ታግቶ የተወሰደው የመተማ ሆስፒታል ሐኪም የተጠየቀው ገንዘብ ቢከፈልለትም ተገድሎ ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, Family
በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ከመተማ አጠቃላይ ሆስፒታል አካባቢ ታፍኖ የተወሰደ የሕክምና ባለሙያ የተጠየቀው ገንዘብ ቢከፈልም መገደሉን የቤተሰብ አባላት ለቢቢሲ ተናገሩ።
በመተማ አጠቃላይ ሆስፒታል የዓይን ሕክምና (ኦፕቶሜትሪ) ነርስ የነበረው አቶ ዳንኤል ነጋ ጥቅምት 19/2018 ዓ.ም. ማታ እራት እየበላ ከነበረበት ምግብ ቤት በታጣቂዎች ታግቶ ከተወሰደ በኋላ 3.5 ሚሊዮን ብር እንዲከፍል ተጠይቆ አንደነበር የቤተሰቡ አባል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ገንዘብ በመጠየቅ ከተፈጸመው እገታ በኋላ ተገድሎ የተገኘው ባለትዳር እና የልጆች አባት የሆነው ነርስ ዳንኤል በሆስፒታሉ ጥቂት ባለሙያዎች ባሉበት ዘርፍ ታታሪ ሠራተኛ እንደነበር ባልደረቦቹ ገልጸዋል።
ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የሟች ቤተሰብ ጥቅምት 19/2018 ዓ.ም. ሟች አቶ ዳንኤል አዳሪ ሠራተኛ እንደነበር እና ከምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ "እራት በልቼ ልምጣ" ብሎ ከሆስፒታሉ መውጣቱን መስማታቸውን ተናግረዋል።
በሆስፒታሉ ዋና በር አካባቢ ሁልጊዜ ምግብ የሚበላበት ቤት ውስጥ እየተመገበ እያለ ስድስት መሣሪያ የያዙ ታጣቂዎች መጥተው እንደወሰዱት መስማታቸውን ጨምረው አስረድተዋል።
በተወሰደበት ምሽት አጋቾቹ ለባለቤቱ ደውለው መታገቱን መናገራቸውን እና ጠዋት ደግሞ ሌሎች ዘመዶች ስለሁኔታው መስማታቸውን ይናገራሉ።
አጋቾቹ ለባለቤቱ በደወሉበት ወቅት "ሕይወቱን የምትፈልጉ ከሆነ 3.5 ሚሊዮን ብር አምጡ" ብለው ሲጠይቁ መስማታቸውን ገልጸዋል።
አክለውም የሟች አቶ ዳንኤል ነጋ አጋቾቹ የሚያናግሩት ባለቤቱን እና ወንድሙን ብቻ መሆኑን ገልጸው የሚጠቀሙትም የእርሱን ስልክ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።
ባለቤቱ የተጠየቀችውን 3.5 ሚሊዮን ብር እንደሌላት ስትናገር "አጥንተን ነው የያዝነው። ብር አላችሁ። ጎንደር ቤት አላችሁ። ሕይወቱን የምትፈልጊው ከሆነ ቶሎ ክፈይ አሏት" ይላሉ።
የሟች ባለቤት አቶ ዳንኤልን ለማስለቀቅ ከወዳጅ ዘመድ ጋር በመሆን ብር ማፈላለግ መጀመራቸውን ገልፀዋል።
ብሩን እያፈላለጉ ምን ያህል እንደደረሰላቸው ለአጋቾቹ በየጊዜው ይናገሩ እንደነበር የሚያስረዱት የሟች ዘመድ "አሁን 150 ሺህ ብር ደርሰናል፣ ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር ደርሰናል እያልን እያሳወቅናቸው ሰነበትን" ብለዋል።
በመሃል አጋቾቹ አቶ ዳንኤል ባለቤቱን እንዲያነጋግር ያደርጉ እንደነበር የተናገሩት እኚህ የቤተሰቡ አባል 'እያሰቃዩኝ ስለሆነ ቶሎ በሉ እባካችሁ' እንዳላቸው ተናግረዋል።
ቤተሰቡ የሚያሰባስበው ገንዘብ 250 ሺህ ብር ሲደርስ ደውለው የደረሱበትን ባሳወቁበት ወቅት "አንድ ሚሊየን ሳትይዙ እንዳትደውሉ" ብለዋቸው ነበር።
በተለያዩ አካባቢ የሚገኙ ጓደኞቹ የቴሌግራም ቡድን በመክፈት ብር ማሰባሰባቸውን እና ወደ 500 ሺህ ብር ሲደርሱ ባለቤቱ ለአጋቾቹ በድጋሚ ደውላ አሳውቃለች።
ባለፈው ሳምንት አርብ አጋቾቹ "ስድስት መቶ ሺህ ብር ክፈሉ እና ሰውየውን መውሰድ ትችላላችሁ" በማለት መልዕክት አስተላልፈው ነበር።
ከዚያ በኋላ የተሰበሰው ብር 500 ሺህ ብር ደርሶ ስለነበር ሕይወቱን እናትርፈው በሚል ብድር ተፈልጎ የተጠየቀውን ስድስት መቶ ሺህ ብር ማስረከባቸውን ገልጸዋል።
ቤተሰቡ ይህ በሚሆንበት ወቅት ለፖሊስ ሄዶ አለማመለክቱን የሚናገሩት የቤተሰብ አባሉ፣ ባለቤቱ ጎንደር ቤት ተከራይታ እንደምትኖር፣ የታጋች ቤተሰቦች ጭልጋ መሆናቸውን እርሱ የታገተበት ስፍራ ደግሞ ገንዳውሃ የሚባል አካባቢ በመሆኑ ይህንን ለማድረግ አለመቻሉን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም አብረውት ከሚሠሩ የሥራ ባልደረቦቹ የአካባቢው ፖሊስ የምግብ ቤቱን ባለቤት፣ አብሮት ምግብ እየተመገበ የነበረውን ግለሰብ እንዲሁም የተወሰነ ባልደረቦቹን በቁጥጥር ስር አውሎ እንደነበር መስማታቸውን አስረድተዋል።
በዚህ የተነሳ የፀጥታ አካላት ክትትል እያደረጉ ነው በሚል ምንም ዓይነት እርምጃ አለመውሰዳቸውን ይናገራሉ።
ባለፈው ሳምንት አርብ ዕለት የተጠየቀው 600 ሺህ ብር ከተከፈለ በኋላ ግለሰቡ ሳይለቀቅ በመቅረቱ እስከ እሁድ ድረስ በትዕግሥት ሲጠባበቁ ነበር።
ነገር ግን ሰኞ ዕለት የሕክምና ባለሙያው ነርስ ዳንኤል በታገተበት አካባቢ ተገድሎ የተጣለ ሰው መኖሩን የሰሙ ሰዎች ከአካባቢው ሚሊሻዎች ጋር በመሆን ወደ ስፍራው በሄዱበት ጊዜ ተገድሎ አስከሬኑን አግኝተዋል።
አስከሬኑን አንስቶ ወደ ቤተሰብ ለማምጣት ባለመቻሉ እዚያው እንደተቀበረ የሚናገሩት የቤተሰቡ አባል ባለቤቱ መሞቱን እንደሰማች ታምማ ሆስፒታል መግባቷን ገልፀዋል።
አቅመ ደካማ ወላጆቹን፣ ወንድሞቹን እና ቤተሰቡን የሚረዳ "የቤተሰቡ ዓይን የነበረ ሰው ነው" በማለት "ከሥራ ቦታ መታገቱ፣ ገንዘብ ከተከፈለ በኋላ መገደሉ፣ የተገደለበት ቦታ እዚያው መቀበሩ" ለቤተሰቡ ሐዘኑን ድርብርብ ማድረጉን አብራርተዋል።
የሁለት ልጆች አባት የሆነው አቶ ዳንኤል በመተማ አጠቃላይ ሆስፒታል ብቸኛው ኦፕቶሜትሪ ነርስ (የዓይን ሕክምና) ባለሙያ እንደነበር ተናግረዋል።
ነርስ ዳንኤል በመተማ አጠቃላይ ሆስፒታል ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሞተበት ቀን መሥራቱንም ጨምረው አስረድተዋል።
በአካባቢው ከዚህ በፊትም ታግተው የነበሩ እና የተጠየቀውን ክፍያ ከተከፈለ በኋላ የተገደሉ ሌሎች ሰዎችም መኖራቸውን የሚናገሩት ግለሰቡ፣ የሆስፒታሉ አምስት ባልደረቦችም በተለያየ ጊዜ ታግተው መለቀቃቸውን መስማታቸውን ገልጸዋል።















