እስራኤል ለ14 ዓመታት በአገሯ የኖረን የኤርትራ መንግሥት ደጋፊን አባረረች

የተባረረው ኤርትራዊ ፊቱ ተሸፍኖ

የፎቶው ባለመብት, Population & Immigration Authority

ወደ እስራኤል በሕገወጥ መልኩ የገባ እና የኤርትራ መንግሥትን በመደገፍ ይታወቃል የተባለ ኤርትራዊ ሰኞ ዕለት ወደ አገሩ መባረሩን የእስራአል መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

እስራኤል የኤርትራ ዜግነት ያለው እና የመንግሥት ደጋፊ የሆነን ግለሰብ ከአገሯ ስታባርር ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል።

የአንድ ልጅ አባት የሆነው ኤርትራዊ ወደ እስራኤል የገባው በአውሮፓውያኑ 2011 ነሐሴ ወር ሲሆን፣ ላለፉት 14 ዓመታት ኑሮውን በዚያው አድርጎ ቆይቷል

ስሙ በይፋ ያልተገለጸው ግለሰቡ በእስራኤል ፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ገጀራ ይዞ በመገኘቱ ነበር።

በአውሮፓውያኑ ሚያዚያ ወር 2025 ላይ የድንበር ቁጥጥር ፖሊሶች ፍርድ ቤት በማቅረብ ጉዳዩ እንዲታይ አድርገዋል።

ግለሰቡ ገጀራ ይዞ ከመገኘት በተጨማሪ ከትዳር አጋሩ ጋር የተፋታ መሆኑ ተገልጾ ቤተሰቦቹ ላይ ማስፈራሪያ እና ዛቻ በማድረስም ተጠርጥሯል።

ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ ወደ ስደተኞች ማቆያ ማዕከል ተልኮ ነበር።

በማቆያ ውስጥ ሳለ የኤርትራ መንግሥት ደጋፊ መሆኑ ግልጽ ሆኖ በመገኘቱ እንዲሁም ጉዳዩን በሚመለከት የሌሎች ሃሳብ ከተሰማ በኋላ ከአገር እንዲባረር ተወስኗል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሰኞ ዕለት ማለዳ የእስራኤል የኢሚግሬሽን ባለሥልጣን ወደ አሥመራ በሚሄድ አውሮፕላን ላይ እንዲሳፈር አድርገውታል።

ኤርትራዊውን የያዘው አውሮፕላን አሥመራ ከመድረሱ በፊት አዲስ አበባ እና ካምፓላ ማረፉ ተሰምቷል።

ኤርትራውያንን ጨምሮ በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች በግብፅ በኩል ድንበር በማቋረጥ እስራኤል ገብተው ይኖራሉ።

እነዚህ ስደተኞች እስራኤል በበረሃማው ድንበሯ ላይ አጥር ከመገንባቷ በፊት ወደ አገሪቱ የገቡ ናቸው።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር በሁለት ኤርትራውያን ቡድኖች መካከል በቴል አቪቭ በተፈጠረ የጎዳና ላይ ግጭት ሁለት ሰዎች ተገድለዋል።

በእስራኤል ከሁለት ዓመታት ገደማ በፊት በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች እና በተቃዋሚዎች መካከል በተነሳ ግርግር እንዲሁም ከፖሊስ ጋርም በተፈጠረው ግጭት ከ170 በላይ ሰዎች ቆስለዋል።

በርካቶች ተጎድተውበታል እንዲሁም ከፍተኛ የንብረት መውደም ተከስቶበታል በተባለውም በዚህ ግርግር ተሳትፈዋል የተባሉ ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎችን በአስቸኳይ ከአገር ማባረርን ጨምሮ ጠንከር ያለ እርምጃም ይወሰድባቸዋል ተብሎ ነበር።

በእነዚህ ግጭቶች ከሁለቱም ወገን ሰዎች የተጎዱ ሲሆን በርካቶችም በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ነበር።

በ2015 ዓ.ም. ነሐሴ ወር ላይ ኤርትራውያኑ ከባድ ሁከት ፈጥረው በፖሊስ እና በንብረት ላይ ጉዳት ካደረሱ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ አፍሪካውያን ስደተኞችን በሙሉ 'በአስቸኳይ' ከእስራኤል ለማባረር ዕቅድ እንዲወጣ ትዕዛዝ እስከመስጠት ደርሰው ነበር።

ከዚያ በኋላም የእስራኤል ፓርላማ መንግሥታቸውን የሚደግፉ የኤርትራ ስደተኞችን ከአገር ለማባረር ያለመውን ረቂቅ ሕግ አሳልፏል።

ክኔሴት ተብሎ የሚጠራው የእስራኤል ፓርላማ ኤርትራውያን ስደተኞችን ከአገር ለማባረር ያለመውን ረቂቅ ሕግ የመጀመሪያ ዙር ያለምንም ተቃውሞ ባሳለፈበት ወቅት የኤርትራ መንግሥትን የሚደግፉ በእስራኤል ያሉ ስደተኞች ጥገኝነት የሚጠይቁበት ምንም ምክንያት እንደሌላቸው ተደርጎ እንደሚቆጠርም ገልጿል።

ያለ ምንም ተቃውሞ ያለፈው ይህ ረቂቅ ሕግ ለኤርትራ መንግሥት ድጋፋቸውን የሚገልጹ ኤርትራውያን ስደተኞችን ከእስራኤል የማባረር ሥልጣንን ለአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ለመስጠት ያለመ ነው።

ኤርትራውያንን ከእስራኤል ባሻገር በሁለት ጎራ ተከፍለው በተለያዩ የአውሮፓ እና የሰሜን አሜሪካ ከተሞች ተጋጭተዋል።

በ2015 ዓ.ም. ማብቂያ ላይ ከኤርትራ የባሕል ፌስቲቫል ዝግጅት ጋር በተያያዘ በእስራኤል፣ በጀርመን፣ በስዊዲን፣ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በስዊትዘርላንድ እና በካናዳ በኤርትራ ውያን መካከል ግጭቶች ተካሂደዋል።

በእነዚህ ጊዜያት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በኤርትራውያን ማኅብረሰብ አባላት የተዘጋጁ ፌስቲቫሎች በተደራጁ ቡድኖች ሲታወኩ ታይተዋል።

በተለያዩ የውጭ አገራት ሁከት እና ብጥብጥ አስነስቷል የተባለው የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚ የሆነው ብርጌድ ንሃመዱ የተባለው ቡድን በጀርመን ሕግ መሠረት "በአገር ውስጥ አሸባሪነት" መፈረጁን የአገሪቱ ዐቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤት ያስታወቀው ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ነበር።

የባሕል ፌስቲቫሉን የሚቃወሙ ኤርትራውያን ሥነ ሥርዓቱ "ለአምባገነኑ የኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት" ገንዘብ ማሰባሰቢያ ነው በሚል ነው።