ስልክዎ የአውሮፕላን በረራን ሊያስተጓጉል እንደሚችል ያውቃሉ?

ዐሥር ግዙፍ የአሜሪካ አየር መንገዶች 5ጂ የበይነ መረብ ግንኙነት አገልግሎት የሚያስከትለው መጻኢ አደጋ ከወዲሁ አሳስቦናል ሲሉ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።

እነዚህ አየር መንገዶች ያሳሰባቸው የ5ጂ ኢንተርኔት ሥርጭት በአቪየሽን ኢንዱስትሪ ላይ ሊያስከትል የሚችለው ደኅንነት ተኮር ጣጣ ነው።

እነዚህ አየር መንገዶች "5ጂ ሥራ ሲጀመር በሺህ የሚቆጠሩ በረራዎች በቀላሉ ሊስተጓጉል ይችላል" ሲሉ ከባድ ማስጠንቀቂያ አስነግረዋል።

ይህ ብቻም ሳይሆን በርካታ የአየር መንገዶች በዚህ ቴክኖሎጂ የተነሳ ከሥራ ውጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ አሳስበዋል።

5ጂ እንዴት የአሜሪካንን የአየር መንገድ አገልግሎት ሊያቃውስ ይችላል?

5ጂ ኢንተርኔት የራዲዮ ሲግናልን ይጠቀማል።

በአሜሪካ 5ጂ የሚጠቀመው የራዲዮ ፍሪኩውንሲ ሲ-ባንድ በሚባለው ሞገድ ክልል የሚጠቃለል ነው።

ይህ ፍሪኩውንሲ ደግሞ አውሮፕላኖች ከሚጠቀሙት ራዲዮ አልቲሜተርስ ጋር ተመሳሳይ ነው።

አልቲሜተርስ ደግሞ አውሮፕላኖች ከመሬት በምን ያክል ከፍታ እንዳሉ የሚጠቁምና ሌሎች የበረራ የደኅንነት መረጃዎችን የሚያቅብል ነው።

የአልቲሜተርስ ፍሪኩዋንሲም በዚሁ 5ጂ በሚጠቀመው ፍሪከውንሲ የሚጠቃለል ነው።

የአየር መንገዶቹ ስጋት የሚመነጨውም ከዚሁ ነው።

5ጂ የመረጃ ቅብብሎሹ በአውሮፕላኖች የደኅንነት መረጃ ማቀበያ ቅብብሎሽ ጋር ስለሚጣረስ በርካታ አውሮፕላኖች በግድ እንዲያርፉ ሊያደርጋቸው ይችላል።

እአአ በ2020 መጨረሻ ለአቪየሽን የቴክኒካል መመሪያ የሚያቀርበው የአሜሪካው አርቲሲኤ ድርጅት በዚሁ ጉዳይ ላይ አንድ ጥናት አሳትሞ ነበር።

ድርጅቱ እንዳለው በመጪዎቹ ጊዜያት በአቪየሽን ኢንዱስትሪው በርካታ መረባበሾች ሊከተሉ ይችላሉ።

በዋናነትም የ5ጂ መጀመር ለዚህ ለሚጠበቀው ምስቅልቅል ምክንያት ሊሆን ይችላል።

በቅርቡ ደግሞ የአሜሪካ አቪየሽን ቁጥጥር ባለሥልን፣ በምህጻሩ ኤፍኤኤ፣ እንዳለው የ5ጂ ሰርጎ ገብ ሞገዶች የቦይንግ 787 ድሪምላይነር ሲስተሞችን ሊያውኩ ይችሉ ይሆናል።

ይህም በአመዛኙ አውሮፕላኖች በሚያርፉበት ጊዜ በምቾት እንዳያርፉና በማኮብኮቢያ አውራ ጎዳና ላይ እንዲንገጫገጩ ብሎም እንዲያዳልጣቸውና እንዲንገዳገዱ ሊያደርግ ይችላል።

ታዲያ የ5ጂ መጀመርን ተከትሎ የአውሮፕላኖች ደኅንነት እንዴት ይጠበቃል?

አውሮፕላኖች አልቲሜትሮችን እንዳይጠቀሙ ለማድረግ ነው ለጊዜው እንደመፍትሄ የታሰበው።

አልቲሜተርስ ከ5ጂ ጋር የመረጃ ቅብብሎሽ ግጭት ሊያስከትል ስለሚችል መዛባትን ሊያመጣ ይችላል።

ስለዚህ ይህን እንዳይጠቀሙ ማድረግ ነው አንዱ አማራጭ።

አልቲሜተርን ካልተጠቀሙ ደግሞ አውሮፕላኖች በሚያርፉበት ጊዜ ዕይታቸው የተገደበ እንዲሆን ያደርጋል።

መግለጫ የሰጡት ዐሥሩ የአሜሪካ አየር መንገዶችም ያሉት ይህንን ነው።

የ5ጂ መጀመር ቢያንስ በዓመት አንድ ሺህ በረራዎች በመጥፎ አየር ንብረት ጋር ተያይዞ እንዲሰረዙ አልያም ደግሞ እንዲዘገዩ ያደርጋል።

የሌሎች አገራት አየር መንገዶች ይህ ችግር ይገጥማቸው ይሆን?

የአሜሪካ አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን የሌሎች አገሮች አየር መንገዶችም ችግሩ በተወሰነ መልኩ ሊነካቸው ይችላል።

ይህም የሆነበት ምክንያት 5ጂ እየተጀመረ ያለበት ሁኔታ ከአገር አገር ስለሚለያይ ነው።

በአውሮጳ አባል አገራት ለምሳሌ፣ እነዚህ የ5ጂ ፍሪኩዌንሲዎች የሚሠሩበት ሞገድ ዝቅ ያለ ነው።

ይህም አውሮፕላኖችና የበረራ ደኅንነት መረጃ ማቀበያዎች እንዳይታወኩ ያደርጋል።

ሌሎች አገራት ደግሞ ከዚህም ሻል ያለ እርምጃን ለመውሰድ አስበዋል።

ለምሳሌ በፈረንሳይ እየታሰበ ያለውን ከወሰድን፣ የ5ጂ ሲግናሎች አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጭ የሚያደርግ አሠራር ለመዘርጋት ታስቧል።

አንቴናዎችም በዚያ አካባቢ ዝቅ ተደርገው ይተከላሉ።

ይህም የአውሮፕላን መረጃ ማቀበያ ፍሪኩዌንሲዎች ያለ ምንም መታወክ ሥራቸውን እንዲሠሩ ያስችላል።

በአሜሪካ ምን ለማድረግ ታስቧል?

በአሜሪካ የበረራ ቁጥጥር መሥሪያ ቤት በርከት ያሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ አቅዷል።

በ50 የአውሮፕላን ጣቢያዎች መካከል የ5ጂ አገልግሎትን የሚያግዱ ቀጠናዎችን አዘጋጅቷል።

ይህ ግን ፈረንሳይ ከወሰደችው ተመሳሳይ እርምጃ አንጻር በስፋትም በመጠንም ዝቅተኛ ነው።

በሌሎች አየር ማረፊያዎች ደግሞ የራዲዮ አልቲሜትሮችን በጂፒኤስ ሲስተም የመተካት ሥራ ተጀምሯል።

ይህም አልቲሜተርስ በ5ጂ ሊታወኩ ስለሚችሉ እነሱን ዘወር ማድረግ፣ ደኅንነትን ጠበቅ የማድረግ ያህል ሆኖ ስለታሰበ ነው።

ይሁንና አየር መንገዶች አሁንም እያሉት ያሉት ይህ ሁሉ በቂ እንዳልሆነ ነው።

የአየር መንገዶቹ ጥያቄ አንድ ነው። የ5ጂ ኢንተርኔት አገልግሎት ከየትኛውም አየር ማረፊያ በ2 ማይል ወይም በሦስት ኪሎ ሜትሮች ርቀት በጭራሽ ድርሽ እንዳይል ማድረግ።

የ5ጂ አገልግሎት ሰጪዎች ምን ይላሉ?

ቨሪዞን እና ኤቲ&ቲ በዚህ ስጋት የተነሳ የ5ጂ አገልግሎትን አዘግይተዋል።

ለዚያውም ሁለት ጊዜ ነው ያዘገዩት።

ብዙዎቹ ቴሌኮሞች አየር መንገዶች አካባቢ አገልግሎታቸውን ላለመስጠትም ተስማምተዋል።

ይሁንና የ5ጂ አገልግሎት በ40 አገራት የተጀመረ ቢሆንም ይህ ስጋት እውን እንዳልሆነ በማንሳት እየተሟገቱ ነው።

ባለፈው ወር የአሜሪካ ገመድ አልባ ኢንዱስትሪ ማኅበር የአየር መንገዶች የማይጨበጥ ፍርሃት እየነዙ ለምጣኔ ሃብት መነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊኖረው የሚችለውን የ5ጂ አገልግሎት እንዲዘገይ አድርገዋል ሲል ወቅሷቸዋል።