ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኮሮናቫይረስ የሚሞቱ ሰዎች መጨመሩን ተከትሎ ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 መመሪያዋን አሻሻለች
በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የሚሞቱ፣ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያግዝ የተሻሻለ መመሪያ መውጣቱ ተገልጿል።
በተሻሻለው መመሪያ መሰረት ከስድስት አመት በላይ የሆኑ ህፃናት ማስክ እንዲያደርጉ፣ በሰርግ፣ በቀብር እንዲሁም በስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ሰዎች ብዛት ከአምሳ እንዳይበልጥ፣ በካፌዎችና በሬስቶራንቶች በአንድ ጠረጴዛ ከሶስት ተገልጋዮች በላይ እንዳይቀመጡ የሚሉና ሌሎች ዝርዝሮች ተካትተውበታል።
የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያወጡት ይህ መመሪያ ከነሐሴ 13 ፣ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።
በተሻሻለው መመሪያ መሰረት ማንኛውም ሰው ማስክ ሳያደርግ እንዳይንቀሳቀስ የሚያግድ ሲሆን ይህም ከስድስት አመት በላይ የሆኑ ህፃናትን እንደሚጨምር የጤና ሚኒስቴር በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አስገዳጅ የማይሆነው ከስድስት አመት በታች ለሆኑ ህፃናት እንዲሁም በማስረጃ የተረጋገጠ የመተንፈሻ አካላት ወይም መሰል ችግር ካለባቸው በስተቀር ሁሉም ዜጎች ሲንቀሳቀሱ ማስክ ማድረግ አለባቸው።
የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛዎች በክፍት ገበያዎች፣ በትራንስፖርት መሳፈሪያ ቦታዎች፣ ህዝባዊ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቦታዎችና ሌሎች ህዝብ በሚበዛባቸው መሰል አካባቢዎች ከመደረግ በተጨማሪ ሁለት የአዋቂ እርምጃ (አካላዊ ርቀት) መጠበቅ አስገዳጅ ነው ተብሏል።
በማንኛውም መንግስታዊ እና የግል ተቋም አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች ላይ ሰራተኞችና ደንበኞች ከሁለት የአዋቂ እርምጃ ወይም አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲገለገሉና ማስክ እንዲያደርጉ ያስገድዳል።
በእነዚህ የአገልግሎት ስፍራዎች በአንድ ጠረጴዛ ከሶስት ተገልጋዮች በላይ እንዲቀመጡ ማድረግም ተከልክሏል።
ማንኛውም የመንግሥታዊ እና የግል ተቋማት በመግቢያና መውጫ በሮች የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚረዱ የጥንቃቄ ቁሳቁሶችን ማቅረብና አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን መተግበራቸውን የማረጋገጥ ግዴታ አለባቸው ብሏል።
በአስከሬን ማስተካከል፣ ግነዛና ማጓጓዝ ወቅትም ሊደረጉ ስለሚገባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎችም መመሪያው አስቀምጧል።
ከቀብር በኋላ ሀዘን ለማስተዛዘን በድንኳን፣ በቤት ውስጥ ወይም ለዚሁ በተዘጋጀው ቦታ ላይ ለቅሶ የሚደርሰው ሰው ከ50 እንዳይበልጥ ያዛል። አካላዊ ርቀት መጠበቅ እንዲሁም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ አለባቸው ይላል።
በስብሰባም ወቅት በተመሳሳይ የኮቪድ-19 ጥንቃቄዎችን በተከተለ መልኩ እስከ 50 ሰው መሰብሰብ ይቻላል።
ከ50 ሰዎች በላይ መሰብሰብ ግዴታ ሆኖ ከተገኘ ስብሰባው ሊደረግበት የታሰበበት ስፍራ ጠቅላላ ስፋት ከግምት ውስጥ ሊገባ እንደሚገባ ጠቁሞ በዚህም መሰረት ቦታው ሊይዝ ከሚችለው ሰው ብዛት አንድ አራተኛ በማይበልጥ መሆን አለበት።
እንዲሁም ልዩ ፈቃድ ከሰላም ሚኒስቴር እንዲሁም ከክልሉ፣ ዞን እና ወረዳ የሰላም እና ፀጥታ መዋቅሮች መገኘት አለበት። ስብሰባውንም የጠራው አካል የመከላከያ ዘዴዎቹ መተግበራቸውን ማረጋገጥ ይገባዋል ይላል።
የሃይማኖት ስነ ስርዓትን በተመለከተ ሃይማኖታዊ አገልግልቶች አካላዊ ርቀትን በጠበቀ መልኩ ሊፈፀሙ እንደሚገባ መመሪያው አስቀምጧል።
የሃይማኖት ስርዓት የሚከናወንባቸው ስፍራዎችም እንዲሁ መያዝ ከሚችሉት አንድ አራተኛ በማይበልጥ ስርዓቱን እንዲያካሂዱ ተቀምጧል። በእነዚህ የእምነት ተቋማት ቅጥር ግቢ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ግዴታ ነው።
የቤት ውስጥ ማህበራዊ ዝግጅቶችን በተመለከተም ለልደት፣ ምረቃ፣ ማህበር እና ቀብር እና ከቀብር መልስ ያሉ ስነ ስርዓቶች ውጭ እና መሰል በቤት ውስጥ የሚዘጋጁ ማህበራዊ በዓላት ከቤተሰብ አባላት ከሆኑ ውጭ ተጠራርቶ ማክበር የተከለከለም ነው።
ሰርግን በተመለከተም አካላዊ ርቀትን በጠበቀ መልኩ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ በማድረግ እና ተገቢውን የኮቪድ-19 መከላከያ የንፅህና እርምጃዎች በተገበረ መልኩ ከ50 በማይበልጡ ሰዎች ማካሄድ እንደሚቻል ተቀምጧል።
የአደባባይ በዓላትን አከባበር ጋር ተያይዞ ህዝብን በብዛት የሚያሳትፉ የአደባባይ ላይ በዓላት የወረርሽኙ ስርጭት እስኪረጋጋ ድረስ ባይደረጉ በማለትም ምክረ-ኃሳብ አስቀምጧል።
በዓላቱ የሚደረጉ ከሆነ ግን የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ መደረጉን እንዲሁም አካላዊ ርቀትን በጠበቀ መልኩ መሆን አለበት ብሏል። ስፍራዎቹም ከሚይዙት ቦታ ከአንድ አራተኛ ቦታ በማይበልጥ ሰው ስርዓቱ ሊካሄድ እንደሚገባም ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል ብሏል።
ስፖርታዊ ውድድሮችም በተመለከተ በተመሳሳይ ስፍራው ከሚይዘው የታዳሚ ብዛት ከአንድ አራተኛ በማይበልጥ እንዲሆን ተቀምጧል።
አገልግሎት የሚሰጡ እንደ ካፌዎች፣ ባር፣ ሬስቶራንቶች፣ መጠጥ ቤቶች፣ የመዝናኛ እና መጫዎቻ አገልግሎቶች በአንድ ጠረጴዛ ከሶስት ሰው በላይ ማስተናገድ አይችሉም። በእያንዳንዱ ጠረጴዛ የሁለት ሜትር ርቀት መጠበቅ አለበት።
አገልግሎትን የሚሰጡም ሆነ ደንበኞች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛን የማድረግ ግዴታ አለባቸው።
ከዚህም በተጨማሪ የወረርሽኙ ስርጭት ያለበት ሁኔታ በየጊዜው እየታየ በሌላ መመሪያ እስኪወሰን ድረስ የአረጋዊያን መጦሪያዎች ስፍራዎች እና የማገገሚያ ማዕከላት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በአካል መጠየቅ የተከለከለ መሆኑን አስፍሮ ነገር ግን እርዳታ ማቅረብ የሚፈልጉ ከተቋሙ አስተዳደር ድረስ በመቅረብ ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉም ጠቁሟል።
በማረሚያ ቤቶች ላይ ታራሚን ለመጠየቅ አካላዊ ርቀትን ጨምሮ ሌሎች አስገዳጅ የኮቪድ- 19 መከላከያን በጠበቀ መልኩ መሆን አለበት ተብሏል።
በቤት ውስጥ ማቆያ እና እንክብካቤን በተመለከተ ቀለል ባለ በኮቪድ-19 የተያዘ ታማሚ በቤት ውስጥ የኮቪድ-19 ህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ ይደረጋል።
ህመምተኞቹ ከሌላው የቤተሰብ አባላት ራሳቸውን መለየት፣ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ መጠቀም፣ ቢያንስ ለ10 ተከታታይ ቀናት መለየትና ከቤት አለመውጣት ይጠበቅባቸዋል።
ኮቪድ-19 ያለበት ሰው ቫይረሱ እንዳለበት እያወቀ ወደ ሃገር ውስጥ መግባት፣ ከማህበረሰቡ ጋር መቀላቀል ወይም ከሌሎች ሰዎች ጋር መገናኘት የተከለከለ ነው።
ከትራንዚት መንገደኛ በስተቀር በአገሪቱ አለም አቀፍ ማረፊያ በኩል የሚገባ ከአስር አመት ዕድሜ በላይ የሆነ ማንኛውም ተጓዥ ከ120 ሰዓት ወይም አምስት ቀን በላይ ያልሆነው የተረጋጋጠ ምርመራ ኔጌቲቭ ውጤት ይዞ መምጣትና ለሰባት ቀናት መንገደኞች ራሳቸውን ለይተው ማቆየት አለባቸው።
ነገር ሰባት ቀናት ራሳቸውን ለመለየት የማይገደዱት በ90 ቀናት ውስጥ ኮቪድ-19 ታመው ያገገሙ፣ ዲፕሎማቶች፣ የኮቪድ-19 ክትባትን በተሟላ ሁኔታ ወስደው ያጠናቀቁ ከሆነ ለተለያዩ ስብሰባዎች የሚመጡ ቱሪስቶች ወይም ለድንገተኛ ጉዳይ የሚመጡ መንገደኞች ናቸው።
ለተለያዩ ጉባዔ የሚመጡ ሰዎች የኮቪድ-19 ምርመራ ማድረግና ውጤታቸው ኔጌቲቭ መሆን አለበት። ማንኛውም ፖዘቲቭ ሰው ወደ ሃገር ውስጥ መግባት የተከለከለ ነው።.
በአገሪቱ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ በኩል የሚያልፉ የትራንዚት መንገደኞችን በተመለከተም በረራቸው እስኪደርስ ድረስ አየር መንገዱን ለቆ መሄድ ወይም አየር መንገዱ ከለያቸው ሆቴሎች ውጪ ወደ ከተማ መግባት አይችሉም።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሳምንታት በፊት ሶስተኛው ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እየጀመረ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች እየታዩ እንደሆነ አስታውቋል።
በተለያዩ የዓለም ሀገራት መረጃዎች እና ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሦስተኛው ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱ ታውቋል።
ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው የኮቪድ-19 ዴልታ ቫይረስ ሲሆን በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 የዴልታ ቫይረስ መኖሩ ባይረጋገጥም የሶስተኛ ዙር ወረርሽኝ መከሰቱን የሚያሳዩ ምልክቶች መታየት መጀመራቸውም ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ሁለተኛው ዙር ካበቃ በኋላ በተወሰነ መልኩ በማህበረሰቡ መዘናጋቶች እንዲሁም የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶች በአግባቡ ባለመተግበራቸው ሶስተኛው ዙር ሊከሰት የሚችልበት ምልክቶች እየታዩ ነው።
ተቋሙ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎቹ እንዲከበሩና ማስክ ማድረግ፣የእጅን ንፅህና በአግባቡ መጠበቅ እና ርቀትን በመጠበቅ በተጨማሪም የኮቪድ-19 ክትባት በመከተብ የኮቪድ-19 መከላከከልና መቆጣጠር እንደሚቻልም አሳሳስቧል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተርር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው "ከፊታችን የተጋረጠብንን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ እንዲያልፍ፣ የጥንቃቄ መንገዶችን፣ ክልከላዎችና ግዴታዎች እያንዳንዱ ዜጋ፣ ተቋም፣ አመራር፣ የህግ አስከባሪ አካላት በከፍተኛ የሃላፊነት መንፈስ በመተግበርና በማስፈፀም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ" ማለታቸውም በመግለጫው ላይ ሰፍሯል።
በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ 295 ሺህ 19 ግለሰቦች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 268 ሺህ 252 ግለሰቦች ከኮቪድ-19 ቫይረስ አገግመዋል እንዲሁም 4ሺህ 553 ግለሰቦች በኮቪድ-19 ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል።
አጠቃላይ ክትባት የተከተቡ ሰዎች ቁጥርም 2,335 ሺህ 71 ሲሆን አገሪቷ በአጠቃላይ 3,134 ሺህ 967 ምርመራዎችን አካሂዳለች።