ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ደሴ ከተማ፡ ለአስርት ዓመታት በሕዝብ አደባባይ የሰንደቅ ዓላማ ሥነ ሥርዓት የምትከውነው ከተማ
የብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተሻሻለው በሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 863/2006 ዓ/ም አንቀጽ 2 መሰረት በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ በመጀመሪያው ሳምንት ሰኞ እንዲከበር ተደንግጓል።
ዘንድሮም ለ14ኛ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች ቀኑ ዛሬ ታስቦ ይውላል።
በኢትዮጵያ ከሚገኙ ጥንታዊ ከተሞች አንዷ በሆነቸው ደሴ፣ ሰንደቅ ዓላማን በክብር በአደባባይ መስቀልና ማውረድ የዕለት ተዕለት ክንውን ነው።
ደሴ ከተማ ፀሐይ ስትወጣና ፀሐይ ስትጠልቅ በሕዝብ አደባባይ ሰንደቅ ዓላማ የመስቀልና የማውረድ ሥነ ሥርዓት ያለማቋረጥ መከወን ከጀመረች አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል።
ከአዲስ አበባ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው እና የደቡብ ወሎ ዞን መቀመጫ የሆነችው ደሴ ከተማ በርካታ ባህላዊ ትውፊቶች፣ ታሪኮችና ቅርሶችን ይዛለች።
የንጉሥ ሚካኤል ቤተ መንግሥት፤ እርሳቸው ያስገነቡትና 'ማንንም የማይጠየፈው' 'አይጠየፍ አዳራሽ'፣ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን የተለያዩ መርሆዎች ይወጡበትና ፍትሕ ይሰጥበት እንደነበር የሚነገርለት 'የመርሆ ቤተ መንግሥት አልጋ ወራሽ ግቢ፣ በርካታ ምሁራንን ያፈራው ወ/ሮ ስኂን ትምህርት ቤት መገኛ ናት።
እንደ ጥንታዊነቷ እድገቷ ጎልቶ የማይታየው ደሴ ከተማ አሁንም ግን ያላረጁና ያልጃጁ ባህላዊ ትውፊቶች፣ የአገራዊ ፍቅር ክንውኖች ፣ በሐይማኖት፣ በብሔርና በኑሮ ደረጃ የተሰባጠረ ቀለል ያለ የአኗኗር ዘይቤዎች አሏት።
ከእነዚህ መካከል አንዱ አላፊ አግዳሚው ጠዋትና ማታ በክብር የሚከውነው ሕዝባዊ የሰንደቅ ዓላማ ሥነ ሥርዓቷ ነው።
ይህ ሥነ ሥርዓት የሚከወንበት ቦታ ደግሞ መሃል ፒያሳ ነው። ፒያሳ የደሴ ከተማ እምብርት ነው። በፒያሳ የሰውና የተሽከርካሪ እንቅስቃሴም በርከት ያለ ነው።
የደሴን ፒያሳ፣ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ከሚገኙ ፒያሳዎች ለየት የሚያደርገው ጠዋትና ማታ የሰንደቅ ዓላማ ሥነ ሥርዓት ስለሚከወንበት ነው።
ፒያሳ አደባባይ መሃል ላይ የተተከሉ ሁለት የሰንደቅ ዓላማ መስቀያዎች አሉ። አንዱ የአማራ ክልል ሌላኛው ደግሞ የፌደራል መንግሥት ሰንደቅ ዓላማዎች ይውሉባቸዋል።
ማለዳ 12፡00 ሰዓት ግራ እና ቀኝ ሰንደቅ ዓላማውን የሚያጅቡና ሰንደቅ አላማ የሚሰቅሉ የፖሊስ አባላት ሰንደቅ ዓላማዎቹን በክብር ይዘው በአደባባዩ ይገኛሉ።
ፊሽካ ይነፋል። እግረኛም ሆነ ተሽከርካሪ ባለበት ይቆማል። ሁሉም በያሉበት ለሰንደቅ ዓላማው ክብር ሰጥተው ሥነ ሥርዓቱን ይከውናሉ።
ማለዳ ላይ እምብዛም የሰዎች እንቅስቃሴ ባይኖርም ይህ ግን የማይቀር ነው።
አመሻሽ 12 ሰዓትም በዚሁ መልኩ ሰንደቅ ዓላማ የማውረድ ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል።
ሁለቱም ሰንደቅ ዓላማዎች [የክልሉም የፌደራሉም] የሚወርዱትም ሆነ የሚሰቀሉት እኩል ነው።
ይህንን የሰንደቅ ዓላማ ሥነ ሥርዓት መከወን መቼ ተጀመረ?
ደሴ ከተማ ተወልደው ያደጉት የ60 ዓመቱ ነዋሪ ይህ የሰንደቅ ዓላማ ሥነ ሥርዓት በትክክል መቼ እንደተጀመረ መናገር ባይችሉም ለ50 ዓመታት ያህል ሲከወን እንደሚያውቁ ይናገራሉ።
በጣሊያን ጊዜ ተሰርቶ የነበረው የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ ጽ/ቤት የሚገኘው ይሄው የሰንደቅ ዓላማ ሥነ ሥርዓት በሚከወንበት ፒያሳ ነበር።
በጽ/ቤቱ በር ላይ የሚሰቀል ሰንደቅ ዓላማ ነበር። ሰንደቅ ዓላማው በሚወጣበትና በሚወርድበት ጊዜም የፖሊስ አባላቱ በወታደራዊ ሰልፍ፣ ወታደራዊ ልብስ ለብሰውና ጡሩምባ መሳይ [ትራምፔት] ይዘው ሥነ ሥርዓቱ ይደረግ እንደነበር ነዋሪው ያስታውሳሉ።
ነዋሪው እንደሚሉት በወቅቱ ሰንደቅ ዓላማውን የሚያወርድና የሚሰቅል ሰውም ተመርጦ ነበር የሚዘጋጀው። ለዚህ ደግሞ ዓይነ ግቡና ሽንቅጥ ያለ ሰው ተመራጭ ነበር።
በዚህ መልኩ የተመረጠው ግለሰብም ጠዋት ሰንደቅ ዓላማውን ይሰቅላል፤ ማታ ደግሞ ያወርዳል።
ሥነ ሥርዓቱ በሚከወንበት ጊዜም ፒያሳ አካባቢ ያለ የሚንቀሳቀስ ሰውም ሆነ ተሽከርካሪ ባለበት ይቆማል።
ሥነ ሥርዓቱ ሲጠናቀቅ ያንን ሥነ ሥርዓት ሲያካሂድ የነበረው ፖሊስ ፊሽካ በመንፋት ሥነ ሥርዓቱ መጠናቀቁን ሲያሳውቅ እንቅስቃሴ ይቀጥላል።
በዚህ ሁኔታም ሥነ ሥርዓቱ ለዓመታት ሲካሄድ ዛሬ ላይ ደርሷል።
"ቆይቶ ግን ፖሊስ መምሪያው ያለበት ቦታ ባልታወቀ ሁኔታ እና የሕዝብ ድጋፍ ሳይኖረው በሊዝ ተሸጠ" የሚሉት ነዋሪው፤ ቦታው አሁን የንግድ ማዕከል መሆኑን ተናግረዋል።
ፖሊስ መምሪያውም ወደ ሌላ ቦታ ተዛውሯል፤ ይሁን እንጂ የሰንደቅ ዓላማው ሥነ ሥርዓት አልተቋረጠም።
በከተማዋ ወጣቶች ጥረት ፒያሳ በሚገኘው አደባባይ የሰንደቅ ዓላማ መስቀያ ቦታ ተዘጋጅቶ ሥነ ሥርዓቱ ቀጠለ።
በመካከል ግን በሚሰቀለው ሰንደቅ አላማ ጉዳይ ክርክር ተፈጥሮ የተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ እንደነበር የሚያስታውሱት ነዋሪው፣ ችግሩ በንግግር ተፈትቶ ሥነ ሥርዓቱ አሁንም መቀጠሉን ተናግረዋል።
አቶ ደረጀ ሁነኛውም ደሴ ከተማ መኖር ከጀመሩ አስር ዓመታት ተቆጥረዋል። በቆዩባቸው በእነዚህ ዓመታት ሥነ ሥርዓቱ ሲካሄድ ተመልክተዋል።
እርሳቸውም እያሽከረከሩም ሆነ በእግራቸው እየተጓዙ ሳለ እንደ አጋጣሚ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እየተገኙ ተካፍለዋል።
መጀመሪያ አካባቢ ሰዎች እና ተሽከርካሪዎች ቆመው ሲመለከቱ ግራ ተጋብተው ነበር።
በጊዜው ምክንያቱን ባይረዱትም ሁሉም ባለበት ቆሞ እርሳቸው ብቻ መጓዛቸው አግባብ እንዳልሆነ ስለተረዱ ዝም ብለው ባሉበት ይቆሙ ጀመር። በኋላ ግን የሰንደቅ ዓላማ ሥነ ሥርዓት መሆኑን ሲረዱ ደስታ እንደፈጠረባቸው ያስታውሳሉ።
"አሁንማ አንዳንዴ ሰዓቱ ሲደርስ ሆነ ብየ ወደ ሥፍራው የምሄድበት አጋጣሚም አለ፤ ታዲያ ይህ እድል ትምህርት ቤት ካልሆነ የት ይገኛል?" ይላሉ አቶ ደረጀ።
የደሴ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዋና ክፍል ኃላፊ የሆኑት ምክትል ኮማንደር ጌታቸው ሙህየም ይህንን ሥነ ሥርዓት ከ20 ዓመታት በላይ ለሆነ ጊዜ እንደሚያውቁት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እርሳቸውም ሥነ ሥርዓቱ ረዥም ጊዜ እንዳስቆጠረ እንጂ የተጀመረበትን ጊዜ በውል አያውቁትም።
በደፈናው "ቀደም ሲል በአባቶቻችን የተጀመረ ነው" ይላሉ።
ፒያሳ ይገኝ በነበረው የደሴ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ጽ/ቤት ሥነ ሥርዓቱ ይደረግ ስለነበር ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ እንደሆነ ነው ኮማንደሩ የሚያውቁት።
ከጠዋቱ 12 ሰዓት ሲሆን የፖሊስ አባላት የክልሉንና የፌደራሉን ሰንደቅ ዓላማ የመስቀል ሥነ ሥርዓት ያከናውናሉ። አመሻሽ 12 ሰዓት ላይ ሰንደቅ ዓላማውን የሚያወርዱትም የፖሊስ አባላት ናቸው።
"የፖሊስ አባላቱ ወደ ቦታው ሄደው ለሰንደቅ ዓላማው ሰላምታ ከሰጡ በኋላ ፊሽካ ይነፋል። አሽከርካሪውም እግረኛውም ይቆማል። ይህ በማኅበረሰቡ የተለመደ ነው" ይላሉ ኮማንደር ጌታቸው።
"ሥነ ሥርዓቱን ለማክበር ፒያሳ የሚመጡ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊትና ፖሊስ አባላት ነበሩ"
ኮማንደር ጌታቸው እንደሚሉት ሰንደቅ ዓላማውን የማውረድና የመስቀል ሥነ ሥርዓት የሚታደሙት በአካባቢው እግር የጣላቸው ብቻ አልነበሩም። ሥራዬ ብለው ሰዓት ጠብቀው በቦታው የሚገኙም አሉ።
ሥነ ሥርዓቱን ማየት የሚፈልጉ የቀድሞ የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊት አባላት 12 ሰዓት ላይ ፒያሳ ይገኙ ነበር።
ኅብረተሰቡ ይህንን ፕሮግራም በፍቅር እያከናወነ እንዳስቀጠለውም ኮማንደሩ ተናግረዋል።
"እስካሁን በሌሎች ከተሞች እንዲህ ዓይነት ሥነ ሥርዓት አላየሁም" ያሉት ኮማንደር ጌታቸው፣ ደሴ ከተማ ላይ የሚታየው የሰንደቅ ዓላማ ፍቅርና ሥነ ሥርዓት እንደ ቅርስ የሚወሰድ ነው ይላሉ።
"ድሮ 'በባንዲራ [ ሰንደቅ ዓላማ] አምላክ!' ይባል ነበር"
የደሴ ከተማ ነዋሪው በከተማው በሕዝብ አደባባይ የሰንደቅ ዓላማ ሥነ ሥርዓት መከበሩ የሰንደቅ ዓላማ፣ የአገር እና የአንድነት ፍቅር ፈጥሯል ይላሉ።
"ድሮ እኮ ለባንዲራ ከነበረው ፍቅርና ክብር የተነሳ በ'ባንዲራ አምላክ' ይባልም ነበር። ይህ የሚባለው ሰንደቅ ዓላማ የሁሉም በመሆኑ፤ ብሔር፣ ሐይማኖት፣ ድሃ፣ ሐብታም . . .ብሎ ስለማይለይ ነው" ይላሉ ነዋሪው።
ይህ ሥነ ሥርዓትም በተከታታይ የቀጠለው ኅብረተሰቡ የሰንደቅ ዓላማ፣ የአገር እና የአንድነት ፍቅር ስላለው ነው ብለዋል።
በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ሐብታምም፣ ድሃም፣ ወታደራዊ የደንብ ልብስ የለበሰውም፣ ባለሥልጣኑም፣ ነዋሪውም በያለበት ይቆማል። ይህ ግን ጫና በመፍጠር የሚደረግ ሳይሆን ኅብረተሰቡ በፍላጎትና በፍቅር የሚከወን መሆኑንም ነዋሪው አክለዋል።
ለበርካታ ጊዜያት እግር ጥሏቸው በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተገኙ የተናገሩት እኚህ ነዋሪ፤ " አንዳንድ እንግዳ ሰዎች ይህ ሲገጥማቸው ግር ይላቸዋል፤ በኋላ ግን ይቆማሉ። ነገር ግን ይህንን በማድረጋቸው የሚያሰሙት ቅሬታ የለም" ብለዋል።
የእርሳቸውን ሃሳብ ኮማንደር ጌታቸውም ይጋሩታል።
ነዋሪው ብቻ ሳይሆን ጠዋትና ማታ ተመድበው ሰንደቅ ዓላማ የሚሰቅሉና የሚያወርዱ የፖሊስ አባላትም ይህን የሚከውኑት በፍቅር ነው።
"በአጋጣሚ ሥነ ሥርዓቱን የተመለከቱ የደሴ እንግዶችም ማኅበረሰቡ ለሰንደቅ ዓላማው ላለው ፍቅር አድናቆትን ይቸራሉ" ይላሉ ኮማንደር ጌታቸው።
ኮማንደር ጌታቸው "ማኅበረሰቡ የባንዲራ ፍቅር አለው። ልዩ ስሜት ይሰጣል። አንድነታችንንም፤ አገራችንንም ጠዋትም ማታ ማስታወሳችንን የሚያሳይ ሥነ ሥርዓት ነው" ሲሉም ገልጸውታል።
ነዋሪዎቹና የፖሊስ ባልደረባ የሆኑት ኮማንደር ጌታቸው ለአስርተ ዓመታት ያህል በሕዝብ አደባባይ የሰንደቅ አላማ ሥነ ሥርዓት መከወኑ በማኅበረሰቡ ዘንድ የአገር፣ የሰንደቅ አላማ እና የአንድነት ፍቅር ፈጥሯል ብለዋል።