የሐማስ ጥቃት እና በሕዝቡ ዘንድ የፈጠረው ድንጋጤ በቤተ እስራኤላዊው ዐይን

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የፍልስጥኤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ ቅዳሜ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ የፈጸመው ጥቃት በመጠኑ እና ባደረሰው ጉዳት ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነው ተብሎለታል።
ድንገተኛው ጥቃቱ ለአስርታት በፍልስጥኤማውያን እና በእስራኤል መካከል የዘለቀው ውጥረት ማሳያ ተደርጓል።
በመካከለኛው ምሥራቅ ከፍ ሲልም በዓለም ላይ ቀውስን ያስከተለው የቅዳሜው ጥቃት ሲጀምር በርካታ እስራኤላውያን መኝታቸው ላይ ነበሩ።
ቅዳሜ የአይሁዶች ሰንበት እና የበዓል ዕለት ስለነበረ ቤተሰቦች በቤት ውስጥ አሊያም በጋራ ፀሎት በሚያካሂዱበት ቦታ ተሰባስበው ዕለቱን ያሳልፋሉ። ጓደኛሞችም ተገናኝተው ይዝናናሉ።
ማለዳው ግን በድንገተኛ የሮኬቶች ተኩስ ነበር የጀመረው። መጠነ ሰፊው እና የተቀናጀው ጥቃት ይፈጠራል ብሎ ያሰበ አልነበረም።
አይቸው ባዬ በእስራኤሏ አሽኬሎን ከተማ ውስጥ ነዋሪ ናቸው። እስራኤል መኖር ከጀመሩ ከ30 ዓመት በላይ ሆኗቸዋል።
የእስራኤል ተጠባባቂ ጦር ወታደር ናቸው። የሻምበልነት ደረጃ ላይም ደርሰዋል። በአደጋ ጊዜም ለማኅበረሰቡ የአደጋ ማስጠንቀቂያ ትምህርት ይሰጣሉ።
አሽኬሎን ለጋዛ ሰርጥ በቅርብ ርቀት ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ለመኖር የሚመርጧት ከተማ ናት።
ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ ብዙ ጊዜ ሮኬቶችን ይተኩሳሉ። ሮኬቶቹ አንዳንዴ ጉዳት ያደርሳሉ። ሌላ ጊዜ ደግሞ የእስራኤል ፀረ ሮኬት ሰማይ ላይ እያፈነዳ ያከሽፋቸዋል።
ቅዳሜ ዕለት ሐማስ የፈጸመውን ጥቃት “ተኩሶ መግደል ነው። አይሲስ የሚያደርገው ዓይነት ግድያ እና ጭፍጨፋ ነው” ሲሉ ሁኔታውን ይገልጹታል።
መጀመሪያ ሮኬቶችን ተኩሰዋል። ይህን ያደረጉት በዝግጅታቸው መሠረት በእግር ለመጣው ‘ኮማንዷቸው’ ከለላ ለመስጠት መሆኑን አይቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“እስከ ዛሬ ድረስ ከ1200 በላይ ንጹሃን ዜጎች እና ወታደሮች ገድለዋል። እንደ ምርኮኛ ይዘው የወሰዷቸውም አሉ” ብለዋል።
ከሰሞኑ እስራኤላውያን በዓል በማክበር ላይ ነበሩ። ቤተሰብ አብሮ የሚያሳልፈበት ጊዜም ነበር።
በጋዛ ሰርጥ አቅራቢያ በሚገኘው የእስራኤል ክልልም ወጣቶች የሙዚቃ ድግስ በመካፈል ላይ ነበሩ። ይህንንም አጋጣሚ የሐማስ ታጣቂዎች ተጠቅመውበት በርካቶችን ኢላማ ማድረጋቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ።
አቶ አይቸው ዘመድ ለመጠየቅ ወደ ሌላ ከተማ አቅንተው ነበር። ወደ መኖሪያ ከተማቸው የተመለሱት ንጋት 6፡20 ገደማ ነበር። ጠዋትም ስለነበር ‘አየር ልቀበል ብለው ወደ ባህር ዳርቻ’ ያቀናሉ።
የሰሙትን ፍንዳታ ድምጽ የእስራኤል ጦር ልምምድ እያደረገ ይሆናል በሚል ነበር ያለፉት።
12፡30 ሲሆን ግን የአደጋ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ደውል አካባቢውን ናጠው ይላሉ።
“መኪናዬን አስነስቼ በምወጣትበት ሰዓት የተተኮሰው ሮኬት ፊት ለፊት ያለውን ህንጻ መታው፤ ነደደ” ሲሉ የቅዳሜ ጠዋቱን ክስተት ያስታውሳሉ።
የሐማስ ታጣቂዎች ድንበሩን ሰብረው እስራኤል ክልል ውስጥ ጥቃት ማድረስ ጀምረዋል።
“ዓመት በዓል በሚሆንበት ጊዜ እንደ ሐማስ ያሉ ቡድኖች ብጥብጥ ይፈልጋሉ” ይላሉ አይቸው።
“ይኼኛውን ጥቃት ግን ማንም ያልጠበቀው ነው። በሚያስደነግጥ ሁኔታ ነው የተፈጠረው። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ማንም አልጠበቃቸውም” ብለዋል።
ቀደም ሲል ጀምሮ ችግር እንዳይፈጥሩ ንግግር ሲደረግ እንደነበርም ያስታውሳሉ። እስራኤል ላይ ጥቃት እንዳይሰነዘር ነው ንግግሩ። ይህ ከሆነ ደግሞ በርካታ የጋዛ ነዋሪዎች በእስራኤል የመሥራት ፈቃድ ያገኛሉ።
ሐማስ ግን ቀደም ብሎ ጀምሮ ወደ ድንበር ተጠግቶ ልምምድ ሲያደርግ ነበር የሚሉት አይቸው “ይህንንም የእስራኤል የስለላ ተቋማት አልደረሱበትም ነበር” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
“ሕዝቡ ደንግጧል”
ጥቃቱ ያልተጠበቀ በመሆኑ “ሕዝቡ ደንግጧል። ለማጥቃት ይገባሉ ብሎ የጠበቀ ሰው አልነበርም” በማለት ሁኔታው ሕዝቡ ድንጋጤ ውስጥ መሆኑን ተናግረዋል።
“ሐማስ እንዴት ድንበር ጥሶ ገብቶ እኛን ይጨፈጭፋል? እንዴትስ አሰበው? እንዴትስ አቀደው?” እያሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እስራኤል በአሁኑ ወቅት በፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ መሆኗን የሚጠቅሱት አይቸው፣ ግራ ዘመም እና ቀኝ ዘመም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተፋጠቱበት ጊዜ ነው።
ይህ ደግሞ ሕብረተሰቡንም ከፋፍሏል።
በሐማስ የተፈጸመው ጥቃት “ሕዝቡን አንድ አድርጎታልት” የሚሉት አይተነው “የበለጠ እንድንትሳሰር እና አንድነታችን እንድናጠናክር ያደረገ ነው” በማለት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት ቁጣን መቀስቀሱን ገልጸዋል።
“በንጹሃን ላይ በተፈጸመው ግድያ ምክንያት. . . እስራኤል የምትወስድባቸው እርምጃ ይበጃቸዋል ወይ? እነሱ [ሐማስ] ለማኅበረሰባቸው አላሰቡላቸውም። ጋዛ ውስጥ ላሉ ፍልስጤሞች እኮ በጣም ነው የምናዝንላቸው። በቅኝ ግዛት፤ በጉልበት የተያዙ ናቸው” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
“እጅግ ዘግናኝ ሁኔታ ነው የነበረው”
ሽመዬል የሚባል አብሯቸው አዳሪ ትምህርት ቤት የተማረ ጓደኛቸው በጥቃቱ ተገድሏል።
ጓደኛቸው የፖሊስ አባል ነበር። በነበረበት ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ እሱን ጨምሮ 13 ፖሊሶች በሐማስ ጥቃት መገደላቸውን ተናግረዋል።
እንደእሳቸው ከሆነ ከኢትዮጵያውያን አይሁዶችም እስካሁን ወደ ሰባት የሚሆኑ ተገድለዋል።
አስከሬን መለየት አስቸጋሪ በመሆኑ እንጂ ቁጥሩ ሊጨምር ይችላል የሚልም ስጋትም አላቸው።
በአጠቃላይ “እጅግ ዘግናኝ ሁኔታ ነው የነበረው” ብለዋል።
ሐማስ ከመቶ በላይ ሰዎችንም አግቶ የወሰደ ሲሆን፣ ታግተው ከተወሰዱት ውስጥም ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገምታሉ።
“እነማን ናቸው? ምንድን ናቸው? የሚለው ነገር ገና እየተጣራ ነው ያለው። ጭፍጨፋ ባካሄዱበት ቦታ አስከሬን አንስቶ ለመለየት እንኳን ብዙ ጊዜ ይጠይቃል” ሲሉ ተናግረዋል።
አብዛኞቹ ታግተው የተወሰዱት በሙዚቃ ድግስ ላይ የተካፈሉ ወጣቶች ናቸው። ታጣቂዎቹ በየቤቱም ገብተው የወሰዷቸው አሉ ግን እነማን እንደሆኑ ሙሉ ለሙሉ አልተለየም።
በጣም ያስደነገጣቸውን ታሪክ ተጠይቀውም “አንድ ቤተሰብ በሙሉ እናት፣ ባል ሁለት ልጆች ተጨፍጭፈዋል። ሟቾቹን ለመለየት የዘረመል ምርመራ እንኳን እንዳይደረግ ቤተሰብ በሙሉ ጠፍቷል። አስከሬን የእኔ ነው ብሎ መውሰድም አልተቻለም። የተቃጠሉም በመኖራቸው መለየት ከባድ ነው። ቤተሰብ እንኳን ተቀብሎ አልቅሶ የሚቀብርበት አጋጣሚ የለም። ሁሉም አልቀዋላ” ብለዋል።
“ሐማስን ከምድረ ገጽ ማጥፋት ነው”
አይቸው እንደሚሉት ቅዳሜ ዕለት በሐማስ የተፈጸመው መጠነ ሰፊ ጥቃት በእስራኤል ማኅበረሰብ ውስጥ ፍርሃት እና ድንጋጤን ፈጥሯል።
“ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ ሁሉም የሚለው ሐማስ ከምድረ ገጽ መጥፋት አለበት። እስራኤል እየወሰደች ያለቸው እርምጃ እዚያ ያሉ ንጹሃን ዜጎችን በማይጎዳ መንገድ ሐማስን ከምድረ ገጽ ማጥፋት አለበት። ያ ከሆነ ሐማስ እንደገና ተመልሶ ጠላት ሊሆን አይችልም” ሲሉ አይቸው ያለውን ድባብ ገልጸዋል።
ጥቃት ይፈጸማል። መልሶ ስምምነት ይደረሳል። ይህ ዑደት ለዓመታት መኖሩን ያስታውሳሉ።
“አሁን ግን ያ ሃሳብ የለም። በሕዝቡ ውስጥ በፍጹም ሐማስ መጥፋት አለበት የሚል አቋም ነው በስፋት የሚንጸባረቀው” ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ በሚኖሩባት አሽኬሎን የከተማ መደበኛው የነዋሪዎች እንቅስቃሴ ተገድቧል። ከቅዳሜ በኋላም ባሉት ቀናት ከተማዋን የሐማስ ሮኬቶች እየመቱ እንደሆነ ዘገባዎች ያመለክታሉ።
የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ የእስራኤል አካባቢዎች እንደ ስጋት ደረጃቸው በአረንጓዴ፣ በቢጫ እና በቀይ ተከፋፍለዋል።
ጋዛ ሰርጥ አካባቢ ያሉት ቀይ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ለአደጋ ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ነው እንደማለት ነው።

የፎቶው ባለመብት, EPA
በእነዚህ አካባቢዎች “እንደልብ መውጣት እና መዝናናት አይቻልም። ከተወሰነ ቦታ ውጪ ተጉዞ ግብይት ለማድረግም አይቻልም።”
በየጊዜውም የአደጋ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ደውል ይደወላል።
የማስጠንቀቂያ ደውሉ ሲደወል ወደ አደጋ መከላከያ መጠለያ ቦታዎች ለመሸሸግ የሚወስደው ሰዓት አለ። ይህ ሰዓት ከቦታ ቦታ እንደ ስጋት መጠኑ ይለያያል።
የከተማቸው ነዋሪዎች ደውል ከተሰማ በኋላ ወደ አደጋ መከላከያ መጠለያ ቦታዎች ለመድረስ 15 ሰከንድ ብቻ ነው እንዳላቸው ተነግሯቸዋል። በ15 ሰከንድ ካልደረሱ ጉዳት ሊያጋጥማቸው ይችላል።
የቴል አቪቭ ነዋሪዎች የአንድ ደቂቃ ተኩል ጊዜ አላቸው።
ሰው ሥራ ገብቶ የአደጋ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ደውል ቢደወል፤ ለመሸሽ የሚፈጅበትን ጊዜ ማወቅ ይኖርበታል።
ሰዓቱ ከተቀመጠው በላይ ከሆነ ሥራ መግባት አይፈቀድም።
“ትምህርት በመላ እስራኤል እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ድረስ አይኖርም። እንቅስቃሴዎች ሁሉ በጥብቅ የተገደቡ ናቸው” ብለዋል።
እስካሁን በተደጋጋሚ ወደ አደጋ መከላከያ መጠለያ ቦታ መሄዳቸውን እና ካለው ስጋት የተነሳ የተረጋጋ ሕይወታቸው መረበሹን ይናገራሉ።
“ወደ አደጋ መሸሸጊያው ቦታ በተደጋጋሚ በመግባታችን መቁጠር አይቻልም። እስካሁን እንቅልፍስ መቼ ተኛንና? መቼ ፋታ ይሰጣል። ደውል በተሰማ ቁጥር ሌሊቱን በሙሉ ስንሮጥ ነው የምታድረው” ብለዋል።
አዛውንቶች እና አቅም የሌላቸውን ይዞ በተደጋጋሚ እና በፍጥነት መግባት አዳጋች መሆኑን ይገልጻሉ።
ተጠባባቂ ወታደር እንደመሆናቸው እሳቸውም ወደ ግዳጅ ቀጠና ሊዘምቱ ይችላሉ።
እንደከተማው ቢለያይም እስከ ትላንት [ረቡዕ] ድረስ የሐማስ የሮኬት ጥቃት ቀጥሏል።
“እኔ እና ወላጆቼ በሚንኖርበት ከተማ በየሰከንዱ ነው የሚተኮሰው። አሁን ግን እየቀነሰ ነው። የተወሰነ ሰዓት ላይ በኃይለኛው ይተኩሳሉ። እንደገና ጋብ ይላል” ብለዋል።












