ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በተጠናቀቀው 2022 ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ያጋጠሙ ስምንት ክስተቶች
የተጠናቀቀው 2022 (እአአ) በርካታ ያልተጠበቁ ሁነቶችን አስተናግዷል። ነገር ግን ሁሉም የተከሰቱት በምድራችን ላይ ብቻ አይደለም። በጠፈር ላይም ዓለምን አጀብ ያሰኙ ክስተቶች ተሰምተዋል።
ትኩረታችንን ከሳቡት ሁነቶች መካከል የተወሰኑትን እናጋራችሁ።
ናሳ የአስትሮይዶችን አቅጣጫ አስለወጠ
የአሜሪካ የህዋ ምርምር ኤጀንሲ (ናሳ) መስከረም 28 ላይ ሆነ ብሎ ከመንኮራኩር ጋር እንዲጋጭ በማድረግ የአንድ አስትሮይድን አቅጣጫ አስቀይሯል።
ግጭቱ እንዲፈጠር የተደረገው ጠፈር ላይ ያሉ ለመሬት ስጋት የሆኑ ግዙፍ አለቶችን መምታት እንደሚቻል እና ከመስመራቸው ወጥተው ጉዳት ሳያደርሱ መሬት ላይ ያርፋሉ ወይ የሚለውን ለማረጋገጥ ነበር። ይህም ዕውን ሆኗል።
አስትሮይዶች በፀሐይ ዙርያ የሚሽከረከሩ አለታማ አካላት ናቸው። የተለያየ መጠን ያላቸው አስትሮይዶች አሉ።
ይህ ናሳ አቅጣጫውን ያስቀየረው አስትሮይድ 160 ሜትር ስፋት አለው ተብሏል።
በሰው ደም ውስጥ የፕላስቲክ ቁርጥራጮች ተገኙ
ባለፈው ሚያዚያ ኢንቫይሮንመንት ኢንተርናሽናል በተባለ ጆርናል ላይ የታተመ ጥናት፣ ከተመረመሩ ሰዎች ውስጥ 80 በመቶ በሚሆኑት የደም ናሙና ላይ ማይክሮፕላስቲክ (የፕላስቲክ ቁርጥራጮች) መገኘታቸውን አመልክቷል።
ማይክሮፕላስቲክ (የፕላስቲክ ቁርጥራጮች) ሲሆኑ በርዝመት ከ5 ሚሊሜትር ያንሳሉ።
ይህ የተከሰተው በአፈር፣ በባሕር እንዲሁም በተበከለ አካባቢ ውስጥ ያሉ የፕላስቲክ ቁርጥራጮች በመበላታቸው ነው። ይሁን እንጂ የፕላስቲክ ቁርጥራጮቹ በሰውነት ውስጥ መገኘታቸው የሚያሳድረው ጉዳት እስካሁን አልታወቀም።
ተመራማሪዎች እንደሚሉት አዲሱ ግኝት ማይክሮፕላስቲክ የሰው ልጅ ሕዋሶችን ሊጎዳ እንደሚችል ጠቁሟል።
በኳታር የተካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ
የ2022 የኳታር የወንዶች የዓለም ዋንጫ የተጠናቀቀው በተከታታይ ያልተጠበቁ ውጤቶችን በማስተናገድ ነበር። ጨዋታው በአረብ ወይም በሙስሊም አገር ሲዘጋጅም ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
በኳታር አስተናጋጅነት የተካሄደው 22ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የተለዩ ገጽታዎችም ነበሩት።
የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ዳኞች እንዲያጫውቱ የተመረጡበትም ነበር።
ከተመረጡት ዳኞች መካከል የ38 ዓመቷ ፈረንሳዊት ስቴፋኒ ፍራፓርት፣ ጀርመን እና ከኮስታሪካ የሚያደርጉትን ጨዋታ በመሐል ዳኝነት መርታለች።
ይህም ፍራፓርትን በፊፋ ዓለም ዋንጫ ታሪክ በዋና ዳኝነት ጨዋታ የመራች የመጀመሪያዋ ሴት አድርጓታል።
ሌላኛው ደግሞ የአፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰችበት አስደናቂ ጨዋታ ነበር። ይህም የአፍሪካዊቷ አገር ምርጡ ውጤት ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል።
ኳታር 2022 ሊዮኔል ሜሲ ከአምስት ሙከራዎች በኋላ የዓለም ዋንጫን ሲያነሳ የታየበት መድረክ ነበር።
የዓለም ሕዝብ ቁጥር ስምንት ቢሊየን ደረሰ
እንደ የተባበሩት መንግሥታት ከሆነ የዓለም ሕዝብ ብዛት ለመጀመሪያ ጊዜ ከስምንት ቢሊየን ያለፈው ባለፈው ኅዳር ነበር።
ድርጅቱ በመግለጫው እንዳለው ይህ ያልተጠበቀ የሕዝብ እድገት የመጣው የሰው ልጅ በሕይወት የመቆያ ጊዜው በሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ፣ በሥነ ምግብ፣ በግል ንጽህና እንዲሁም በመድኃኒት መሻሻል በማሳየቱ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም በተወሰኑ አገራት የታየው ከፍተኛ የሆነ እና ቀጣይነት ያለው የውልደት መጠን አስተዋጽኦ አለው።
ሆኖም የዓለም ሕዝብ ከነበረበት ሰባት ቢሊየን ወደ ስምንት ቢሊየን ለማደግ 12 ዓመታትን እንደወሰደበት ድርጅቱ አስታውቋል።
ነገር ግን በአጠቃላይ በዓለም ላይ የውልደት መጠን እየቀነሰ በመሆኑ በቀጣይ የዓለም ሕዝብ በአንድ ቢሊየን ለመጨመር በትንሹ 15 ዓመታት ይወስድበታል።
ዓለምን ይቀይራል የተባለው የወባ ክትባት ተገኘ
የኦክስፎርድ ተመራማሪዎች መስከረም ላይ ዓለምን ይቀይራል የተባለለትን የወባ ክትባት ማበልጸጋቸውን አስታውቀዋል። ክትባቱ በሚቀጥለው ዓመት ይሰራጫል ተብሎም ይጠበቃል።
አዲሱ ክትባት በዓመት የ400 ሺህ ሰዎችን ሕይወት የሚቀጥፈውንና ገዳይ የሆነውን በሽታ ለመከላከል 80 በመቶ ውጤታማ ነው ተብሏል። ተመራማሪዎቹ እንዳሉት ክትባቱ ርካሽ ነው።
ክትባቱ ውጤታማ መሆኑ የተረጋገጠው ከስድስት ዓመታት በፊት ሲሆን፣ እስከ 40 በመቶ የሚደርሰውን የበሽታውን ቁጥር የሚቀንስ፣ 30 በመቶ ደግሞ አስጊ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ይታደጋል ተብሏል።
የወባ በሽታ በዓለም ላይ ሕጻናትን ከሚገድሉ ዋና ሽታዎች አንደኛው ሲሆን በሽታውን የሚያመጣው ጥገኛ ተህዋስ ውስብስብ በመሆኑ የወባ ክትባትን ማበልጸግ እጅግ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል።
ግዙፉ ጀምስ ዌብ ቴሌስኮፕ
የጀምስ ዌብ ቴሌስኮፕ ሐምሌ ወር ላይ ሥራ ከጀመረ አንስቶ የዜና አርዕስት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው።
ቴሌስኮፑ የጠፈርን አስደናቂ ምስል አጋርቷል። ምስሉ 13 ቢሊየን ዓመታትን ካስቆጠረው JADES-GS-z13-0 ምስልን ጨምሮ እስካሁን ከተነሱት የዓለማችን ጥልቅ ምስሎች አንዱ ነው።
10 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት የዓለማችን ግዙፏ ቴሌስኮፕ፣ እስከ ዛሬ ከተሠሩ ቴሌስኮፖች ሁሉ ለየት ተደርጎ ነው የተሰራው።
የዓለማችን ግዙፉ ቴሌስኮፕ በአቅራቢያው ያሉትን የማይታወቁ ፕላኔቶች ያላቸውን ባህርይ ከመርመር ጀምሮ በሚቀጥሉት አምስት እና አስር ዓመታት ውስጥ በህዋ ሳይንስ ውስጥ ተስፋ የሚፈነጥቁ ተግባራትን ያከናውናል ተብሏል።
የመጀመሪያው እስያዊ ዝርያ ያላቸው የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር
ዩናይትድ ኪንግደም በተጠናቀቀው የአውሮፓውያን ዓመት በርካታ ሁነቶችን አስተናግዳለች።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ሥልጣን ከለቀቁ በኋላ ሊዝ ትረስ መንበሩን ተቆጣጥረው 45 ቀናትን ብቻ ካሳለፉ በኋላ ሥልጣናቸውን ለቀዋል።
ይህም በዩኬ ታሪክ አጭሩ የሥልጣን ዘመን ሆኖ ተመዝግቧል።
ከዚያም ሊዝ ትረስ በሪሺ ሱናክ ተተክተዋል። ሪሺ ሱናክ ጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ሥልጣኑን በመረከብም የመጀመሪያው እስያዊ ዝርያ ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ተመዝግበዋል።
ሪሺ ወላጆቻቸው ትውልዳቸው ከምሥራቅ አፍሪካ ሲሆን የዘር ግንዳቸው ከሕንድ የሚመዘዝ ነው።
ያለማይክሮስኮፕ የታየው የዓለማችን ትልቁ ባክቴሪያ
ተመራማሪዎች ሰኔ ወር ላይ የዓለማችንን ትልቅ ባክቴሪያ አግኝተዋል።
ቲኦማርጋሪታ ማግኒፊካ የተባለውን የባክቴሪያ ዝርያ ለማየት ማይክሮስኮፕ አያስፈልግም።
አዲስ የተገኘው ፍጥረት ከአንድ የሽፋሽፍት ጸጉር ጋር ተመሳሳይ ቅርጽ እና መጠን አለው።
ወደ 1 ሴንቲሜትር የሚጠጋ ርዝመት አለው።
በቀላሉ ለማስረዳት ከሚታወቁት ትላልቅ ባክቴሪያዎች 50 እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን፣ በሌጣ ዐይን የሚታይ የመጀመሪያው ባክቴሪያ ሆኗል።
በዓለም ትልቁ እና በዐይን ሊታይ የሚችለው ይህ ባክቴሪያ የተገኘው በፍሬንች ካረቢያን ውሃ ውስጥ የሰጠመ ዛፍ ላይ ተጣብቆ ነበር። ባክቴርያው እንደ ሌሎች ባክቴርያዎች ሰዎችን ለሕመም የሚያጋልጥ ግን አይደለም።