትረም እንዲሁም እንደ ሞባይል ኔትዎርክ አቅራቢዎች ይለያያል። ሞባይል ኔትዎርክ የሚያቀርብልዎ ድርጅት በርካታ ማስተላለፊያዎችን የመትከል አቅም ካለው የተሻለ ኢንተርኔት ይኖርዎታል ማለት ነው።

ነገር ግን ይህን ቴክኖሎጂ ለመዘርጋት የሚወጣው ወጪ ቀላል የሚባል ስላልሆነ ኔትዎርክ አቅራቢ ድርጅቶች ፈተና ሊገጥማቸው እንደሚችል እሙን ነው።

ፍጥነቱ ምን ያል ነው?

በአሁኑ ወቅት ብዙዎች በይነ መረብን የሚዘውሩበት 4ጂ ኢንተርኔት በአማካይ በሰከንድ 45 ሜጋባይት ዳታ ያሽከርክራል።

ነገር ግን 4ጂ በዚህ ብቻ ሳይገደብ በሰከንድ እስከ 1 ጂቢ [1 ሺህ ሜጋባይት] ኢንተርኔት ለማቅረብ አቅም እንዳለው ይነገራል።

5ጂ ይህንን የኢንተርኔት ፍጥነት እስከ 10 እጥፍ ሊያደርሰው ይችላል። በሌላ አባባል ኢንተርኔትን ለመዳሰስ አሊያም ፋይል ለማውረድ አሁን ከሚጠቀሙት ፍጥነት እስከ 20 እጥፍ የተቀላጠፈ ይሆናል ማለት ነው።

በዚህ ፍጥነት በከፍተኛ ጥራት የተሠራን አንድ ፊልም በአንድ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከበይነ መረብ ሊያወርዱ ይችላሉ።

ይህ ፍጥነት እውን የሚሆነው ኔትዎርክ አቅራቢ ድርጅቶች የኮርና ራድዮ ኔትዎርኮች በ5ጂ ቴክኖሎጂ እንዲሠሩ ማድረግ ሲችሉ ነው።

5ጂ ለምን ያስፈልገናል?

ዓለማችን የተንቀሳቃሽ ቴክኖሎጂዎች ዓለም እየሆነች ነው። ሰዎች ከዓመት ዓመት የሚጠቀሙት ዳታም እያሻቀበ ነው።

በተለይ ደግሞ የተንቀሳቃሽ ምስሎች ተወዳጅነት እንዲሁም አዝናኝና መረጃ ሰጪ ዘገባዎች በቀጥታ መተላለፋቸው የተሻለ ኢንተርኔትን የሚጠይቁ ናቸው።

አሁን ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ የራድዮ ስፔክትረሞች እየተጨናነቁ ነው። በተለይ ደግሞ በርካታ ሰዎች በአንድ ቦታ በተመሳሳይ ሰዓት ኔትዎርክ ለማግኘት ሲጥሩ ቴክኖሎጂው ይጨናነቃል።

5ጂ፤ ተንቀሳቃሽ ቴክኖሎጂዎችን፣ የደኅንነት ካሜራዎችን እንዲሁም የመንገድ መብራቶች በአንድ ጊዜ በርካታ ሰዎች እንዲጠቀሙበት ያስችላል።