የእስራኤል ፓርላማ የኤርትራ መንግሥትን የሚደግፉ ስደተኞችን ከሀገር የሚያባርር ረቂቅ ሕግን አሳለፈ

የፎቶው ባለመብት, AP
የእስራኤል ፓርላማ መንግሥታቸውን የሚደግፉ የኤርትራ ስደተኞችን ከአገር ለማባረር ያለመውን ረቂቅ ሕግ የመጀመሪያውን ዙር በሙሉ ድጋፍ አሳለፈ።
ክኔሴት ተብሎ የሚጠራው የእስራኤል ፓርላማ ኤርትራውያን ስደተኞችን ከአገር ለማባረር ያለመውን ረቂቅ ሕግ የመጀመሪያ ዙር 51 ለ 0 በሆነ ድምጽ ማሳለፉን የእስራኤሉ ጋዜጣ ዘ ታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘግቧል።
ያለ ምንም ተቃውሞ ያለፈው ይህ ረቂቅ ሕግ ለኤርትራ መንግሥት ድጋፋቸውን የሚገልጹ ኤርትራውያን ስደተኞችን ከእስራኤል የማባረር ሥልጣንን ለሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ለመስጠት ያለመ እንደሆነ ዘገባው አስነብቧል።
የኤርትራ መንግሥትን የሚደግፉ በእስራኤል ያሉ ስደተኞች ጥገኝነት የሚጠይቁበት ምንም ምክንያት እንደሌላቸው ተደርጎ እንደሚቆጠርም ተገልጿል።
የተለያዩ የእስራኤል የመንግሥት ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም የተለያዩ ተከታታይ እርምጃዎችን የወሰዱ ሲሆን፣ አንዳንዶቹም በፍርድ ቤት ታግደዋል።
በእስራኤል ውስጥ ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች ይኖራሉ። ስደተኞቹ በሀገራቸው ያለውን ጭቆና እንዲሁም ጦርነት ሸሽተው በእስራኤል ጥገኝነት የሚጠይቁ ናቸው።
ከባለፉት ጥቂት ዓመታት ጀምሮ እስራኤልን ጨምሮ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኤርትራውያን ስደተኞች በአገዛዙ ደጋፊዎች እና በተቃዋሚዎች ጎራ ተከፋፍለው ተደጋጋሚ ግጭቶች ውስጥ ገብተዋል። ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር በሁለት ኤርትራውያን ቡድኖች መካከል በቴል አቪቭ በተፈጠረ የጎዳና ላይ ግጭት ሁለት ሰዎች ተገድለዋል።
በእስራኤል ከሁለት ዓመታት ገደማ በፊት በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች መካከል በተነሳ ግርግር እንዲሁም ከፖሊስ ጋርም በተፈጠረው ግጭት ከ170 በላይ ሰዎች ቆስለዋል።
በርካቶች ተጎድተውበታል እንዲሁም ከፍተኛ የንብረት መውደም ተከስቶበታል በተባለውም በዚህ ግርግር ተሳትፈዋል የተባሉ ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎችን በአስቸኳይ ከሀገር ማባረርን ጨምሮ ጠንከር ያለ እርምጃም ይወሰድባቸዋል ተብሎ ነበር።
በዚህ ሳምንት ደቡብ ቴል አቪቭን ጎብኝተው "ያለውን ትርምስ ማየታቸውን" የተናገሩት እና ረቂቅ ሕጉን ካዘጋጁት መካከል አንዷ የሆኑት የዩክሬን ተወጇ እስራኤላዊቷ ፖለቲከኛ ዩሊያ ማሊኖቭስኪ ኩኒን "ዋነኞቹ ወንጀለኞች የኤርትራ መንግሥት ደጋፊ የሆኑ ሰርጎ ገቦች ናቸው" ብለዋል።
ረቂቅ ሕጉን "የደቡብ ቴል አቪቭ ነዋሪዎችን ደኅንነት እና ሰላም ወደ ቀድሞው ለመመለስ የመጀመሪያው እርምጃ" ሲሉ ጠርተውታል።
የኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች "እዚህ [እስራኤል] በጥገኝነት ጥየቃ ላይ ናቸው። ነገር ግን በተመሳሳይ ወቅት አገዛዙን ይደግፋሉ፤ ይህ ማለት በአገራቸው ውስጥ ስጋት የለባቸውም። ስለዚህ ወደ ትውልድ አገራቸው ሊመለሱ ይችላሉ" ብለዋል ፖለቲከኛዋ።
ከኤርትራ የነጻነት ትጥቅ ትግል ጀምሮ በውጭ አገራት ጠንካራ የማኅበረሰቦች አደረጃጀትን መፍጠር የቻለው የኤርትራ መንግሥት፣ በሰኔ መጨረሻ የሚከበረውን የሰማዕታት እና የግንቦት የነጻነት በዓሎችን በኤምባሲው እና በደጋፊዎቹ አማካኝነት ሲያከብር ቆይቷል።
ነገር ግን ባለፉት ጥቂት ዓመታት አገዛዙን የሚቃወሙ እና የኤርትራ መንግሥት እነዚህ ክብረ በዓላትን ለፕሮፓጋንዳ እና ገንዘብ ለማሰባሰብ ይጠቀምበታል የሚሉ 'ብርጌድ ን ሀመዱ' የሚባል ቡድን ድንኳኖችን ማቃጠል ጨምሮ ሌሎች መንገዶችን በመጠቀም እየተቃወሙ ይገኛሉ።
በደጋፊዎች እና በተቃዋሚዎች መካከል በተከሰቱ ሁከቶች የተነሳ በተለያዩ አገራት የፓሊስ አባላትን ጨምሮ በኤርትራውያን እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኤርትራ የባሕል ፌስቲቫል ዝግጅትን ምክንያት በማድረግ በኤርትራውያን መካከል በአውሮፓ እና በአሜሪካ ከተሞች ግጭት ሲፈጠር መመልከት የተለመደ ሆኗል።
በባለፉት ዓመታት እስራኤልን ጨምሮ በጀርመን፣ በስዊድን፣ በኖርዌይ እና በካናዳ ብዙዎችን ለጉዳት የዳረገ ግጭት ተከስተዋል።
በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የኤርትራ መንግሥት በዜጎቹ ላይ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጽማል ይላሉ።
በዚህም ምክንያት በኤርትራ ያለውን የፖለቲካ እና የእምነት ነጻነት ጭቆና እንዲሁም የጊዜ ገደብ የሌለውን አስገዳጅ የብሔራዊ አገልግሎት በመሸሽ በርካታ ኤርትራውያን አገር ጥለው ይሰደዳሉ።












