የዓለማችን ግዙፉ ቴሌስኮፕ ወደ ጠፈር መጠቀ

አስር ቢሊዮን ዶላር ያህል የፈጀውና ጄምስ ዌብ የተሰኘው የዓለማችን ግዙፍ ቴሌስኮፕ ወደ ጠፈር መጥቋል።

ግዙፉ ቴሌስኮፕ በጠፈር ላይ ያሉ ከዋክብትን ይቃኛል እንዲሁም ምርምር ያደርጋል።

በአቅራቢያው ያሉትን የማይታወቁ ፕላኔቶች ያላቸውን ባህርይ ከመርመር ጀምሮ በሚቀጥሉት አምስት እና አስር አመታት ውስጥ በህዋ ሳይንስ ውስጥ ተስፋ የሚፈነጥቁ ተግባራትን ያከናውናል ተብሏል።

በአሜሪካ የህዋ ምርምር ተቋም፣ ናሳ አማካኝነት የመጠቀው ጄምስ ዌብ ወደ መዳረሻው ለመድረስ አንድ ወር ያህልም ይፈጅበታል።

ቴሌስኮፑ መነሻውን ያደረገው በደቡብ አሜሪካ ሰሜናዊ ምስራቅ የባህር ዳርቻ ላይ በምትገኘው የፍሬንች ጉያና የጠፈር ወደብ ነው።

ወደ ምህዋር የተደረገው በረራ ከግማሽ ሰአት በታች የፈጀ ሲሆን በኬንያዋ ማሊንዲ የጠፈር መቃኛ የምድር አንቴና መሰረት የተሳካ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ታይቷል።

ጄምስ ዌብ የተሰኘው ቴሌስኮፕ ስያሜውን ያገኘው የሃብል ቴሌስኮፕን ያመጠቀው አፖሎ ሙን ተብሎ የሚጠራው ዘመቻን ንድፍ ካወጡት በአንደኛው ነው።

ሆኖም ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ እና ካናዳ የጠፈር ኤጀንሲዎች የተውጣጡ መሐንዲሶች አዲሱን ቴሌስኮፕ ከቀድሞው ሃብል ቴሌስኮፕ በ100 እጥፍ በበለጠ ሃይለኛ አድርገው ገንብተውታል።

"ጄምስ ዌብ ከትሮፒካል ሬይን ፎረስት ተነስቶ ጠፈር ወደተወለደችበትና የሁሉ ነገር ጅማሮ ወደሆነው ጉዞውን ጀምሯል" ሲል የናሳ የቴሌቪዥን ተንታኝ ሮኬቱ ምድርን ለቆ በወጣበት ቅጽበት ተናግሯል።

የቴሌስኮፑን መምጠቅ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረና ለባለሙያዎችም ጭንቅ ነበር።

በዓለም ዙሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በፕሮጀክቱ ላይ ላለፉት 30 ዓመታት ሰርተዋል። የጄምስ ዌብ መመንጠቅ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ ውስብስብ ተከታታይ እንቅስቃሴዎች ጅማሮም እንደሆነ ተገልጿል።

ቴሌስኮፑ ከመሬት በላይ 1.5 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኝ ተመልካች ጣቢያ እየሄደ ነው።