በአማራ ክልል መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት መካከል "ዘላቂ የሰላም ስምምነት" ተፈረመ

የፎቶው ባለመብት, amco
በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ የፋኖ ቡድኖች አንዱ የሆነው የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ከክልሉ መንግሥት ጋር የዘላቂ ሰላም ስምምነት መፈራረሙ ተገለጸ።
የሰላም ስምምነቱ እንዲፈረም በማደራደር የአፍሪካ ኅብረት እና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) መሳተፋቸውም ተነግሯል።
ስምምነቱን የተፈራረሙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ እና ከአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት በኩል አቶ ማስረሻ ሰጤ መሆናቸው ታውቋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መሰተዳደር በስምምነቱ ወቅት ዕለቱን "ለክልላችን ሕዝብ የመጀመሪያው ትልቅ የሰላም ኩነት የተካሄደበት ቀን ነው" ሲሉ ካፕቴን ማስረሻ ሰጤ ደግሞ "ማንኛውም ግጭት መጨረሻው ውይይትና ድርድር ነው" ማለታቸውን ተዘግቧል።
እንዲሁም ከአሸማጋዮቹ አንዱ የሆነው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር አምባሳደር ሰልማ ማሊካ አዳዲ ስምምነቱ የአገሪቱን ቀጣይ መዳረሻ የሚያቃና ነው ሲሉ መናገራቸው ተገልጿል።
ከአምስት ቀን በፊት የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ሁለት አመራሮች ከሌሎች አባሎቻቸው ጋር ለመንግሥት እጃቸውን መስጠታቸው ሲዘገብ ነበር።
እጃቸውን ሰጡ ከተባሉት ኃላፊዎች መካከል አሁን ከአማራ ክልል መንግሥት ጋር ዘላቂ የሰላም የተፈራረሙት ካፕቴን ማስረሻ ሰጤ ይገኙበታል።
የመንግሥት አሁን የአማራ ክልል መግለጫውን እስኪያወጣ ድረስ በጉዳዩ ላይ ምንም ያለው ነገር አልነበረም።
ከዚህ በፊት የአፋሕድ መሪ እንደሆኑ የሚነገረው አቶ እስክንድር ነጋ ከአፍሪካ ኅብረት፣ ከምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ)፣ ከአውሮፓ ኅብረት እንዲሁም በኢትዮጵያ ከአሜሪካ ኤምባሲ ተወካዮች ጋር ስፍራው ባልተገለጸ የክልሉ አካባቢ ተገናኝተው መወያየታቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች ወጥተው እንደነበር ይታወሳል።
በወቅቱ አቶ እስክንድር ከፌዴራል መንግሥት ጋራ መደራደር የሚለው ጉዳይ በውይይቱ ወቅት እንዳልተነሳ ገልጸው ነበር።
አሁን ድርጅቱን ወክለው ከክልሉ መንግሥት ጋር ስምምነት የፈረሙት ካፕቴን ማስረሻ ሰጤ ሲሆኑ፣ በዚህ ስምምነት ውስጥ አቶ እስክንድር የነበራቸው ሚና አልተገለጸም።
ስምምነቱ የክልሉ መንግሥት ለሰላም የሰጠው አማራጭ አካል እንደሆነ እና ለቀጣይ የሕዝብ ሰላማዊ እፎይታ መሠረት የሚጥል ነው ተብሏል።
ባለፈው ሳምንት የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ሁለት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላቱን "ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል" በሚል ማባረሩ በስፋት ሲዘገብ ነበር።
የድርጅቱ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ናቸው የተባሉት አቶ አሻግሬ ባየህ መቀመጫቸውን በአሜሪካ ላደረጉ የዩቲዩብ ሚዲያዎች ኃላፊዎቹ የታገዱት ከመንግሥት "ተልዕኮ ተቀብለው" በመገኘታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
"የታገዱት ኃላፊዎች በጎጃም የአማራ ፋኖ ሊቀመንበር እና የድርጅቱ የውጭ ጉዳዮች ኃላፊ ማስረሻ ሰጤ እና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና በወሎ የደኅንነት ኃላፊ የሆኑት መስፍን ከፋለ ናቸው" ብለዋል።
የተባረሩበት ዋና ምክንያትን ሲጠቅሱ "ከመንግሥት ጋር ግንኙነት መፍጠራቸው እና ተልዕኮ መቀበላቸው ስለተደረሰበት" መሆኑን ተናግረዋል።
በግለሰቦቹ ላይ የተገኘው ማስረጃ ይፋ ከሆነ በኋላ "ከእኛ ጠፍተዋል የት እንዳሉ አናውቅም" ሲሉ ከዩቲዩብ ገፁ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ወቅት ገልፀዋል።
አሁን ከአማራ ክልል ጋር የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅትን ወክለው የሰላም ስምምነት ፈርመዋል የተባሉት ካፕቴን ማስረሻ ሰጤ የቀድሞ የአየር ኃይል አባል ነበሩ።
ከዚህ በፊት በመንግሥት ቁጥጥር ስር በነበሩበት ወቅት በቅሊንጦ ማረሚያ ቤት ከተከሰተ የእሳት ቃጠሎ ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት በሚል ተወንጅለው ነበር።
ከእስር ከተፈቱ በኋላ በአማራ ፖለቲካ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ያጠናከሩት ካፕቴን ማስረሻ ሰጤ በወሎ በነበረው የፋኖ አንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው ይነገራል።
በኋላም ከአቶ እስክንድር ነጋ ጋር በመሆን የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅትን መሥርተው በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።
አሁን ከክልሉ መንግሥት ጋር የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት መንግሥት በክልሉ ታጥቀው ለሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በተደጋጋሚ መሣሪያቸውን አስቀምጠው ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲገቡ ለሚያቀርበው ጥሪ እንደ ከፍተኛ ድል ሊቆጥረው ይችላል።
መንግሥት በአገሪቱ የሚገኙ ታጣቂዎችን በትኖ በፌዴራል መንግሥቱ ኃይል ሥር ለማካተትና ወደ ማኅበረሰቡ መልሰው እንዲቀላቀሉ ለማድረግ መወሰኑን ተከትሎ፣ በፋኖ ታጣቂዎች እና በፌዴራል መንግሥት ኃይሎች መካከል በሚያዚያ 2015 ግጭት ተቀስቅሷል።
በዚያው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ መንግሥት 23 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ በሚኖርበት በአማራ ክልል አስቸኳይ ጊዜ አውጇል።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በሚደረጉ ውጊያዎች በርካቶች ቤት ንብረታችን እንዲሁም ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በተለያየ የአማራ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱት የፋኖ ታጣቂዎች በተለያየ አመራር ሥር ሆነው የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፣ ወጥ የሆነ የጋራ አመራር የላቸውም።















