ኢንስታግራም የህፃናት የግል መረጃዎችን መብት በመጣስ 405 ሚሊዮን ዩሮ ተቀጣ

የኢንስታግራም አርማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአየርላንድ ተቆጣጣሪዎች የህፃናት የግል መረጃዎችን በመተላለፍ በኢንስታግራም ላይ 405 ሚሊዮን ዩሮ የቅጣት ውሳኔ አስተላለፉ።

ለረጅም ጊዜ የቀረበው ይህ ቅሬታ የህፃናቱን የስልክ ቁጥርና የኢሜይል አድራሻቸውን መረጃዎች አስተላልፎ መስጠትን ይመለከታል።

አንዳንድ ህፃናት ባለማወቅ የኢንስታግራም አካውንታቸውን ከግል ወደ ቢዝነስ ያሻሻሉ ሲሆን በዚህም መረጃዎቻቸው በበለጠ ተጋላጭ ሆኗል ብሏል።

የኢንስታግራም ባለቤት ሜታ፣ ውሳኔውን ይግባኝ እንደሚል አሳውቋል። ተቆጣጣሪው ኩባንያው ላይ ቅጣት ሲያስተላልፍ ለሦስተኛ ጊዜ ነው።

“የመጨረሻ ውሳኔያችንን ባለፈው አርብ አስተላልፈናል።በዚህም 405 ሚሊዮን ዩሮ እንዲቀጣ ወስነናል” በማለት የአየርላንድ የመረጃ ጥበቃ ኮሚሽነር ዲፒሲ አስታውቋል።

የሜታ ባለስልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት “የቀረበብን ቅሬታ ከአንድ አመት በፊት በነበረው የመተግበሪያዎቻችን ‘ሴቲንግ’ ላይ ያተኮረ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ታዳጊዎች ደኅንነታቸው የተጠበቀ እና የግል መረጃዎቻቸው ሚስጥራዊ እንዲሆኑ የሚያግዙ በርካታ አዳዲስ መገልገያዎችን አስተዋውቀናል” ብለዋል።

“ከ18 ዓመት በታች የሆነ ማንኛውም ሰው ኢንስታግራምን በሚቀላቀልበት ወቅት መረጃዎቻቸው ግላዊ/ ሚስጥራዊ ይሆናሉ። በዚህም የሚያውቋቸው ሰዎች ብቻ የሚለጥፉትን ማየት እንዲችሉና የማይከተሏቸው አዋቂዎችም ለታዳጊዎቹ መልዕክት መላክ እንዳይችሉ አድርገናል” ሲሉም አክለዋል።

የአየርላንድ መረጃ ጥበቃ ምርመራውን በሚያካሂድበት ወቅት ሙሉ በሙሉ እንደተባበረ ያስታወቀው ሜታ “ቅጣቱ እንዴት እንደተጣለ አልገባንም” እንዲሁም “ይግባኝ እንላለን” ብሏል።

"የቀረውን ውሳኔ በጥንቃቄ መገምገም እንቀጥላለን።" ብለዋል የሜታ ባለስልጣን።

የአየርላንዱ ዲፒሲ በመላው አውሮፓ የሚሰራ ሲሆን ትልልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችም ላይ ቁጥጥር ያደርጋል።

የአውሮፓ ኅብረት የመረጃ ጥበቃ ደንብን በመጣስ ከዚህ በፊት ቅጣቶች ቢጥልም በኢንስታግራም ላይ የተጣለው የቅጣት ውሳኔ በጣም ከፍተኛው ነው ተብሏል።

ባለፈው ዓመት በዋትስአፕ ላይ የ225 ሚሊዮን ዩሮ ቅጣት ያስተላለፈ ሲሆን የሉክሰምበርግ የመረጃ ባለስልጣን በበኩሉ ክብረወሰን የተባለውን የ746 ሚሊዮን ዩሮ ቅጣት በአማዞን ላይ አስተላልፏል።

“በኢንስታግራም የተፈጸመው የመረጃ መተላለፍ ከፍተኛ አንድምታ ያለውና ኢንስታግራም በሚጠቀሙ ህፃናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ጥሰት ነበር” በማለት ህፃናትን ከኢንተርኔት ጉዳቶች ለመከላከል የተቋቋመው ኤንኤስፒሲሲ ተቋም የፖሊስ ኃላፊ አንዲ ቡሮውስ ተናግረዋል።