ሳሙኤል ሞላልኝ፡ በነዋሪዎች እየተወደሱ ያሉት የደሴ ከተማ ከንቲባ

ላለፉት አስርት ዓመታት ተዳክማ የነበረችው ደሴ ከተማ እንደገና እያንሰራራች ይመስላል።

ከአዲስ አበባ በ400 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በአማራ ክልል ውስጥ የምትገኘው ጥንታዊቷ እና ታሪካዊቷ ከተማ ለዓመታት እዚህ ግባ የሚባል የልማት እንቅስቃሴ እንዳልነበራት ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በግብር፣ በመልካም አስተዳደር እና በመሠረተ ልማት በመማረር ከተማዋን ለቀው የወጡ ነዋሪዎችም አሉ።

በተለይ ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋሉ ባሉት ዓመታት በአገሪቷ ተረስተዋል ከሚባሉት ከተሞች አንዷ እንደሆነች ይነገራል።

“ከተማ ሲያረጅ ደሴን ይመስላል” እየተባለም ተተርቶባታል።

ይባስ ብሎ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ከአንድ ወር በላይ ለሆነ ጊዜ በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር በነበረችበት ወቅት የመሠረተ ልማት ውድመት፣ የመንግሥት መዋቅር መፈራርስ አጋጥሟታል።

አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው የተሾሙትም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ደም አፋሳሽ ጦርነት ማብቂያ ላይ ነበር።

አቶ ሳሙኤል ደሴ ከተማን አይወለዱባት እንጂ ለከተማዋ ቅርብ ናቸው።

በሰሜን ወሎዋ ዋድላ ተወልደው ቢያድጉም ትምህርት ሲዘጋ ክረምቱን በከተማዋ ነበር የሚያሳልፉት።

ከዚያም በሥራ ሕይወታቸው መቀመጫቸውን ደሴ አድርገው፣ የምሥራቅ አማራን ከተሞች ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

ታዲያ የወሎ ማኅበረሰብ መዳረሻዋ፣ መናገሻ ከተማዋ፣ በርካታ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴት ያላት እንዱሁም በኪነ ጥበቡም ሆነ በሙዚቃው ስመ ገናና የነበረችው ከተማ በሚገባት ልክ አለማደጓ አቶ ሳሙኤልን ያስቆጫቸው ነበር።

“ለምንድን ነው ወደ ኋላ የምትቀረው? ሰው የላትም ወይ? መሥራት አይቻልም ወይ ?” ሲሉም ይብሰለስሉ ነበር።

ሆኖም ግን ከተማዋን በከንቲባነት እመራለሁ ብለው አስበው እንደማያውቁ ይናገራሉ።

የሰሜኑ ጦርነት ካበቃ በኋላ ግን አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ከተማዋን በተቀዳሚ ምክትል ከንቲባነት እንዲመሩ ከክልሉ ጥያቄ ቀረበላቸው።

“የነበርኩበት ቦታ የተሻለ ስለነበር እና በነበርኩበት የሥራ ኃላፊነትም ሕዝቡን የማገለግልበት ዕድል ስለነበር ጥያቄውን ለመቀበል ትንሽ አቅማማሁ” የሚሉት አቶ ሳሙኤል፣የነበረባቸው ቁጭት አይሎ ጥያቄውን ተቀብለው ኃላፊነቱን ተረከቡ።

ኃላፊነቱን ሲረከቡም ለውጥ ለማምጣት እንጂ ለሥልጣን አሊያም ለጥቅም እንዳልነበር ይናገራሉ።

ሥልጣን በድኅረ ጦርነት

አቶ ሳሙኤል ኃላፊነቱን የተረከቡት ጦርነቱ ከደሴ ከተማ በራቀ ማግስት ነው።

ከተማዋ የባሰ ተዳክማለች። ንብረቶች ተዘርፈዋል። ቅርሶች ተዘርፈዋል፤ ወድመዋል። የፀጥታውን ጨምሮ የመንግሥት መዋቅሮች ፈራርሰዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብ የተረጋጋ አልነበረም። ሥነ ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ቀውሱም በርትቶ ነበር። ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴውም ተቀዛቅዟል።

ለወትሮው የፍቅር ንፋስ የሚነፍስባት ከተማ ደሴ፣ ያኔ የደኅንነት ስጋት አንዣቦባት ነበር።

ጦርነቱን ሽሽት ከከተማዋ የተፈናቀሉ ነዋሪዎችም ገና የሚያውቋትን ከተማ አዲስ ጠባይ አልተለማመዱም።

የወርቅ ቤቶች ዘረፋ፣ የሰዎች መጠለፍ ነበር።

“አመራሩ ወደ ኃላፊነት ሲመጣ ዙሪያውን ፈንጂ ሆኖ፣ ፈንጂውን ለማምከን መሃል ላይ በፓራሹት የወረድን ያህል ነበር የተሰማን” ይላሉ በተለይ ከፀጥታው ጋር በተያያዘ የነበረውን ከፍተኛ ስጋት ሲያስታውሱ።

የከተማዋን ሰላም ወደ ነበረበት መመለስ፣ ተቋማትን እንደገና ማደራጀት፣ ነዋሪዎችን ማነቃቃት ለአቶ ሳሙኤል ቀላል አልነበረም።

ቅድሚያ የሰጡት ግን ይህንኑ ነበር።

ከአዲሱ የከተማዋ አመራሮች ጋር ውይይት በማድረግ ውጤት ላይ የተመሠረተ ተግባር ለማከናወን ከስምምነት ደረሱ።

‘የሁሉ እኩል አገር’ ተብሎ እንደተዜመላት “የውጤት አመራር እንሁን እና ችግሮችን እንፍታ። በመርኅ አንድ እንሁን። ከዝምድና ወጥተን ሙስሊም ክርስቲያን ሳንል ወሎዬ ሆነን [ሁሉንም እኩል በማየት] እንምራ ተባባልን” ይላሉ አቶ ሳሙኤል።

እስከ ቀበሌ ወርደው ሕዝብ አነጋገሩ። የሕዝቡን ጥያቄ እና ስጋት ተቀበሉ። ከዚያም “ሥነ ልቦናውን ተረዳሁ” ይላሉ።

በዚሁ መሠረት የከተማው የንብረት ግዢ እንዲፈፀም፣ የወደሙ እና የተዘረፉ ንብረቶች እንዲተኩ አደረጉ።

የፀጥታ መዋቅሩን እና ተቋማቱን መልሰው አደራጁ። የደሴን ሰላም በአጭር ጊዜ ካስተካከሉ በኋላም ከተማዋን ለማነቃቃት ስብስባዎች እና ሥልጠናዎች እንዲካሄዱ ማስተዋወቅ ያዙ።

ይህም ሆቴሎች እና የእንግዳ ማረፊያ ቤቶች እንዲሁም የንግድ ተቋማት በፍጥነት ሥራ እንዲጀምሩ አስቻለ። ከተማዋ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዋ ተመለሰች።

ሳይጠናቀቁ ዓመታት ያስቆጠሩ ፕሮጀክቶች

ከሁለት ዓመት በፊት ቢቢሲ ለምርጫ ዘገባ ወደ ደሴ ከተማ ባቀናበት ወቅት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦላቸው ያልተጀመሩ፣ አሊያም ተጀምረው ያልተጠናቀቁ፣ ተጠናቀው አገልግሎት ሳይሰጡ አስር እና ከዚያ በላይ ዓመታት ያስቆጠሩ ፕሮጀክቶችን ለማየት ችሎ ነበር።

ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ጢጣ በተባለው አካባቢ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦለት የነበረው የወሎ ቴሪሼሪ ሆስፒታል ነበር። በዚሁ አጋጣሚ የበርካታ ሕዝብ ገንዘብ እና ተስፋ የቀለጠበትን ሆስፒታል የመሠረት ድንጋይ ፎቶ ለማንሳት ወደ ሥፍራው አቅንተን ነበር።

አንድ ወጣት ከወደዚያው አቅጣጫ ሲመጣ አግኝተን የመሠረት ድንጋዩ የቱ ጋ እንደተቀመጠ እንዲጠቁመን ጠየቅነው።

“እዚያ ጋ . . . ነው፤ ካልሰመጠ ታገኙታላችሁ” ነበር መልሱ። እውነትም ሰምጦ ቢሆን እንጂ ፈልገን ባላጣነው ነበር።

በእርግጥ በከተማዋ ታቅዶ እና ታልሞ የውሃ ሽታ ሆኖ የቀረው የወሎ ቴሪሼሪ ሆስፒታል ብቻ አይደለም።

በ2004 ዓ.ም. በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት የወሎ ባህል ማዕከል፣ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ያልጀመረው የምሥራቅ አማራ ሪጂናል ላብራቶሪ፣ በዕቅድ ላይ የነበሩ በርካታ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ግንባታ፣ የአሰፋ አባተ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ግንባታ እና የመርሆ ቤተ መንግሥት ግቢ እድሳትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።

ከአራት ዓመታት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የቀድሞው የክልሉ ፕሬዝደንት አምባቸው መኮንን ደሴ ከተማ ተገኝተው ከሕዝብ ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅትም እነዚሁ የመሠረተ ልማት፣ የሥራ አጥነት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዋናነት መነሳታቸው አይዘነጋም።

የደሴ ከተማ ከንቲባው አቶ ሳሙኤል ወደ ኃላፊነት ከመጡ አንድ ዓመት ከመንፈቅ ቢሆናቸው ነው። በዚህ አጭር ጊዜ ሁለት የመንግሥት ሥርዓት ያዩ ፕሮጀክቶችን ጥያቄ መመለስ አይችሉም።

ሆኖም ያቀዱት ካለ ብለን ጠይቀናቸው ነበር።

አቶ ሳሙኤል “በሕዝቡ ፍላጎት መሠረት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ለይተን ነው ወደ ሥራ የገባነው” ይላሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት የሕብረተሰቡ ዋነኛው የመሠረተ ልማት ጥያቄ መንገድ ነበር።

በዚህም ለዓመታት ከነዋሪዎች እሮሮ ሲሰማባቸው የነበሩ በርካታ የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት እና የጠጠር መንገድ ፕሮጀክቶች ተሠርተው ተጠናቀዋል። በሒደት ላይ ያሉም ይገኛሉ።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአስርት ዓመታት ተቆፋፍረው እና ፈራርሰው የቆዩ መንገዶችን እንዲሁም የውሃ መፋሰሻዎች ተቀላጥፈው መሠራታቸውም በብዙዎች ዘንድ አግራሞትን አጭሯል።

ምስጢሩ ምንድን ነው? አልናቸው።

አቶ ሳሙኤል ለጥያቄያችን የሰጡት መልስ አጭር ነው። “የአመራር አንድነት በመፈጠሩ ነው” የሚል።

እርሳቸው እንደሚሉት ከመምሪያው ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ በመርኅ ላይ የተመሠረተ ጠንካራ የአመራር ቡድን ተመሥርቷል።

“አመራሩ በተግባር ማሳየት ሲጀምር፣ ሕዝቡ አመራሩ ላይ እምነት ኖሮት ከአመራሩ ጎን ተሰልፏል” ይላሉ።

‘ቅን ልቦች’ በሚል የተሰባሰቡ የደሴ ተወላጆች በራሳቸው ተነሳሽነት ሕዝቡን አሰባስበው በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተገነባውን እና የከንቲባው ቢሮ የሚገኝበትን ባለ ሁለት ወለል ሕንጻ መልሰው ገንብተው እንዳስረከቧቸው ለአብነት ጠቅሰዋል።

“ታይቶ ለማይታወቅ ችግር ታይቶ የማይታወቅ መፍትሔ ማፍለቅ ያስፈልጋል” የሚሉት አቶ ሳሙኤል፣ አዳዲስ አሠራሮችን ማፍለቅ መጀመራቸውን እና ሕብረተሰቡም መተግበር እንደጀመረ ያስረዳሉ።

ለዚህም በአብነት የሚያነሱት ‘አስፓልት ፕላንት’ [አስፓልት የሚመረትበት ማሽን] ነው። ይህን ማሽን በክልሉ ድጋፍ ከቀረጥ ነጻ ማስገባት ችለዋል።

ይህ መሆኑም በከተማዋ የሚሠሩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በፍጥነት እንዲከናወኑ አግዟል።

ማሽኑ መግባቱ ለከተማዋ ብቻ ሳይሆን በአቅራቢያ ላሉ ከተሞች እንደሚረዳ እና የሥራ ዕድል ለመፍጠር አስተዋፅኦ እንደሚያደርግም አስረድተዋል።

በአማራ ክልል ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚበዛበት የደሴ ከተማ የአውቶብስ መናኸሪያም የሕዝብ ቅሬታ ከሚነሳባቸው ቦታዎች አንዱ ነበር።

ይህም አቶ ሳሙኤል ወደ ከንቲባነት ከመጡ በኋላ ምላሽ አግኝቶ፣ በከተማ አስተዳደሩ ዲዛይን ተሰርቶለት እየተገነባ ይገኛል።

ከዚህም በተጨማሪም ገራዶ ላይ ትልቅ የአውቶብስ መናኸሪያ ተገንብቶ ተጠናቋል።

ከግንባታዎቹ ፍጥነት ጋር የጥራቱን ጉዳይ የጠየቅናቸው አቶ ሳሙኤል፣ የመንገዶቹም ሆነ የግንባታዎቹ ጥራት በባለሙያዎች በቤተ ሙከራ እየተመረመረ እና ክትትል እየተደረገበት እንደተሠራ ገልጸዋል።

እያንዳንዱን ፕሮጀክት የሚከታተል፣ መሃንዲሶች የተካተቱበት እና ከየአካባቢዎቹ የተውጣጡ ግለሰቦች ያሉበት የልማት ኮሚቴ እንደተቋቋመም ጠቁመዋል።

“የልማት ተነሺዎች ‘ሕይወታችን ተቀየረ’ እንዲሉ ነው ያደረግነው”

ልማት ሲሠራ፣ ከተሞች ሲያድጉ ከአካባቢያቸው የሚፈናቀሉ ዜጎች መኖራቸው አይቀሬ ነው።

የደሴ ከተማ አስተዳደር እያካሄደ ባለው የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታም ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዲነሱ ተደርገዋል።

ይሁን እንጂ ምትክ ቦታ ተዘጋጅቶላቸው እና አምነውበት እንደሆነ አቶ ሳሙኤል ይናገራሉ።

“የልማት ሥራ ሲከናወን ነዋሪዎች በዚህ ፕሮጀክት ምክንያት ሕይወቴ ተለወጠ እንዲሉ እንጂ እንዲማረሩ ማድረግ አይገባም” ይላሉ አቶ ሳሙኤል።

ምክንያታቸው ደግሞ ለዜጎች በሚሠራው ልማት ዜጎችን መጉዳት የለበትም የሚል ነው።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የደሴ ከተማ ነዋሪም በልማት ከተነሱት ውስጥ ሰፈር ለመቀየር ከተፈጠረባቸው ስሜት ውጪ ይህ ነው የሚባል ቅሬታ እንዳልሰሙ ተናግረዋል።

ከንቲባው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ2000 በላይ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ መቻላቸውንም ጠቅሰዋል።

ከዚህም ባሻገር በጦርነቱ ወቅት የእሳት አደጋ መኪና ተዘርፎ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሳሙኤል፣ ለከተማዋ አዲስ የእሳት አደጋ መኪና መግዛት ተችሏል ብለዋል።

‘የከንቲባ ችሎት’

ነዋሪዎች ይማረሩባቸው ከነበሩ ችግሮች አንዱ የመልካም አስተዳደር እጦት ነው።

ከንቲባ ሳሙኤል ይህንን ችግር ለመፍታት ‘የከንቲባ ችሎት’ መሥርተው ተግባራዊ እያደረጉ ነው።

በከተማዋ በሳምንት ውስጥ ማክሰኞ እና ሐሙስ የሕዝብ ቀን ተደርገው ተለይተዋል።

እነዚህ ቀናት አቤቱታ አቅራቢው እና አቤቱታው የሚቀርብበት አመራር አዳራሽ ውስጥ ፊት ለፊት የሚገናኙባቸው ናቸው።

ቅሬታ ያለው ግለሰብ በተራው መሠረት ከንቲባው ፊት አቤቱታቸውን ያሰማሉ። እዚያው መፈታት የሚችል አቤቱታ ከሆነ ተነጋግረው ይፈታል፣ አሊያም ለሚመለከተው አካል አቅጣጫ ይቀመጣል።

አስተግባሪ ቡድንም ስላላ አፈጻጸሙን ይከታተላል።

በዚህም መሠረት ከ1800 በላይ የተበደሉ ሰዎች ችግራቸው እንደተፈታላቸው ከንቲባ ሳሙኤል ተናግረዋል።

በዚህ አሠራርም ሸኽ አሕመድ መሐመድ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ላለፉት ስምንት ዓመታት ሲደክሙበት ለነበረው ጉዳይ ፍትሕ ማግኘታቸውን ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

“ለአቤቱታ 12 ጊዜ ክልል ሄጃለሁ፣ ሁለት ጊዜ ወደ ፌደራል ሄጃለሁ። ዛሬ ፍትሕ ስለተሰጠኝ ደስ ብሎኛል” ብለዋል ሸኽ አሕመድ።

የከንቲባ ችሎት ታች ያለው የሕብረተሰብ ክፍል በቀጥታ ከንቲባውን የሚያገኝበትን ዕድል የሚፈጥር አሠራር ነው።

“ይህም ሕብረተሰቡ መብቱን እንዲያስጠብቅ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል” ይላሉ አቶ ሳሙኤል።

አቶ ሳሙኤል በወጣቶች ሥራ ፈጠራ፣ በስፖርቱ ዘርፍ፣ እንዲሁም በሌሎች የልማት ዘርፎች ላይ ለመሥራትም ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።

“ደሴን የምሥራቁ ቀጠና የልማት ኮሪደር አድርጎ መፍጠር፣ በሆቴል እና በቱሪዝም፣ በንግድ፣ በትምህርት፣ በመሠረተ ልማት ተደራሽነት አንድ ምዕራፍ ወደፊት ማሻገር” ግባቸው ነው።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በከተማዋ በሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች ደስተኛ ናቸው።

“ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ከፍተኛ የመንግሥት በጀት በነበረበት ወቅት ያልተሠራችውን ከተማ፣ አሁን መንግሥት እጅ ባጠረው እና ነዋሪዎችም በኑሮ ውድነት እየተፈተኑ ባሉበት ወቅት፣ በአጭር ጊዜ ይህን ማሳካታቸው የሚደነቅ ነው” ብለዋል ሁሴን ካሳ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ።

ነገር ግን ከላይ ያለው የአመራሩ ጥንካሬ ታች ድረስ መውረድ እንደሚቀረው ነዋሪው ሳይጠቁሙ አላለፉም። “ይህ ባለመሆኑም ታች መፈታት ያለበት ሥራ ከንቲባው ድረስ እየሄደ እርሳቸው ላይ ጫና እየፈጠረ ነው” ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ነዋሪዎቹ አንድ ስጋት አላቸው።

የተሻለ አፈጻጸም የሚያሳዩ አመራሮች ብዙውን ጊዜ በቦታቸው ሲረጉ አይታይም፣ እናም ያስቀመጡትን ግብ ሳያሳኩ ወደ ሌላ ኃላፊነት ይዛወሩ ይሆን ወይ የሚል።

ይህንኑ ስጋት ለአቶ ሳሙኤል ሰንዝረንላቸው ነበር።

እኔ ዓላማዬ በተመደብኩበት ውጤታማ ሆኖ መሥራት ነው። የአመራር ቡድኑ ጥሩ ለውጥ እያመጣ ነው። ባለንበት ትንሽ መሥራት እንፈልጋለን። ከዚያ ውጪ ያለው የፈጣሪ ሥራ ነው።

ጥያቄ ቢቀርብልዎት ይቀበሉታል ማለት ነው?

ያሰማራኝ ብልጽግና ነው። ያሰማራኝ ሕዝብ ነው። በዚያ መሠረት ሥራዬን እሰራለሁ። በግሌ ግን ሕብረተሰቡን ማገልገል እፈልጋለሁ።

ያስቀመጡትን ግብ መቼ አሳካለሁ ብለው ያስባሉ?

ግለሰብ ተፅዕኖ መፍጠር ይችላል። ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በየቦታው መኖር አለባቸው። እኔም ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ አመራሮችን መፍጠር ነው አላማዬ። መፍጠርም ተችሏል። በአመራር ለውጥ ምክንያት ሥራው እንዳይቆም ሥራዎችን ሠርተናል። ወደ ኋላ አይመለሱም። ሥራዎች እንዲጠናከሩ እየሰራን ነው ያለነው። እኔም አብሬ እንደምቀጥል ነው ተስፋ የማደርገው።

ጥቂት ስለ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ

አቶ ሳሙኤል የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው ከመሾማቸው ቀደም ብሎ በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነቶች ላይ ሠርተዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን፣ ዋድላ ደላንታ ወረዳ የፋይናንስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ ከዚያም የወረዳው አስተዳዳሪ በመሆን አገልግለዋል።

በአማራ ክልል የኢንደስትሪ ፓርኮች የገበያ ትስስር ዘርፍ አስተባባሪ ሆነው ሠርተዋል።

አሁን ወዳሉበት የደሴ ከተማ ከንቲባ ከመሆናቸው በፊትም በአማራ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ የምስራቅ አማራ የከተሞች ተቋማዊና መሠረተ ልማት ማስፋፊያ የዓለም ባንክ ፕሮግራም ዋና አስተባባሪ ሆነው ሲያገለግሉ ነበር።

አቶ ሳሙኤል የመጀሪያ ዲግሪያቸውን ከሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ አግኝተዋል።

ወደ አውሮፓ፣ ዱባይ እንዲሁም ወደ ደቡብ አፍሪካም ተጉዘው የከተሞችን እድገት ጎብኝተዋል። የከተሞች ልማት ላይ በሚሠሯቸው ተግባራትም በተለያዩ ጊዜያት እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

በደሴ ከተማ እያሳዩ ባሉት የሥራ አፈጻጸምም ከተማ አስተዳደሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሁለት ተሽከርካሪዎችን ተሸልሟል።