ግዙፎቹ አውሮፕላን አምራቾች ቦይንግ እና ኤርባስ አሜሪካ የ5ጂ አገልግሎትን እንድታዘገይ ጠየቁ

በዓለም ግንባር ቀደም የአውሮፕላን አምራቾቹ ቦይንግ እና ኤርባስ የአሜሪካ መንግሥት 5ጂ አገልግሎትን እንዲያዘገይ ጠየቁ።

5ጂ በአቪየሽን ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል በመጥቀስ ነው ሁለቱ ድርጅቶች ስጋታቸውን ለአሜሪካን መንግሥት የገለጹት።

ገመድ አልባው 5ጂ የኢንተርኔት ትስስር የአውሮፕላኖችን የኤሌክትሪክ ሥርዓትን ሊያደናቅፍ እንደሚችል ሲነገር ቆይቷል።

ግዙፎቹ የአሜሪካ ቴሌኮም ተቋሞች ኤቲኤንድቲ እና ቬርዞን፤ 5ጂ አገልግሎት ጥር ላይ እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።

የቦይንግ እና የኤርባስ ዋና ኃላፊዎች ዴቭ ካሎን እና ጀፍሪ ኒትል በጋራ ለአሜሪካ የትራንስፖርት ዘርፍ ፀሐፊ ፒት ቡድዤዥ አንድ ጥናትን ጠቅሰው በጻፉት ደብዳቤ የአየር ትራንስፖርት ባለሥልታኑ ውሳኔ ተግባራዊ ቢሆን ኖሮ በአውሮፓውያኑ 2019 345ሺህ የመንገደኛ በረራዎች እና 5,400 የጭነት አውሮፕላኖች ይዘገዩ፣ ይሰረዙ አልያም መዳረሻ ይቀይሩ ነበር።

በወቅቱ 5ጂ እንዳይጀመር የወሰነው የፌደራል አቪየሽን አስተዳደር (ኤፍኤኤ) ነው።

የአውሮፕላን ከፍታ መለኪያን (ራድዩ አልቲትዮድ ሜትር) የመሰሉ ስሱ የሆኑ የአውሮፕላን ክፍሎች በ5ጂ ምክንያት ሊሰናከሉ እንደሚችሉ ኤፍኤኤ ስጋቱን ገልጿል።

"ኤርባስ እና ቦይንግ ከሌሎች አውሮፕላን አምራቾች ጋር 5ጂ በረራ ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ መክሯል። የአሜሪካ የትራንስፖርት ሚኒስትር ያቀረብነውን የማሻሻያ ምክረ ሐሳብ እንዲቀበል እንጠይቃለን" ሲሉም አውሮፕላን አምራቾቹ ተናግረዋል።

ባለፈው ጥቅምት የቴሌኮም ድርጅቶቹ ኤቲኤንድቲ እና ቬሪዞን ሲ-ብራንድ የተባለውን የገመድ አልባ ትስስር አገልግሎት ሊጀምር ነበር። ኋላ ላይ ግን የሚያሳድረውን ተጽዕኖ እስከምቀርፍ ብሎ ወደ ጥር አዛውሮታል።

አውሮፕላን አምራቾቹ በበኩላቸው ገመድ አልባ ትስስሩ በረራ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመቅረፍ የቴሌኮም ድርጅቶቹ የሄዱበት ርቀት በቂ አይደለም ሲሉ ወቅሰዋል።

የዩናይትድ ኤርላየንስ ዋና ኃላፊ ስኮት ኪርቢ ባለፈው ሳምንት እንዳሉት፤ 5ጂ ጥቅም ላይ ሲውል የአውሮፕላን ከፍታ መለኪያ ወደ 40 በሚጠጉ አውሮፕላን ማረፊያዎች በአግባቡ እንዳይተገበር ያደናቅፋል።

በአሜሪካ ገመድ አልባውን የኢንተርኔት ትስስር 5ጂ የሚዘረጋው ሲታ በበኩሉ 5ጂ ሙሉ በሙሉ ደኅንነቱ የተጠበቀ እንደሆነ ገልጿል። አውሮፕላን አምራቾቹ እውነታውን አንጋደው ለማሳየት እየሞከሩ ነው ሲሉም ወቅሰዋል።