የሲሚንቶ ግብይት በነፃ ገበያ መወሰኑ አቅርቦቱን እና ዋጋውን ያረጋጋው ይሆን?

ግንባታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሲሚንቶ ለሁሉም የግንባታ ሥራዎች ዋነኛ ግብዓት ነው

በፈረንጆቹ 2019 በኢትዮጵያ የሲሚንቶ ፍላጎት 12 ሜጋቶን (12 ቢሊዮን ኪሎ ግራም) ሲደርስ የነበረው አቅርቦት ግን 8.9 ሜጋቶን ገደማ ነበር።

የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ጥናት ተቋም ዘገባ ጨምሮ እንደሚጠቁመው ኢትዮጵያ እስከ 20 ሜጋቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም አላት።

የኢትዮጵያ መንግሥት በፈረንጆቹ 2020-21 የበጀት ዓመት ለመንገድ እና ድልድይ ግንባታ 58.8 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ሲሚንቶ ጥቅም ላይ አውሏል።

ኢትዮጵያ የውጭ አገር ድርጅቶች በሲሚንቶ ማምረት ሥራ ላይ ጥላው የነበረውን እገዳ ያነሳችው የካቲት 2020 ነበር።

በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ 17.1 ሜጋቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም አላት ሲል ኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ጥናት ተቋም ዘግቦ ነበር።

ነገር ግን አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ የሲሚንቶ እጥረት እንዳለ ነው።

ከሦስት ዓመት በፈት ለሲሚንቶ እጥረት ዋነኛው ምክንያት የነበረው የነዳጅ እጥረት ነበር። ይህን ለመቅረፍ በወቅቱ የንግድ ሚኒስቴር የ50 ኪሎ ግራም ሲሚንቶ ዋጋ ከ450 ብር እንዳይበልጥ የሚል ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም።

ይህ የዋጋ ተመን ከወጣ በኋላ 50 ኪሎ ግራም ሲሚንቶ ዋጋ ከ200 - 250 ብር ሲሸጥ እንደነበርም ይታወሳል።

ምንም እንኳ በቅርቡ መንግሥት የሲሚንቶ ዋጋን ተመን አውጥቶ በአማካይ 50 ኪሎ ሲሚንቶ ከ600 ብር ባልበጠ ዋጋ እንዲሸጥ ቢወስንም ከ2000 ብር በላይ ሲሸጥ ቆይቷል።

የሲሚንቶ ዋጋ ይበልጥ እንዲንር ካደረጉት ምክንያቶች አንደኛው ግዙፍ የሚባሉ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሚገኙበት የኦሮሚያ ክልል ያለው የፀጥታ ሁኔታ ነው።

ይህን የሲሚንቶ ዋጋ ንረት ተከትሎ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሲሚንቶ ሽያጭ በነፃ ገበያ እንዲሰራ ወስኗል።

የሲሚንቶ ነፃ ገበያ ምን ማለት ነው? ይህ መመሪያ የሲሚንቶ ገበያን ያረጋጋው ይሆን?

የሲሚንቶ ‘ነፃ ገበያ’

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የምጣኔ ሃብት ሳይንስ ‘ነፃ ገበያ’ ማለት አቅራቢው እና ተጠቃሚው በፍላጎት በሚመሰርቱት ሕግ መሠረት የሚገበያዩበት መስክ ነው ይላል።

በዚህ የነፃ ገበያ ምጣኔ ሃብት የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ላይኖር አሊያም በጣም አናሳ ሊሆን ይችላል።

የሲሚንቶ ገበያ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ውስጥ በነፃ ገበያ መርህ ይተዳደር እንደነበር የሚያስታውሱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ሃብት ምሑር ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) ናቸው።

“ሲሚንቶ ለኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት ነው” የሚሉት ምሑሩ በተለይ ኢትዮጵያ በኢንደስትሪው ዘርፍ ለመላቅ ለምታደርገው ጥረት ሲሚንቶ አስፈላጊው ምርት እንደሆነ ይናገራሉ።

“ለዚህ ነው ከዚህ ቀደም የነበረው አመራር (ኢሕአዴግ) ሲሚንቶ በብዛት እንዲመረት፤ ከውጭ ማስገባት የሚፈልጉ ደግሞ ከቀረጥ ነፃ በገፍ እንዲያስገቡ ፈቅዶ የነበረው።”

ደርብ ተካ አዲስ አበባ ውስጥ በተለምዶ 22 ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲሚንቶ በችርቻሮ በመሸጥ ይተዳደራል።

ከዚህ ቀደም መንግሥት ቸርቻሪዎች ሲሚንቶ እንዳይገዙ እና እንዳይሸጡ በከለከለበት ወቅት እሱና መሰል ቸርቻሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ገዢዎችም እጅግ ተጎድተው እንደነበር ያወሳል።

“ይህ መመሪያ በወጣ ሰሞን አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ከ2 ሺህ ብር በላይ ሲሸጥ ነበር። ‘ነፃ ገበያ’ ከተባለ በኋላ ግን በሦስት እና በአራት ቀናት ውስጥ ዋጋው ኪ1 ሺህ እስከ 1 ሺህ 500 ወርዶ መሸጥ ጀምሯል። በጅምላ ለሚገዙ ደግሞ ዋጋው ከዚህም በላይ ወርዷል።”

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ዋጋውን ለማረጋጋት ፋብሪካዎች የራሳቸውን ዋጋ እንዲተምኑ ጠይቆ ፋብሪካዎቹ ያወጡት ዋጋ ከፍተኛ መሆኑን ካስተዋለ በኋላ እንደሆነ ገልጿል።

ይህንን ተከትሎ ሚኒስቴሩ የሲሚንቶ ዋጋ ዝቅተኛው 510 ብር ከፍተኛው ደግሞ 683 ብር እንዲሆን በቅርቡ ወስኖ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም።

መንግሥት ከዚህ ቀደም የሲሚንቶ ምርት ዝቅተኛ በመሆኑ ለመንግሥታዊ ፕሮጅከቶች ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል የሚል ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር።

ደርብም ሆኑ ሌሎች የሲሚንቶ አከፋፋዮች ኢትዮጵያ ውስጥ በቂ የሲሚንቶ ምርት አለ ብለው ያምናሉ፤ ዋጋውም ከዚህ በታች ይወርዳል የሚል ተስፋ አላቸው።

“እኔ የማውቃቸው የችርቻሮ ነጋዴዎች የሲሚንቶውን ዋጋ አውርደው እየሸጡ ነው። እኔ ግን ገና አልጀመርኩም። ዋጋው ተረጋግቶ ምናልባት 1 ሺህ ብር አካባቢ ሲደርስ መሸጥ እጀምራለሁ።”

ደርብ ደንበኞች እንዲረጋጉ እየመከረ ነው። “አንዳንድ ጊዜ ፋብሪካዎች ምርታቸውን ይይዙታል፤ ስለዚህ ትንሽ ረጋ በሉ እያልኩ ነው” ይላል።

ግንባታ

የፎቶው ባለመብት, iStock

“የሲሚንቶ ድርቅ ገብቶ ነበር”

የኢትዮጵያ ሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር ፕሬዝዳንት ኃይሌ አሰግዴ ‘ነፃ ገበያ’ ቢባልም አሁንም ሲሚንቶው እየተሸጠ ያለው መንግሥት ባስቀመጠው ተመን ነው ይላሉ።

በምድራችን በብዛት ጥቅም ላይ ከሚውሉ የተፈጥሮ ትሩፋቶች አንዱ የሆነው ሲሚንቶ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ዋጋው ሊንር የቻለው የአቅርቦት ሰንሰለቱ ‘ስለተጠለፈ’ ነው የሚሉት ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) ናቸው።

እሳቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከዚህ ቀደም ምርታቸውን ይሸጡ የነበረው ገበያው በሚተምነው ዋጋ ነው።

ነገር ግን ባለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት ነፃ ገበያ የሚባለው ተነስቶ “ባለሥልጣናት ምርቱ እንዲጠፋ እና ዋጋው እንዲንር ማድረጋቸው ግርምት ፈጥሮብኛል” ይላሉ።

“እንዴት ሆኖ ነው ሲሚንቶን የሚያክል ነገር ከነፃ ገበያ ወጥቶ መንግሥት እንደ ስኳርና ዘይት የሚያከፋፍለው?” የሚል ጥያቄ አላቸው።

ምሑሩ እንደሚሉት አንዳንድ የፌዴራል እና የክልል ባለሥልጣናት የሲሚንቶ ገበያውን ሰንሰለት በመቆጣጠራቸው “ሲሚንቶ መንግሥት ነው የሚሸጠው” ለማለት የሚያስደፍር አካሄድ ነበር።

“ይህን በምጣኔ ሃብት ‘ሞኖፖሊ’ እንለዋለን። አንድ ነጋዴ፣ አንድ አቅራቢ ብቻ ሲሸጥ ‘ሞኖፖላይዝድ’ ሆኗል ማለት ነው። እንዴት ሁሉንም የሲሚንቶ ፋብሪካ ጨፍልቆ ‘ሞኖፖላይዝ’ እንዳደረገው በጣም ጥያቄ የሚፈጥር ነገር ነው።”

እንደሳቸው እምነት አሁን መንግሥት ተመልሶ ወደ ነፃ ገበያው ያመራው ‘በሞኖፖሊ’ የተያዘው ገበያ የሲሚንቶ ዋጋ እንዲንር፤ የሥራ አጥንት እንዲስፋፋ እና የኮንስትራክሽን ዘርፉ እንዲጎዳ በማድረጉ ነው።

የአምራቾች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ኃይሌ እንደሚሉት ከዚህ ቀደም ቸርቻሪዎች እንዳይሸጡ በመከልከሉ ትላልቅ የመንግሥት ፕሮጅከቶች ብቻ ነበሩ ሲጠቀሙ የነበሩት።

አዲሱ መመሪያ የወጣው ይህንን ችግር ለመፍታት ነው ብለው የሚያምኑት ፕሬዝዳንቱ ይህም “ኬላዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር እና ማንም እየተነሳ የሚወስነው ውሳኔን ያስቀራል” የሚል ተስፋ አላቸው።

የማኅበሩ ፕሬዝዳንት እንደሚሉት ለገበያው መረጋጋት ቁልፉ ጉዳይ በተለያዪ አካባቢዎች የሚመረተው ሲሚንቶ እንደልብ መንቀሳቀስ መቻሉ ነው።

አዲሱ አመራር መሠረት ፋብሪካዎች እና አከፋፋዮች ከሲሚንቶ ምርት ላይ ማትረፍ የሚችሉት የገንዘብ መጠን ተተምኗል።

“አንድ ከፋብሪካ የሚወስድ አከፋፋይ በፋብሪካው ዋጋ ላይ እስከ 10 በመቶ ነው መጨር የሚችለው። በችርቻሮ የሚሸጡ ደግሞ ሁሉንም ወጪያቸውን ሸፍነው እስከ 15 በመቶ ነው ዋጋ መጨመር የሚችሉት።”

የቦካ ሲሚንቶ

የፎቶው ባለመብት, iStock

ነፃ ገበያው ለተጠቃሚው ይጠቅማልን?

ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) ሲሚንቶ በነፃ ገበያ መርህ እንዲመራ መደረጉ ገዢዎችን ቢጠቅም እንጂ አይጎዳም የሚል እምነት አላቸው።

አቶ ኃይሌ አሰግዴም፤ አዲሱ መመሪያ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ምርታቸውን ከፋብሪካ እንዲያገኙ ትናንሽ ፕሮጀክቶች ደግሞ ከአከፋፋዮች በተመጣጠነ ዋጋ እንዲያገኙ ያስችላል ብለው ያስባሉ።

“በበፊቱ አሰራር ሲሚንቶ በችርቻሮ የሚሸጡ፣ ብሎኬት የሚያመርቱ፣ ኮንትራክተሮች ሲሚንቶ እንደልብ ስለማያገኙ ከጥቁር ገበያ ነበር የሚገዙት። ከፋብሪካው በ600 ብር የወጣ ሲሚንት እስከ 2 ሺህ ብር ሲሸጥ ነበር ይላሉ።”

መንግሥት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የሲሚንቶ ዋጋን ለማረጋጋት የተለያዪ እርምጃዎች ቢወስድም ዋጋው በፊት ከነበረበት በላቀ ሲያሻቅብ እንደነበር የሚናገሩት ጉቱ (ዶ/ር) አዲሱ እርምጃ በተገቢው መንገድ ከተተገበረ ስኬታማ ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ።

ነገር ግን በሲሚንቶ ግብይት ሰንሰለት ውስጥ እጃቸው ያለበት ሰዎች ነፃ ገበያውን እንዳያበላሹት ስጋት አላቸው።

“የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጡንቻ ላዳበሩ ግለሰቦች የሲሚንቶ ገበያው የሚታለብ ላም ማለት ነው። በአንድ ሌሊት ባለብዙ ሚሊየነር የሚያደርግ ነው። ስለዚህም በእውነት የሲሚንቶ ገበያ በነፃ እንዲመራ ይተዉታል የሚለው ነገር ጥርጣሬ ይፈጥራል።”

ለሲሚንቶ አምራቾች ፕሬዝዳንት ሌላው ተስፋ ሰጪ ጉዳይ ትግራይ ክልል የሚገኘው የመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ በቅርብ ወደ ሥራ ሊመለስ መቻሉ ነው።

ኃይሌ፤ እንደሚሉት መሰቦ በቅርቡ ወደ ምርት የሚገባ ከሆነ በጎንደር እና በአፋር በኩል ያለውን የሲሚንቶ ፍላጎት ሊያሟላ ይችላል።

“ፋብሪካዎች ከመንግሥት ድጋፍ ካገኙ፣ ሲሚንቶው እንደልብ መንቀሳቀስ ከቻለ፣ ፋብሪካዎች በራሳቸው ማከፋፈያ እንዲሸጡ መፈቀዱ ታክሎበት ዋጋው ቢቀንስ እንጂ አይጨምርም።”

ምሑሩ ግን ይህ የነፃ ገበያ መርኅ ስኬታማ እንዲሆን የመንግሥት ቁርጠኝነት ቁልፍ ጉዳይ ነው።

“ከተራ ደላላ እስከ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ድረስ ነው ከሲሚንቶ ገበያው የሚጠቀሙት። ይህ ሰንሰለት ተበጥሶ የተሻለ የገበያ ሥርዓት ሊመሰረት ይችላል ወይ? መንግሥትስ ይህን ነገር ተግባራዊ እንዲሆነ ቁርጠኝነት አለው ወይ? አቅምስ አለ ወይ?” የሚሉት ዋነኛ ጥያቄዎቻቸው ናቸው።