የእስራኤል ወታደርን ሕይወት የታደገው ኤርትራዊ ጥገኝነት ጠያቂ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ተሰጠው

የፎቶው ባለመብት, INTERIOR MINISTRY
በሐማስ ጥቃት ወቅት ጉዳት የደረሰበትን የአንድ እስራኤላዊ ኮሎኔል ሕይወትን ያተረፈው ኤርትራዊ ለፈጸመው ተግባር በእስራኤል መንግሥት ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ተሰጠው።
ሐማስ ስዴሮት በተባለችው የእስራኤል ከተማ ላይ ጥቃት በፈጸመበት ጊዜ ስሙ ያልተጠቀሰው የእስራኤል መከላከያ ኃይል አባል ቆስሎ ክፉኛ ተጎድቶ በነበረበት ወቅት ነው ሙሉጌታ ፀጋይ የተባለው ኤርትራዊ ጥገኝነት ጠያቂ የወታደሩን ሕይወት የታደገው።
ኤርትራዊው የእራሱን ሕይወት አደጋ ላይ በመጣል የኮሎኔሉን ሕይወት ለማትረፍ ለፈጸመው ተግባር ከእስራኤል የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሼ አርቤል እጅ በአገሪቱ ውስጥ በቋሚነት ለመኖር የሚያስችለውን ፈቃድ መቀበሉን የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ቢቢሲ ትግርኛ ሙሉጌታ ፀጋይን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ባይሳካለትም ጉዳዩን የሚያውቁትን እና በእስራኤል የኤርትራውያን ማኅበረሰብ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ብርሃነ ነጋሲ ስለሁኔታው አስረድተዋል።
መስከረም 26/2016 ዓ.ም. የሐማስ ታጣቂዎች ወደ እስራኤል ግዛት ዘልቀው በመግባት ጥቃት ሲፈጽሙ በስዴሮት ከተማ ውስጥ ሆዱ ላይ በጥይት ተመትቶ ከባድ ጉዳት የደረሰበት ኮሎኔል በኤርትራዊው ድጋፍ ሕይወቱ ሊተርፍ ችሏል ብለዋል።
ሙሉጌታ ጥቃቱን ለመሸሽ ሲጓዝ ነበር ኮሎኔሉን ከወደቀበት የተመለከተው፤ ክፉኛ ደሙ ሲፈስ የነበረውን ቁስለኛ ደሙን ለማስቆም በመጣር ሌሎች ደርሰው እርዳታ እስኪያገኝ ድረስ ለሰዓታት እየረዳው አብሮት እንደቆየ ተነግሯል።
ከሰዓታት በኋላም ሌሎች ደርሰው ኮሎኔሉ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ለሳምንታት ሕክምና አግኝቶ ከሆስፒታል ሲወጣ ሕይወቱን ያተረፈለትን ሙሉጌታ ፀጋይን ማመስገን እደሚፈልግ እና የአገሪቱ መንግሥትም ለጥገኝነት ጥያቄው ምላሽ እንዲሰጥ ጥያቄ ማቅረቡ ተነግሯል።
በሙሉጌታ ተግባር የተደነቁት የእስራኤል የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሼ አርቤል “የእስራኤል ሠራዊት አባልን ሕይወት ለማዳን የራሱን ሕይወት ለአደጋ ላጋለጠ ሰው እስራኤል ውስጥ በክብር እንዲኖር ዕድል መስጠት ማድረግ ከምንችለው ትንሹ ነው” ማለታቸውን የእስራኤል መገናና ብዙኃን ዘግበዋል።
ስደተኞች በዘላቂነት ለመኖር የሚያስችል ፈቃድ ለማግኘት አስቸጋሪ ከሆኑባቸው አገራት መካከል አንዷ በሆነችው አስራኤል ውስጥ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ለዓመታት እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
ለፈጸመው በጎ ተግባር አሁን ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ በእስራኤል መንግሥት የተሰጠው ሙሉጌታ ፀጋይም ከእነዚህ መካከል አንዱ ነበር።
በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ ሐማስ በእስራኤል ላይ በተፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት 1400 ሰዎች መግደሉን እና ከ220 በላይ ሰዎችን ደግሞ አግቶ ወደ ጋዛ ሰርጥ መውሰዱን የእስራኤል መንግሥት ገልጿል።
ይህንንም ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ላይ ለሳምንታት ባካሄደችው ወታደራዊ ዘመቻ አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕጻናት የሆኑባቸው ከ14 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ እና ታጋቾችን እንዲሁም እስረኞችን ለመልቀቅ እስራኤል እና ሐማስ በደረሱት ስምምነት መሠረት ባለፉት ሦስት ቀናት ጦርነቱ ጋብ ብሏል።
ነገር ግን እስራኤል እንደዛተችው ከታጋቾች መለቀቅ በኋላ ከጋዛ ሐማስን ለማጥፋት የጀመረችውን ወታደራዊ ዘመቻ አጠናቀክራ እንደምትቀጥል ደጋግማ እየገለጸች ነው።












