በኢትዮጵያ በኮሮና የሞቱ ሰዎች ወደ 6 ሺህ ሲጠጋ ሁሉም በሚባል ሁኔታ ያልተከተቡ መሆናቸው ተገለጸ

የዴልታ ኮሮናቫይረስ እየተዛመተ ባለባት ኢትዮጵያ የሟቾች ቁጥር እያሻቀበ ሲሆን ሟቾቹ ሁሉም በሚባል ሁኔታ ያልተከተቡ መሆናቸውንም የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ከሰኔ እስከ ነሐሴ ወር አጋማሽ ህይወታቸውን በኮሮናቫይረስ ካጡት መካከል አንዱ ብቻ ብቻ ክትባት የወሰደ መሆኑንና ሌሎች ግን ያልተከተቡ መሆናቸውን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በኢትዮጵያ እስከ ትናንትናው ዕለት መስከረም 29፣ 2014 ዓ.ም ድረስ ባለው ወቅት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 5 ሺህ 950 ደርሷል።

ባለፈው ሳምንት በኮሮና ቫይረስ የሞቱ ሰዎች 308 ሲሆን ይህም ወረርሽኙ ከጀመረበት ጊዜ ከፍተኛው ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን በየቀኑም በአማካይ ከ1 ሺህ በላይ በቫይረሱ ሲያዙ በዚህ ሳምንትም በየቀኑ በአማካኝ 44 ሰዎች እየሞቱ እንደሆነም የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

የሟቾች ቁጥር ማሻቀብ፣ ወደ ፅኑ ህሙማን የሚገቡ ሰዎች ቁጥርና በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማንሰራራት ያሳየው የዴልታ ቫይረስ ዝርያ በመኖሩ፣ ስብሰባዎች መበራከት እና ማስክ አለማድረግና ውሳኔዎችና ደንቦችን ማክበር በመቀዛቀዙ ምክንያት እንደሆነም የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ተናግረዋል።

በወረርሽኙ ዙሪያ ወቅታዊ ጉዳዮች፣ ክትባት እና በመጪው ቀናት የሚከፈቱ ትምህርት ቤቶች ማድረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄን አስመልክቶም በሰጡት መግለጫ ነው ይህንን የተናገሩት።

ሚኒስትሯ የሲዲሲን ጥናት ዋቢ አድርገው እንዳስረዱት ያልተከተቡ ሰዎች ለበሽታው ከፍተኛ ተጋላጭ እንደሆኑና በቫይረሱ የመያዝ እድላቸው ከ4.5 እጥፍ በላይ፣ ሆስፒታል የመግባት እድላቸው ከ10 እጥፍ በላይ፣ ታመው የመሞት እድላቸው፣ ከ11 እጥፍ በላይ ነው ብለዋል።

ከትምህርት ቤቶች መከፈት ጋር ተያይዞም ሊደረግ የሚገባውን ጥንቃቄም አስመልክተውም መምህራንን መክተብ፣ ወላጆችንና ተማሪዎችን መከላከያ ዘዴዎችን ማስተማር፣ ማስክን አስገዳጅ ማድረግ እንዲሁም አካላዊ ርቀትን መጠበቅና የፈረቃ ስርዓትም ተግባራዊ እንዲሆን ጠይቀዋል።