ስድስት እህትና ወንድም በአንድ ቀን የተዳሩበት እና 15 ሠንጋዎች የተጣለበት ሠርግ

የፎቶው ባለመብት, tefri
“ስድስቱን ልጆቼን በአንድ ቀን እድራለሁ የሚል ሃሳብ ቢኖረኝም እንኳ ይሳካልኛል ብዬ አስቤ አላውቅም” ይላሉ አቶ ተፈሪ በላይ።
ቢቢሲ ወደ አቶ ተፈሪ የእጅ ስልክ ላይ በደወለበት ወቅት ስድስት ልጆቻቸውን ድረው፣ በደስታ ባሕር ውስጥ ሆነው ነበር ያገኛቸው።
ግንቦት 28/2014 ዓ.ም. እሁድ ዕለት፣ የወረ ጃርሶዋ ጎሃጽዮን ከተማ በሠርግ እድምተኞች እና በሙሽሮች 'ሃይ ሎጋ ሆ' ደምቃ፣ በእልልታ እና በጭብጨባ ግላ ነው የዋለችው።
ሺህዎች የዕለቱ ታዳሚ ነበሩ፤15 ሠንጋ ደግሞ ለእድምተኞቹ የተዘጋጀ የፍሪዳ ብዛት ነው።
ሠርጉ በቤተሰብ አቅም ብቻ የሚወጡት አልነበረም። አገሬው ወገቡን አስሮ ተፍ ተፍ ብሏል። ያለውን እየያዘ በመምጣት 'ደስታዎ ደስታዬ ነው' ብሏቸዋል።
አቶ ተፈሪም “...ደስታዬ ከአቅሜ በላይ ነው” ይላሉ ስለሁኔታው ሲጠየቁ።
ስድስቱ ልጆቻቸውን በአንድ ቀን የዳሩት የሰሜን ሸዋ ዞኑ የወረ ጃርሶ ወረዳ ቀሬ ጎሃጽዮን ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ተፈሪ በላይ የረዥም ጊዜ ምኞታቸው እና እቅዳቸው እውን መሆኑን ይናገራሉ።
አቶ ተፈሪ የዘጠኝ ልጆች አባት ናቸው።
“ካሉኝ ዘጠኝ ልጆች መካከል ስድስቱ እሁድ ዕለት የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን በአንድ ቀን አከናውነዋል” ብለዋል ለቢቢሲ።
አቶ ተፈሪ በአንድ ቀን የዳሯቸው ሦስት ወንዶች እና ሦስት ሴት ልጆቻቸውን ነው።
ባለፈው ዓመት ቤታቸው ልጅዎትን ለልጃችን ያሉ ሽማግሌዎች መምጣታቸውን ይናገራሉ አቶ ተፈሪ።
ይህ እንግዲህ ለሁለት ሴት ልጆቻቸው መሆኑ ነው። በዚህ ዓመት ደግሞ አንዷ ልጃቸው ላይ አይኑን የጣለ ወጣት፣ ሽማግሌ መላኩን ያስታውሳሉ።
እርሳቸውም ለሦስት የወንድ ልጆቻቸው፣ ልጃችሁን ለልጆቼ በማለት የሴቶችን ቤተሰቦችን በመጠየቅ የሠርጉ ቅድመ ጥንስስ ተጀመረ።
አቶ ተፈሪ ስድስት ልጆቻቸውን በአንድ ቀን ለመዳር ዝግጅት ሲያስቡ ብቻቸውን የሚወጡት አለመሆኑ ገብቷቸዋል።
ለዚያም ነው የጓደኞቻቸውን እና የጎረቤቶቻቸውን ንቁ ተሳትፎ የፈለጉት።
ግንቦት 28/2014 ዓ.ም. በተከናወነው የልጆቻቸው የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይም፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች የተጋበዙ ሲሆን፣ የሠርጉ ሥነ ሥርዓት የተሳካ እንዲሆን ቀደም ብለው የቤተዘምድ ኮሚቴዎችን አዋቅረው እንደነበር ያነሳሉ።
“እነዚህ ኮሚቴዎች የሚበላውን፣ የሚጠጣውን፣ እንዲሁም ሰዎች በሥነ ሥርዓት እንዲስተናገዱ እና ችግሮች እንዳይፈጠሩ፣ የሚከታተሉ ናቸው”ይላሉ የስድስት ሙሽሮች አባት የሆኑት አቶ ተፈሪ በላይ።
“በዚህ ዓይነት ሁኔታ ነው ሁሉንም አመቻችቼ ሁሉም በአንድ ቀን እንዲዳሩ ያደረግኩት” ብለዋል ለቢቢሲ።

የፎቶው ባለመብት, Teferi
‘ይህ እንዲሆን ሳስብ ነበርኩኝ’
አቶ ተፈሪ በላይ ልጆቻቸው በአንድ ቀን እንዲዳሩ የረዥም ጊዜ ዕቅድ እንደነበራቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ይህንን ሃሳብ በማቀርብበት ጊዜ ባለቤቴም ‘ይህ ጉዳይ መልካም ሳይሆን አይቀርም’ በማለት ሃሳቤን ደገፈች” በማለት ከባለቤታቸው ጋር በሃሳቡ ላይ መስማማታቸውን ይናገራሉ።
በዚሁ መሰረት ይህንኑ ሃሳባቸውን ለልጆቻቸው በመንገር ተቀባይነት እንዲያገኝ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።
“ልጆቼ ሥነ ሥርዓት ያላቸው ናቸው። በጣም ነው የምወዳቸው” ይላሉ አቶ ተፈሪ፣ ስድስቱም ልጆቻቸው በአንድ ቀን እንዲዳሩ ያደረጉበትም ምክንያት ለእነርሱ ካላቸው ፍቅር የተነሳ መሆኑን ያስረዳሉ።
“ልጆቼ በሥራቸው በጣም ያስደስቱኛል፤ ሁሉም ይዋደዳሉ። ከዚህም የተነሳ የጋብቻ ሥነ ሥርዓታችሁ በአንድ ቀን ይፈፀማል ብዬ ነገርኳቸው። እግዚአብሔርም ረድቶኝ አንዳሰብኩት ተከናወነልኝ” ብለዋል።
አስራ አምስት ሠንጋዎች እና ትልቅ ወጪ

የፎቶው ባለመብት, Teferi
የአቶ ተፈሪ ልጆችን ለመዳር ተፍ ተፍ የሚለው ሰው ቁጥር ስፍር ያለው አይመስልም።
የሠርጉ እድምተኛ ለመሆን የተጠራውም የስድስት ቤተሰብ አባል ነው።
የተጠራው ሁሉ በልቶ ተጫውቶ እንዲሄድ አቶ ተፈሪ ያዋቀሩት ኮሚቴ በጋራ የሚጠበቅበትን ተወጥቷል።
ለልጆቻቸው የሠርግ ሥነ ሥርዓት ሰፊ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን የሚናገሩት አቶ ተፈሪ በላይ፣ የሠርጉ ወጪም ቢሆን የዚያኑ ያህል ከባድ እንደነበር ይናገራሉ።
“ወጪው ከባድ ነበር። ይህም ቢሆን ግን የግድ ማድረግ ስለነበረብኝ የሚያስፈልገውን ሁሉ በማውጣት፣ የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱን ማከናወን ችያለሁ” ብለዋል።
ምን ያህል ገንዘብ አወጡ? ቢቢሲ አጥብቆ የጠየቀው ጥያቄ ነበር "ወጪው ከባድ ነበር" ከማለት ውጪ በቁጥር አስረግጠው መናገር አልፈለጉም።
በተጨማሪም የአካባቢው ማኅበረሰብ ያደረገላቸው ድጋፍም ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ።
“ሕዝቡ እኔ ይህንን እገዛለሁ፣ እኔ ይህንን አደርጋለሁ በማለት ተከፋፍለው የነበረብኝን ሸክም አቅልለውልኛል” በማለት ከአካባቢያቸው ሕብረተሰብ የተደረገላቸውን ድጋፍ ይገልጻሉ።
“መልካም ባህል አለን፤ ሕዝባችን እርስ በእርስ በመረዳዳት ረገድ ቀዳሚ ነው ለማለት እችላለሁ። ግማሹ በግ ገዝቶ ይመጣል፣ ግማሹ ጠጅ፣ ጠላ፣ ሌላኛው አረቄ በመያዝ የሚያስፈልገውን ነገር ይዞ ነበር የመጣው” በማለት የነበረውን ድጋፍ ይገልጻሉ።
በአንድ ቀን ለተከናወነው የስድስት ልጆቻቸው ሠርግ 15 ሠንጋ አዘጋጅተው የነበሩት አቶ ተፈሪ፣ ከእነዚያ መካከልም አስሩ እሁድ ለነበረው እድምተኛ መሸኛ መታረዳቸውን ይናገራሉ።
የተቀሩትም ሠንጋዎች በተከታታይ ቀናት በሚኖረው ዝግጅት ላይ ቀስ በቀስ የሚታረዱ ይሆናሉ ብለዋል።
በመጨረሻም አቶ ተፈሪ የተቀሩትን ሦስት ልጆቻቸውን በአንድ ቀን ለመዳር እቅድ እንዳላቸውም ተናግረዋል።
እኛም ‘የዛሬ ዓመት የሚሚዬ/የማሙሽ አባት፣ ለክርስትና እንመጣለን ገና’ ብለናል።












