የእስራኤል ጦር በጄኒን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በጀመረው ከፍተኛ ጥቃት ሰዎች ተገደሉ

የእስራኤል ጦር በጄኒን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በጀመረው ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ ዘጠኝ ፍልስጥኤማውያን ሲገደሉ መቶ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ቆሰሉ።

እስራኤል በኃይል በቁጥጥሯ ስር ባደረገችው ዌስት ባንክ በሚገኘው የጄኒን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያም በጦሩ እና እና በታጠቁ የፍልስጥኤም ታጣቂዎች መካከል ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ተደርጓል።

የእስራኤል ጦር በዌስት ባንክ እስካሁን ካደረገው መጠነ ሰፊ የተባለውን ወታደራዊ ዘመቻ ሰኞ የጀመረች ሲሆን ይህም ጥቃት በሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) የታገዘ ነው።

በዚህም ዘጠኝ ፍልስጥኤማውያን ሲገደሉ መቶ መቁሰላቸውን የጤና ባለሙያዎች ተናግረዋል።

እስራኤል በስደተኞቹ የመጠለያ ጣቢያ ላይ የከፈተችውን ጥቃት ጄኒን “የሽብርተኝነት መሸሸጊያ” መሆኗን ለማክተም መሆኑን አስታውቃለች። ፍልስጥኤማውያን በበኩላቸው እስራኤል እየፈጸመችው ያለው የጦር ወንጀል ነው ሲሉ ከሰዋል።

የእስራኤል ጦር እያካሄደ ላለው ወታደራዊ ዘመቻ የያዘው የጊዜ ገድብ ባይኖርም “የሰዓታት ወይም የጥቂት ቀናት ጉዳይ” ሊሆን ይችላል ብሏል።

ጄኒን በፍልስጥኤም አመራር የተሰላቹ እንዲሁም እስራኤል በወረራ በተቆጣጠረቻቸው ግዛቶች ባስቀመጠችው ጥብቅ የቁጥጥር ፖሊሲን የሚቃወሙ የአዲሱ የፍልስጥኤማውያን ትውልፈድ ወጣቶች ማዕከል ሆናለች።

ይህንንም ተከትሎ እስራኤል በአካባቢው ላይ ባለፈው አንድ ዓመት ጦሯ ተደጋጋሚ ወታደራዊ ጥቃቶችን አድርሷል። ጦሩ የፈጸመው ጥቃትም ፍልስጥኤማውያን በእስራኤላውያን ላይ ላደረጉት ከባድ ጥቃት ምላሽ እንደሆነም ተነግሯል። በዚህ ስፍራ ላይ የፍልስጥኤም አጥቂዎች ተደብቀው ይገኛሉም ተብሏል።

በአውሮፓውያኑ 2002 ሁለተኛው የፍልስጥኤም ኢንቲፋዳ ተብሎ በሚጠራው ዘመቻ የእስራኤል ጦር ጄኒን ላይ ሙሉ ወረራ በመፈጸም ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ አድርጓል። ለአስር ቀናት በተካሄደውም ውጊያ ቢያንስ 52 የፍልስጥኤም ታጣቂዎች እና ሲቪሎች እንዲሁም 23 የእስራኤል ወታደሮች ተገድለዋል።

ጦሩ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሩንም ተከትሎ በአሁኑ ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ የእስራኤል ወታደሮች በጄኒን ተሰማርተው ይገኛሉ።

በተጨማሪም የሰው አልባ አውሮፕላኖች ድምጽ እየተሰማ ሲሆን ተደጋጋሚ ፍንዳታዎች እና ተኩሶችንም እያስተናገደች ትገኛለች። 18 ሺህ ያህል ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሆነችው ጄኒን በአሁኑ ወቅት የእስራኤል ጦር ወታደራዊ ዞን ነው በሚል ዘግቷት ይገኛል።